Saturday, 28 December 2019 13:36

ቦምቡ ፍቅርሽ ቢፈነዳ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

     “አሀ…መጀመሪያ ነገር ፍቅርን ካልጠፋ ነገር ከቦምብ ጋር ማገናኘት ምን ይሉታል! ደግሞ ቦምቡ ከፈነዳ…አለ አይደል… የምን እዳ፣ የምን ጣጣ ነው፡፡ ፈነዳ፣ በቃ ፈነዳ! ዋናው ነገር እሱ
መትረፉ ነው፡፡ ግን እኮ ‘ክሬቲቪቲው’ አሪፍ ነው፡፡--”
       
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…የብር ኢዮቤልዩ ካከበረች በኋላ አራት የዓለም ዋንጫ አልፋ ኳታርን እየጠበቀች ያለች ካፖርት…መሆን ያለባት ሰው ትከሻ ላይ ሳይሆን ሙዚየም ውስጥ ነበር፡፡ እኔ የምለው…ድሮ እኮ ኮት…አለ አይደል በነተበ ጊዜ፣ አዲስ መግዛት አያስፈልግም ነበር፡፡ ይሄኛው የውስጡ ወደ ውጭ ‘ተገልብጦ’ ሲሰፋ፤ አዲስ ሆነ ማለት አይደል! ግዴላችሁም አያስነቃም…ውሀ አይብዛበት እንጂ! ይሄ ኮት ምናምን ‘ገልብጦ’ የመስፋት ነገር አሁንም ካለ አሪፍ ነው፡፡
ልጄ...ዘንድሮ ኑሮ እንደሆን ሌባና ፖሊስ አይነት እያሯሯጠን ስለሆነ፣ በጥንቃቄ መደበቂያን ማዘጋጀት ነው፡፡ “ይህንን ኮት ብሎ ከሚለብስ ምናለ አንደኛውን የቤታቸውን የእግር መጥረጊያም ቢደርብበት!” መባሉ ለሞራልም ጥሩ ስለማይሆን፣ መገልበጥ የሚቻለውን ‘መገልበጥ’ ነው፡፡ (“ይሄ ነገር ደግሞ በክፋት ይመነዘርብኝ ይሆን እንዴ!” ያለው ሰው ማን ነበር?!)
እናማ…ዘዴ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ካልሲ ለምሳሌ በጨቅ፣ በጨቅጨቅ ብትልም ችግር የለም፡፡ ነገር የሚመጣው በትልቁም በትንሹም ንጉስ በሉኝ ማለት ሲመጣ ነው፡፡ እሱዬው እሷዬዋ ላይ ንጉስ መሆን አምሮት እግሮቹን አጣምሮ ካልሲውን ያዝ ለቀቅ ሲያደርግ ተስባ፣ ተስባ ቀዳዳዋ ብቅ አለች አሉ፡፡ ልጅትዬዋ “እኔን ልጅትን ያውም በቀዳዳ ካልሲ!” ብትል ቆዳዋን አዋደደች ምናምን ይባላል! እናማ… ሸላዮች ካልሲ መሳብ ከመጀመራችሁ በፊት አስቀድማችሁ የአዋጭነት ጥናት ነገር ሥሩ ለማለት ያህል ነወ፡፡ 
አለ አይደል… ቁርጥ ቤት ሰዉ ሁሉ ቢላዋውን ሲያፋጭ፣ ሥጋ ሊበላ ሳይሆን ለደፈጣ ውጊያ ሳንጃ በአፈሙዝ የተባለ ነው የሚመስለው፡፡
ስሙኝማ… በቀደም በሆነ ቡቲክ ነገር አጠገብ ስናልፍ፣ አንድ የጥንት ዘፈን በሰፊው ተለቆ ነበር::
ቦምቡ ፍቅርሽ ቢፈነዳ
ለአንቺ ብዬ ገባሁ እዳ
እንደዚያ አይነት ዘፈን አሁንም ይሠራል እንዴ! አሀ…መጀመሪያ ነገር ፍቅርን ካልጠፋ ነገር ከቦምብ ጋር ማገናኘት ምን ይሉታል! ደግሞ ቦምቡ ከፈነዳ…አለ አይደል… የምን እዳ፣ የምን ጣጣ ነው፡፡ ፈነዳ፣ በቃ ፈነዳ! ዋናው ነገር እሱ መትረፉ ነው፡፡ ግን እኮ ‘ክሬቲቪቲው’ አሪፍ ነው፡፡ “ያን  ያህል ሲፈነዳ እሱ እንዴት ተርፎ ለዘፈን በቃ!” የሚለውን ለፎሬንሲክ ባለሙያዎች እንተወውና፣ ባይፈነዳም እኮ አንዲህ ያለ ፍቅር ሁልጊዜም “ከአሁን አሁን ዷ ብሎ፣ እኔንም ዷ እንዳያደርገኝ” ሲል ይኖራል ማለት ነው፡፡ አሀ…እንዲህ ከመሳቀቅ ክሌኦፓትራን መንከባከብ ነዋ! (ቦሌ ምን የመሰለች ሰባት ነው ስምንት ሺህ ብር የምታወጣ የሴቶች ሂል ጫማ አለች አሉ፡፡ ጥቆማ ካስፈለገ ብለን ነው፡፡)
