Print this page
Saturday, 28 December 2019 13:40

ጎንደር ለጥምቀት እየተሞሸረች ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

    - ፋሲል ቤተ
             - መንግስት ነፍስ ይዘራል ተብሏል
             - ጎንደር ለጥምቀት በዓል አስፓልቷን ታጥባለች
             - ነዋሪዎች እንግዶችን በየቤታቸው ያሳድራሉ

            በዘንድሮው የጎንደር የጥምቀት በዓል ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይታደማሉ ተብሎ… የሚጠበቅ ሲሆን የጎንደር ከተማ ለበዓሉ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገች ነው ተብሏል። ስለ በዓሉ ዝግጅት በቅርቡ የከተማው ተቀዳሚ ም/ከንቲባ ሆነው ከተሾሙት አቶ ማስተዋል ስዩም ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ቆይታ አድርጋለች፡፡


            ምንም እንኳን ሂደቱ ረጅም ጊዜ ቢወስድም እርስዎ በከንቲባነት በተሾሙ ማግስት የጐንደር መለያ የሆነው የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡ ገዳም ነኝ ብለው ያስባሉ?
እንደሚታወቀው ጥምቀት በጐንደር በተለየ ሁኔታ ይከበራል፡፡ ምናልባትም ዩኔስኮ ለመመዝገብም እንደ አንድ ድርሻ የሚወስደው የጐንደር ጥምቀት ነው:: በኢትዮጵያም ትልቅ ገጽታ የሚፈጥር ነው:: እኔም ወደ ኃላፊነቱ እንደገባሁ አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ በስሩ ዘጠኝ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተመርጠው እንቅስቃሴ ጀምረን ነበር - ጥምቀትን በተለየ መልኩ ለማክበር ይህ እንግዲህ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ከመታወጁ በፊት ነው፡፡ ህዝቡም አብሮ ለመስራትና ጐንደርን ለመቀየር ተነሳሽነቱና መነቃቃት ስለነበረው ማለቴ ነው፡፡ እናም ጐንደርን በዚህ በዓል አማካኝነት ቀይረን ህዝቡን ጋብዘን፣ ኢንቨስትመንቱንና ቱሪዝሙን ማሳደግና ኢንዱስትሪዎችን መሳብ አለብን ብለን እንቅስቃሴ ጀምረን ነበር፡፡ እንዳልኩሽ በዚህ ረገድ ህዝቡ አንድ ዓይነት ስሜት ነው ያለው፤ እድገት ይፈልጋል፡፡ መንግስትና ህዝብ ሳይገፋፉ አብረው ቢሰሩ ለውጥ ይመጣል በሚለው ተስማምተን፣ ጥምቀትን በልዩ ሁኔታ ለማክበር በእንቅስቃሴ ላይ እያለን ‹‹በዩኔስኮ ተመዘገበ›› የሚለው ዜና መጣ፡፡ ይሄ ደግሞ በግሌም በቢሮውም ትልቅ ደስታን ፈጥሮብናል፡፡
በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ ከመደበኛው የጥምቀት አከባበር ምን የተለየ ዝግጅት ታደርጋላችሁ?
ዘንድሮ ጥምቀትን በተለየ ሁኔታ ለማክበር ለሁሉም ጥሪ እያደረግን ነው:: ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና ለሁሉም የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲሁም ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ለሚኒስትሮች፣ ለአምባሳደሮች፣ በአሜሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጥሪ ተዘጋጅቷል፡፡ ኤምባሲዎች ቱሪስቶችን እንዲጠሩልንም ጭምር ጥያቄ አቅርበናል በርካታ ሰው ነው የሚመጣው፡፡
በእርስዎ ፊርማ በወጣ ደብዳቤ፤ ኤርትራዊያን ጥምቀትን በጐንደር እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ እስኪ ስለ እሱ ይንገሩኝ?
