Saturday, 28 December 2019 13:35

የ35 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የጨው በረንዳ የእሳት አደጋ 31ኛ ዓመት

Written by  ብርሃኑ ሰሙ ethmolla2013@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

  አቶ በላይነህ ጎሳዬ፣ ከ31 ዓመት በፊት ወታደር ሆኖ፣ በሰሜን ጦር ግንባር አገሩን በማገልገል ላይ ሳለ ነው፤ በትውልድ መንደሩ ጨው በረንዳ፣ የእሳት አደጋ ተከስቶ፣ በርካታ ሕይወትና ንብረት መጥፋቱን የሰማው፡፡ ‹‹በኤርትራ ጦር ግንባር እያለሁ በሰማሁት አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ለመዘከር ሃሳቡ በውስጤ ከተፀነሰ ቀይቷል›› የሚለው አቶ በላይነህ፤ የፊታችን ሃሙስ ታህሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም፤ 35ቱ ሰዎች በድንገተኛው አደጋ ሕይወታቸውን ባጡበት ስፍራ፣ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ ሻማ በማብራት ለማሰብ ከጓደኞቼ ጋር አቅደናል ብሏል፡፡    
***
ጨው በረንዳ መርካቶን በስተሰሜን ከሚጎራበቱ መንደሮች አንዷ ናት፡፡ በዙሪያዋ ቁጭራ ሠፈር፣ ክፍለ ሀገር አውቶቢስ መናኸሪያ፣ አባ ኮራን ሠፈር፣ አዲሱ ሚካኤል… ያዋስኗታል፡፡ ወደ መንደሩ በሁለት አቅጣጫ መግባት ይቻላል፡፡ ከፒያሳ ጳውሎስ ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ ጉለሌ ቤተል መካነ ኢየሱስ ሲደረስ ወደ ግራ በመታጠፍ ወይም ከጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ክፍለ ሀገር አውቶቢስ ተራ ሲመጣ፣ ጎጃም በረንዳ አካባቢ የሚገኘው ወለጋ ሆቴል ጋ ሲደረስ ወደ ቀኝ በመታጠፍ ጨው በረንዳ ይደረሳል፡፡ ውስጥ ለውስጥ የሚያስኬዱ በርካታ መግቢያዎችም አሏት፡፡
ጨው በረንዳ የአሁኑን መጠሪያዋን ከማግኘቷ በፊት የተለያዩ ሥሞች ነበሯት፡፡ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ዘመን ከአዲስ አበባ የተለያዩ መንደሮች ተነስተው፣ መርካቶ እንዲሰፍሩ የተደረጉ ኢትዮጵያዊያንን እንዲያስተዳድር የተቋቋመው ‹‹ጠቅላይ ቢሮ››፤ የዚህች መንደር አንዱ መጠሪያ ነበር:: በቢሮው ያገለግሉ የነበሩ ጦር አንጋች ባንዳዎች መኖሪያም ነበረች ይባላል፡፡ ከነጻነት በኋላ ከአርበኝነት የተመለሱ የንጉሠ ነገሥቱ ተከታዮች ስለሰፈሩበት ‹‹ነፍጠኛ ሠፈር›› ተባለች፤ ዛሬም ድረስ በዚያ ሥሟ የሚጠሯት አሉ፡፡ የአሁኑን መጠሪያዋን ያገኘችው ግን ከአሰብ የሚመጣ ጨው ማራገፊያ ትልቅ መጋዘን ከተሰራባት በኋላ ነው፡፡
በመንደሩ ውስጥና ዙሪያ በርካታ ሰዎች ታሪካዊ ሥራዎችን አኑረውበት አልፈዋል፡፡ የልዑል ራስ እምሩ ጥብቅ ደን ይገኝበት የነበረው ግቢንና ጨው በረንዳን የሚለያቸው ከእስላም መቃብር የሚመጣው ወንዝ ነው፡፡ ከጨው በረንዳ በስተሰሜን የሚገኘው የጉለሌው እስላም መቃብር (ኮሶ ሜዳም ይባል ነበር) የቀብር አገልግሎት እንዲሰጥ በአፄ ምኒልክ ዘመን ለሙስሊሞች የተመራ ቦታ ነው፡፡ በዚሁ አካባቢ በ1910 ዓ.ም የተቋቋመው የሕንዶች አስከሬን ማቃጠያ ግቢና የአይሁዳዊያን መቃብር ስፍራም ይገኛል፡፡