እውነት ነው፡፡ ለኤርትራዊያን እንደ ከተማችን ጥሪ አቅርበናል፤ ክልሉም ጥሪ ያደርጋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ደግሞ እንደ አገር ጥሪ ያቀርባል፡፡ እስካሁን በተደረገው ጥሪ፣ ከሁሉም አቅጣጫ በጐ ምላሽ እያገኘን ነው፡፡ እኛ የምንፈልገው አንድነት፣ ሰላም፣ ፍቅር ነው፡፡ ይህ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን መገለጫም ነው፡፡
ባለፈው ዓመት እንኳን ወደ ግማሽ ሚሊዮን ገደማ ህዝብ በጥምቀት በዓል ላይ መታደሙን የከንቲባ ጽ/ቤት ይፋ አድርጐ ነበር፡፡ ዘንድሮ በዩኒስኮ ከመመዝገቡና እያደረጋችሁት ካላችሁት ጥሪ አንፃር ምን ያህል ታዳሚ ይጠበቃል? ከፀጥታ፣ ከሆቴልና መስተንግዶ፣ ከጽዳትና ከበጀት አኳያ እየተደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?
ዝግጅቱን በተመለከተ በቢሮ ደረጃም ሆነ ዘጠኙ ንዑሳን ኮሚቴዎች በየተሰማሩበት ዘርፍ በስራ ላይ ናቸው፡፡ ከመስተንግዶ፣ ከኮሚዩኒኬሽን፣ ከባህል፣ ከፀጥታ፣ ከፍትህ (ችግሮች ሲያጋጥሙ እዛው የሚፈታ ማለት ነው) ሁሉም በንቃት እየሰሩ ነው፡፡ ከዚያ አልፎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጐንደር ላይ የራሷን ዝግጅት እያደረገች ነው:: የጐንደር ኦርቶዶክስ ወጣቶች ማህበርም የታቦት አስተጃጀብ ስርዓትንና መሰል ዝግጅቶችን እየሰራ ይገኛል፡፡ የጐንደር ወጣቶች ማህበርም ሁለት ሺህ ጃኖ አሰፍተው ከአለባበስ ድምቀት ጀምሮ በተለየ ሁኔታ ታቦታትን ለማጀብ በዝግጅት ላይ ናቸው:: ሌሎችም በየሰፈሩ ያሉ ወጣቶች ሰረገላ በመስራት፣ የባህል ልብስ በማስፋት በዓሉን ለማድመቅ ሁሉም በየፊናው እየተጋ ይገኛል:: ከዚህም አልፎ ከተማውን ለማጽዳት እንዲሁም በየቦታው የተደፉ የግንባታ ተረፈ ምርት ለማስወገድ ፕሮግራም ተይዟል፡፡ ህብረተሰቡ በየአካባቢው የአስፋልት ማጠብ ተግባር ያከናውናል፡፡ ለዚህም ውሃ በብቃት የሚያቀርቡ ቦቴዎች ሳይቀር ተዘጋጅተዋል:: ዘንድሮ በጥምቀት በዓል ላይ ለሚገኙ ታዳሚዎች ለየት ያለ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ፋሲል ግንብ፤ ነፍስ ይዘራል፡፡
ነፍስ ይዘራል ሲባል… በምን መልኩ ነው?
ህይወት ይዘራል ማለት አንድ እንግዳ ወደ ፋሲል ቤተመንግስት ሲመጣ፣ የድሮ ጥበቃዎችን ከእነ አለባበሳቸው ያያል፣ አጋፋሪ ይቀበለዋል፣ ደጃዝማቹ  ራሱ በቀደመው አለባበስና ሥርዓት ተቀብሎ ወደ ንጉሱ ይወስደዋል፣ ቤተመንግስት ሲገባ ንጉሱና ንግስቲቱ ይቀበሉታል፣ ከዚህ ቀጥሎ ወደ ግብር አዳራሹ ገብቶ ይመገባል - ሞሰቡ፣ ጠላው፣ ጠጁ ይቀርባል፡፡ በዚህ መሃል ባለቅኔው ቅኔ ይዘርፋል፡፡ አዝማሪው በማሲንቆው ታጅቦ እንግዳውን ያዝናናል፡፡ የጐንደር አለባበስና እስክስታው ይቀርባል:: ሌላው ቀርቶ በቤተ መንግስቱ ፈረስ ቤት፣ ፈረሶች አጊጠውና ተሸልማው ይቆማሉ፡፡ በሁሉም የቤተ መንግስቱ በሮች የድሮ አይነት ጥበቃዎች ውጭ ይቆማሉ፡፡ ብቻ ቤተ - መንግስቱ ነፍስ ዘርቶ፣ በቀድሞ መንፈሱ ይሰራበታል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከክልል ለመጡ ኃላፊዎች የመጀመሪያ ሙከራችንን አሳይተናል፡፡
በጀትን በተመለከተ ከተማው ያለው ውስን ስለሆነ በቂ አይሆንም፤ ነገር ግን ስፖንሰሮች እናግዛለን ብለው ወደ እኛ መጥተዋል፡፡ ይህ አበረታች ነው፡፡ ምክንያቱም ለቀጥታ ስርጭት፣ ለመስተንግዶና ለመሰል ወጪዎች በጀት በጣም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ የሀብት ማፈላለግ ስራው ተጀምሮ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው:: ክልሉንም፣ ፌደራል መንግስትንም ትልልቅ ኩባንያዎችንም እየጠየቅን ነው፡፡ ሆቴሎችን በተመለከተ ሆቴሎቹ የኮሚቴ አባል ሆነው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ በማህበር ተደራጅተውም ስራ ጀምረዋል፡፡ እኔም በበኩሌ ኦረንቴሽን ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ ምን ያህል ሰው ይጠበቃል ብለሽኝ ነበር፤ እኛ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰው ይመጣል ብለን እንጠብቃለን:: ምክንያቱም ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በርካታ ሰው እየተጋበዘ በመሆኑ የአልጋ እጥረት እንደሚኖርም ይጠበቃል:: ሆቴሎች ከመላው ዓለም ለሚመጡ ቱሪስቶች ደረጃቸውን የጠበቀ ድንኳን ተክለው እንዲያስተናግዱ  ተስማምተናል፡፡ ሆቴላቸው ከሞላ ማለት ነው:: ከዚህ ሁሉ ተርፎ ማረፊያ ከጠበበ ልክ እንደ ዩኒቨርሲቲው የቃል ኪዳን ፕሮጀክት ሁሉ የታሰበ ነገር አለ:: በዩኒቨርስቲው ፕሮጀክት፣ አንድ ቤተሰብ 10 ልጅ በደስታ በቃልኪዳን ወላጅነት ተረክቧል፡፡ እኔም አራት ከተለያየ ቦታ የመጡ ልጆችን ተረክቤያለሁ፡፡ ልክ እንደዚያው ሁሉ “ቤት ለእምቦሳ” የተሰኘ ፕሮጀክት ቀርፀናል:: ይህ ምን ማለት ነው? እያንዳንዱ የጐንደር ቤተሰብ፣ ለጥምቀት የመጣውን እንግዳ አንድ አንድ እየወሰደ የሚያሳድርበት ፕሮጀክት ነው፡፡ ይሄ ሰው ሳይንገላታና ሳይቸገር በአግባቡ ተስተናግዶ የሚመለስበት ፕሮጀክት ነው፡፡ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰው የሚያስተናግድ ሆቴል እንደማይኖረን እሙን ነው ስለዚህ አማራጮችን ሁሉ ነው እያዘጋጀን ያለነው፡፡ የዩኒቨርስቲ መኝታዎችን ሁሉ ለመጠቀም እገዛ ጠይቀናል፡፡