ለጨው በረንዳ መንደር ስያሜ ምክንያት የሆነውን መጋዘን የሰሩት አባ ቦራ፣ መኖሪያቸው ከመጋዘኑ በስተጀርባ እዚያው ጨው በረንዳ ነበር፡፡ 30 የሚደርሱ መኝታ ክፍሎች ያሉት (አሁን መርሻ መታሰቢያ) ሆቴል ሕንጻን የሰሩት አቶ ተክሌ ጉንጆ፣ ሌላኛው የመንደሩ ባለውለታ ናቸው:: የመርካቶ አስፋወሰን ሆቴል ሕንጻን በማስገንባት የሚታወቁት አቶ ነጋሽ ቢርቢርሶ፣ የዚሁ መንደር ነዋሪ ነበሩ:: ከአንዋር መስጊድ ፊት ለፊት የነበረው የመዲና ሕንጻ ባለቤት ሐጂ ዑመር ኢማም፣ በጨው በረንዳ መጋዘኖች ነበሯቸው:: በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ከነበሩ የመርካቶ ነጋዴዎች ‹‹በእሳቸው ደረጃ ረብጣ ብር የነበረው ነጋዴ ማንም የለም›› የሚባልላቸው አቶ ተስፋዬ ፎዬ፤ በከተማዋ ውስጥ ከነበሯቸው 500 የሚደርሱ ቪላ ቤቶች የተወሰኑት በጨው በረንዳ ነበር የሚገኙት:: በደርግ ዘመን ቀበሌ ሲቋቋም፣ ጨው በረንዳን ያስተዳድር የነበረው የከፍተኛ 7ቱ 33 ቀበሌ፤ ከአቶ ተስፋዬ ፎዬ የተወረሰ ቪላ ነበር፡፡
የበርበሬ፣ የቆዳ፣ የቡና ቦርድ (በደርግ ዘመን እፍ እፍ ኮሌጅ ይባል ነበር)… በርካታ መጋዘኖች የሚገኙባት ጨው በረንዳ፤ እሁድ ታህሳስ 23 ቀን 1981 ዓ.ም ማለዳ በሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥፋት ያስከተለ የእሳት አደጋ ተከስቶባት ነበር፡፡ ለእሳቱ አደጋ ምክንያት የሆነው 32 ሺህ ሊትር ነዳጅ የጫነ ቦቴ (ከነተሳቢው) ተገልብጦ ቁልቁል የፈሰሰው ነዳጅ፣ ደጅ ላይ  ከተለኮሰ እሳት ጋር ተገናኝቶ በመቀጣጠሉ  ሲሆን፤ ነዳጅ ለጫነው ቦቴ መገልበጥ ዋነኛ ምክንያቱ በሙቀትና ቅዝቃዜ ቀልጦ አስፋልቱ ላይ የተንጠባጠበ ጨው  ነው፡፡
አባ ቦራ ያሠሩት የጨው መጋዘን፣ በደርግ ዘመን ከተወረሰ በኋላ፣ የመንግሥት ተቋም የሆነው ጅ.ን.አ.ድ ተረክቦት ከአሰብ የሚያስመጣው ጨው ዋነኛ ማራገፊያ አደረገው፡፡ ከአሰብ የሚመጣው ምርት ብዛትና የመጋዘኑ የመያዝ አቅም ባለመመጣጠኑ፣ ጨው የጫኑ በርካታ ስካኒያ ባለተሳቢ መኪኖች ከነጭነታቸው፣ ሰልፍ እንደያዙ ለቀናት ብቻ ሳይሆን ለሣምንታትም ይቆዩ ነበር፡፡ ቀዳሚዎቹ ጭነታቸውን ቢያራግፉም አዲስ መጪዎቹ ከስር ከስር ስለሚተኳቸው፣ በመቶ ሜትሮች የሚለካው ሰልፍ ሳይቀንስ ወራት ይቆጠር ጀመር፡፡ በኤሊ ጉዞ እየተንፏቀቁ ጭነት ለማራገፍ የሚጠባበቁት መኪኖች፣ የቀን ሃሩርና የለሊት ቁር ሲፈራረቅባቸው፤ በላያቸው ሸራ ለብሶ የተጫነው ጨው እየሟሟ፣ አስፋልቱ ልይ በመንጠባጠብ፣ እግረኞችን አንሸራትቶ ሲጥል ነበር፣ የከፋ አደጋም ሊያስከትል እንደሚችል ምልክቱ የታየው፡፡ ነገር ግን አደጋውን ቀድሞ ለመከላከል የሞከረ አልነበረም፡፡
ታህሳስ 23 ቀን 1981 ዓ.ም፡፡ እሁድ ማለዳ፡፡ በአካባቢው ባሉት በአዲሱ ሚካኤልና በራጉኤል የለሊት ቅዳሴ መጀመሩን ሰምተው፣ ማልደው በመነሳት፣ ወደ አብያተ ክርስቲያናት በሄዱ ነዋሪዎች ነበር የመንደሩ እንቅስቃሴ የተጀመረው:: በመቀጠል የመርካቶው አንዋር መስጊድ ‹‹አዛን››ን ሰምተው ከእንቅልፋቸው የነቁ የመንደሩ ወጣቶች ተጠራርተው፣ ሳምንታዊ መዝናኛቸው ወደሆነው 72 ደረጃና ጃን ሜዳ አቀኑ፡፡ ከጎጃም በረንዳ ወደ ሩፋኤል ተጓዥ የሚያመላልሱ ‹‹ውይይት›› ታክሲዎች፣ ከላይ ታች ውር ውር ሲሉ ድምፃቸው መሰማት ጀመረ፡፡ የአንድ እግር ጉዳተኛ የነበረው ጋሽ በቀለ፣ ዕለቱ ሰማዕቱ ጊዮርጊስ የሚዘከርበት መሆኑን በነጎድጓዳ ድምጹ እያወጀ፣ የልመና ተግባሩን ጀምሯል:: አእዋፋት የንጋት ማብሰሪያ ዜማቸውን ማሰማት ሳያበቁ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ፤ በጨው በረንዳ መጋዘንና በተስፋዬ ፎዬ የግንብ ቤቶች መሐል በሚገኙ፣ የቆርቆሮ መኖሪያ ቤቶች ደጅ፣ 32 ሺህ ሊትር የጫነው ቦቴ ከነተሳቢው አስፋልቱ ላይ የቀለጠው ጨው አንሸራትቶት ተገለበጠ፡፡  