የፀጥታን ጉዳይ በተመለከተ እኛ ይህንን ሁሉ እንግዳ ጠርተን የፀጥታውን ሁኔታ አስተማማኝ አለማድረግ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ የፀጥታ አካላት ስልጠናና ግንዛቤ ተሰጥቷቸዋል፡፡  በኬላ ፍተሻ፣ የተለየ እንቅስቃሴ ሲታይ ማህበረሰቡ እንዴት ለፀጥታ አካላት መጠቆም እንዳለበት ስልጠናና ግንዛቤ ተሰጥቷል፡፡ አሁን ላይ ሁሉም የጐንደር በሮች እየተጠበቁ ነው፡፡ የፀጥታ አካላት በየድርሻቸው በንቃትና በተጠንቀቅ ይሰራሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ህብረተሰቡና ወጣቱ ለፀጥታው ትልቅ ድርሻ አለው:: በጣም በትጋት የሚሰሩና ልምድ ያላቸው ወጣቶች አሉን፡፡ እነሱም የበኩላቸውን ይወጣሉ፡፡ ስለዚህ ለደህንነት የሚያሰጋ የፀጥታ ችግር አይኖርም፡፡ የክርስቲያን ህብረቱ በስሩ ከ10ሺህ በላይ ወጣት አለው፡፡ ሙስሊሙ ማህበረሰብም ለፀጥታው ከጐናችን በመቆም የተለመደ እገዛውን ያደርግልናል፡፡ የጐንደር ገጽታ እንዳይበላሽና ችግር እንዳይገጥም ሁሉም በተጠንቀቅ እየሰራ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
በአሁን ሰዓት ጐንደር በጥሩ ሰላም ላይ ትገኛለች፡፡ እንግዶች ከወዲሁ መምጣት ጀምረዋል፡፡ በቅርቡም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር መጥተው ሁሉን ነገር አይተው ተመልሰዋል፡፡ ትልልቅ ፎረሞችም በከተማው እየተካሄደ ነው:: የፀጥታውን አስተማማኝነት በዚህ ደረጃ መግለጽ ይቻላል፡፡
ጎንደር ላይ እንደ ችግር ሲነሳ የሰማሁት…  የጥምቀት በዓል ሲቃረብ የመኝታ ዋጋን ጨምሮ ሁሉ ነገር መወደዱን ነው፡፡ ይህን እንዴት ያዩታል? የመቆጣጠሪያ መንገድ አላችሁ?
ተገቢ ጥያቄ ነው! ለሆቴል ማህበሮች በዝርዝር ከሰጠናቸው የቤት ስራ አንዱ ይሄ ያነሳሽው ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ዋጋ ጭማሪ ላይ ጥንቃቄ አድርጉ፤ ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪ ካደረጋችሁ  ሆቴሉን እስከ መዝጋት የሚያደርስ ቅጣት ይጣላል›› ብለን አስጠንቅቀናል። ለዚሁ ጉዳይ አንድ ቡድን ተቋቁሞ የቁጥጥር ስራ ለመስራት ተዘጋጅቷል። ይሄ ቡድን በየሆቴሉ በመሄድና ተስተናጋጆችን በማግኘት የመስተንግዶውን ሁኔታ፣ የአልጋውን ዋጋ ሁሉ በመጠየቅ ያልተገባ ክፍያና የመስተንግዶ መጓደል ከተገኘ፣ በሆቴሉ ላይ አፋጣኝ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ እንግዶችም ቢሆኑ ባረፉበት ሆቴል ችግር ካጋጠማቸው፣ ለዚሁ ኮሚቴ ጥቆማና ቅሬታ እንዲያቀርቡ በዚሁ አጋጣሚ መግለፅ እወዳለሁ።
በቅርቡ ጐንደር ዩኒቨርሲቲ መተግበር የጀመረው ለተማሪዎች የቃል ኪዳን ወላጅ የማገናኘት ፕሮጀክት ሃሳብ አፍላቂ እርስዎ እንደሆኑም ሰምቻለሁ፡፡ ሃሳቡ እንዴት መጣልዎት?