ከወለጋ ሆቴል በጨው በረንዳ በኩል ወደ ጉለሌ ቤቴል መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የሚወስደው የአስፋልት መንገድ፣ በወቅቱ 7 ሜትር ያህል ስፋት የነበረው ሲሆን፤ ዳገታማም ነበር፡፡ ከታች  የመጣው ቦቴ ተገልብጦ፣ የጫነው ነዳጅ ቁልቁል መፍሰስ እንደጀመረ፣ በመንደሩ ጠላ በመነገድ የሚተዳደሩ ወይዘሮ፣ ለጠላ እንኩሮ ደጃቸው ላይ የለኮሱትን እሳት ሲያገኝ፣ በግምት የ200 ሜትር ርዝመትና የ50 ሜትር ከፍታ ያለው የእሳት ግድግዳ ፈጠረ፡፡ ጨው በረንዳ በዋይታ፣ በጩኸትና ሽብር ተሞላች:: ነፍሳቸውን ለማዳን፣ እርቃነ ሥጋቸውን የእሳቱን ነበልባል ሰንጥቀው ለመውጣት የሚሞክሩ ሰዎች ይታዩ ነበር…::
ለእሳቱ የቀረበው ሕይወቱን ለማዳን፣ ከእሳቱ የራቀው ንብረት ለማትረፍ ትርምስ ሆነ፡፡  ታህሳስ 23 ቀን 1981 ዓ.ም ማለዳ በጨው በረንዳ የተከሰተው ድንገተኛ የእሳት አደጋ የ35 ሰዎችን ሕይወት ቀጠፈ፤ የሚያሳዝነው አብዛኞቹ የዘጉትን ቤት ሳይከፍቱ፣ ከተኙበት አልጋ ሳይነሱ ነበር የእሳት ራት የሆኑት፡፡ ማልደው ወደ አብያተ ክርስቲያናት የሄዱ እናትና አባቶች፣ ለስፖርታዊ ጨዋታ ወደ 72 ደረጃና ጃን ሜዳ የሄዱ ወጣቶች ወደ ሠፈራቸው ሲመለሱ ቅስም የሚሰብር ሀዘን ገጠማቸው:: በእሳት አደጋው ቤት ንብረታቸው ወድሞ ሕይወታቸው የተረፈ ሰዎች፤ በፈለገ ብርሃን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ እንዲያርፉ ተደረገ፡፡ በወቅቱ አገሪቱን ያስተዳድሩ የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አደጋው በደረሰ ማግስት በቦታው ተገኝተው ጉዳቱን ካዩ በኋላ፣ ተጎጂዎቹን አጽናንተው ተመለሱ፡፡ በመንግሥት ይዞታ ስር የነበሩት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ፣ አዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች፣ በየወሩ ይታተም የነበረው የካቲት መጽሔት ለአደጋው ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ዘገቡት፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በጋዜጠኛ ክፍሌ ሙላት የሚዘጋጀውና ከፍተኛ አንባቢ የነበረው ‹‹አድማስ አምድ››፤ በጨው በረንዳ እሳት አደጋ ‹‹ከ15 ቀን በኋላ የወጣችው ድመት›› በሚል ርዕስ፣ በቁፋሮ መገኘቷ አስደናቂ ታሪክ ሆኖ  ተነበበ፡፡ የሟቾቹ ቀጥር ከዕለት ዕለት በሚደረግ ቁፋሮ እያደገ መጥቶ ነው 35 መድረሱ የተነገረው፡፡
በጨው በረንዳ በደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ምክንያት፣ በፈለገ ብርሃን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ እንዲጠለሉ ተደርገው የነበሩት የተጎጂ ቤተሰቦች፣ አዲሱ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ይገኝ በነበረ አነስተኛ የእግር ኳስ ሜዳ ላይ የተሰሩ የቁጠባ ቤቶች ተሰጣቸው፡፡ የእሳት አደጋውን ተከትሎ የተጎጂ ቤተሰቦችን ለማቋቋም በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር ተሞክሮ የተሳካ አስተማሪ ተግባር ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላም በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ በሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ለመዘከር መታቀዱም፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ጭምር ስለሚያስተሳስርና ማህበራዊ ግንኙነትን  ስለሚያጎለብት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡      


Read 1662 times