እኔ በመሰረቱ ሃሳቡን የወጠንኩት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲተገበር ነው፡፡ ፕሮጀክቱ እንደ ሀገር ይንቀሳቀሳል ብዬ ባስብም ሁኔታዎች ምቹ ሊሆኑልኝ አልቻሉም፡፡ ነገር ግን የጐንደር ዩኒቨርሲቲ የስራ ባልደረባ ስለነበርኩኝ እድል አግኝቼ ፕሮጀክቱን አቀረብኩኝ፡፡ ተቀባይነት አገኘ፡፡ አሁን በጥሩ ሁኔታ መተግበር ጀምሯል:: ሃሳቡን ያፈለቅኩት የኢትዮጵያን ችግር ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ችግር እንደ ዜጋ ይሰማኛል ያመኛልም፡፡ ስለዚህ ከዚህ ህመም ለመውጣት የኔ አስተዋጽኦ ምን ሊሆን ይችላል ብዬ ማሰብ ጀመርኩኝ፡፡ በዚህ ወቅት ዋናው የሚያስፈልገው ነገር ፍቅር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አንድነትና ሰላም መመስረት አለባቸው፡፡ ይሄ ሠላምና አንድነት ደግሞ ከልማት ሁሉ ይቀድማል፡፡ እናም ይህንን ነገር ለምን አናደርግም አልኩኝ፡፡ ምክንያቱም የዚህ የወላጅና የተማሪ ቤተሰባዊ ትስስር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ተማሪን በልጅነት የተቀበለ ወላጅ አገርን ከጥፋት የመታደግ እድሉ ሰፊ ነው፡፡ እርግጥ ሆላንድ እያለሁ በዚህ ደረጃም ባይሆን ተቀራራቢ ሃሳብ አይቻለሁ፡፡ እኔ ያንን ሃሳብ ነው ያሳደግኩት፡፡
ሐሳቡ አገራችን ላይ ቢተገበር አሁን ከገባንበት የዘረኝነት እርስ በእርስ በክፋት የመተሳሰብና አገር የመበተን አደጋ እንድናለን፡፡ በተለይ የአገሪቱ ሃይል የሆነው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በሄደበት ወላጅ ካገኘ፣ ኢትዮጵያኒዝምን በአንዴ ማስረጽ ይቻላል በሚል ሃሳቡ ዳብሮ፣ 1500 ያህል ተማሪዎችን ከወላጅ ጋር አገናኝተናል፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላም ሁለተኛ ዙር ትግበራ አለን፡፡ ያኔም ከዚህ በላይ ተማሪዎችን ከወላጅ ጋር እናገናኛለን የሚል እቅድ አለን፡፡ የጐንደር ወላጆችም ለመላው የኢትዮጵያ ልጆች ወላጅ ሆነው፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ትስስር ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፤ ፕሮጀክቱ አገር አቀፍ እንዲሆን ነው የኔ ፍላጐት:: በዚህ ጉዳይ ላይ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ከፕሮፌሰር ሒሩት ገ/ማርያም ጋር ተወያይተንበታል፡፡ ሚኒስቴሩ ይህን እንደሚገብር ቃል ገብተዋል:: በዚህ ፕሮጀክት የዘረኝነት መንፈስ ተወግዶ ቤተሰብን በማስተሳሰር፣ የኢትዮጵያ ቤተሰብ ይመሰረታል ማለት ነው፡፡ 40ዎቹም ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ የቤተሰብ ፕሮጀክት ይተሳሰራሉ፡፡
እንደሰማሁት በከንቲባነት የሚያገለግሉት ያለ ደሞዝ ነው፡፡  እውነት ነው?
እውነት ነው፤ ደሞዝ አልቀበልም፡፡ ለእኔ የሚሆን ነገር አለኝ፡፡ አሁን አገልግሎቴ ነው የተፈለገው፤ አገለግላለሁ፡፡ ለአንድ አመት ካገለገልኩ በቂ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በመጨረሻ በዓሉን አስመልክተው የሚያስተላልፉት መልዕክት አለ?
የጎንደር የጥምቀት በዓል ‹‹ሰላምና አብሮነት በጎንደር ጥምቀት›› በሚል መሪ ቃል ነው የሚከበረው፡፡ ሰላም፣ አንድነት፣ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማምጣትና ጎንደርን ወደ ቀደመ ክብሯ መመለስ ነው ህልማችን:: የጎንደር መገለጫም ሰላምና አንድነት በመሆኑ ሁሉም ከተለያየ አቅጣጫ ወደ ጎንደር መጥቶ ጥምቀትን እንዲያከብር ስለ ኢትዮጵያ እንዲዘመር በአክብሮት ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

Read 4781 times