የምር ግን ለምሳሌ ዘንድሮ…አለ አይደል… “በሰላ ጎራዴ አንገቴን ቆርጠሸ…” ብሎ ሚዘፍን ሰው ወላ ‘ሲንግል’ ብሎ ነገር የለ፣ ወላ ‘ኦልዲስ’ ምናምን ብሎ መሸወድ የለ…‘ሲጠየቅ’ ብቻ መልስ ለመስጠት መዘጋጀት ነው:: ሀገር ያግባው፣ አያግባው በማይታወቀው ነገር ‘ቫላንታይንስ ዴይ’ እያለ የአበባ ገበያ በሚያራቁትበት ጊዜ የምን ጎራዴ ምናምን ነው! አንዳንድ ሀገራት እንዲህ ተብሎ ቢዘፈን ምሽቱን የሚያሳልፈው ስቱዲዮ ሳይሆን ሸቤ ይሆን ነበር፡፡ እኛ ዘንድ ግን ሀገር የሚበጠብጥ መፈክር ተይዞ ፌስቡክ ላይ ቢለጠፍ እንኳን ዝም፣ ጭጭ እየሆነ ተቸግረናል::
“ሎሚ ብወረውር ደረቱን መታሁት፣” ብዙም ጣጣ የላትም፤ የሎሚ ዱላ ያልተቻለ የምን ሊቻል ነው! በዘንድሮ አረዳዳችን ግን “አሁን አፕልን የመሰለ ፍሬ እያለ ሎሚ ማለት ለሰው ያለውን ንቀት የሚሳይ ነው፣” ሊባል ይችላል፡፡ ዘንድሮ ለአንድ ሰው የተነገረ ነገር፣ አንድን ሰው ብቻ የሚመለከት ነው የሚባል ነገር አይሠራም:: “በአንድ ሰው አስመስሎ ሁላችንንም ነው እየተናገረ ያለው፣” አይነት አንድን በአንድ አባዝቶ ውጤቱን “አንድ ሺህ” የማለት አተረጓጎም ተለምዷል፡፡
ወዳጆቻችን እንዳጫወቱን፤ በቀደም የሆነ ሰርግ በትልቅ አዳራሽ ውስጥ ይካሄድ ነበር፡፡ ሙሽሮች
እንደተለመደው ከአንድ ሰዓት በላይ አርፍደው ይመጣሉ፡፡ ለካ ምድረ ሚዜና ምድረ አጃቢ በአረቄዋ ‘ጦሽ’ ብሎ ኖሮ፣ ምን ብለው እየዘፈኑ ቢገቡ ጥሩ ነው… “እየሰበረ፣ ሰጠው ለአሞራ!” እኔ የምለው ሰርግ ላይ እንዲህ አይነት ዘፈኖች እንደ ጎጂ ባህል አይነት መታየት ጀምረው አልነበር እንዴ! አሁን የምን መሬት ፈንቅሎ መውጣት ነው! ለማን ‘መልእክት ለማስተላለፍ’ ነው! (ቂ…ቂ…ቂ…) አሀ…ሰርጉን እንኳን ተዉልን እንጂ!
ኮሚክ እኮ ነው… ሠርግ ስነስርአቱ ላይ…አለ አይደል…
“ተዋጋ ወይ ሚዜው ተዋጋ ወይ
መች ተዋጋና ያስባል ገና”
ተብሎ ተዘፍኖ እንዴት ነው ትዳሩ ሰላማዊ የሚሆነው! “እኔም እኮ ያኔ ገና ዘመዶችህ ’ሚዜው ተዋጋ ወይ‘ እያሉ ሲዘፍኑ ነገር እንደሚመጣ ገብቶኝ ነበር፣” ትላለች፡፡ ልክ ነቻ! የምር ‘ጀግንነት’ ያን ያህል አላስችል ካላቸው፣ ለምን ፋሉጃ ምናምን ሄደው አይፎክሩም! ገና ለገና ሁሉም ‘ፎካሪ’ ሆኗል ተብሎ በእሷ ሰርግ ላይ ነው እንዴ ‘ጀግና’ መሆን!
እሱዬውም ቢሆን እኮ ብቅል ሳያስፈልገው ‘‘ሆድ ያባውን’ … ያወጣዋል፡፡ ያ ሞቅ ብሎት የነበረው ዘፋኝ…
“ስትሄድ ውላ፣ ስትመለስ ጊዜ
ተኛች በጊዜ፣”
ሲል የነበረው … ለእኔ መልእክት እያስተላለፈ መሆኑን አውቄው ነበር፡፡ እኔ የማላውቃቸው አክስቶች ከትዳር በኋላ የሚመጡት፣ ምነው በፊት አልነበሩ! ነው ወይስ እንደ ኮሌጅ ‘ሪአድሚሽን’ ጠይቀው ነው!” ሊል ይችላል፡፡ እናማ… ምን ለማለት ነው፣ ዘንድሮ ሰዋችን ሁሉ ሆድ ብሶት በሆነች ትንሽዬ ነገር ጠብ ውስጥ የሚገባበት ሆኗል፡፡
እግረ መንገድ ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ጓደኛውን…
“ስማ… ይሄን ጢምህን ትንሽ ብትቆርጠው ምን አለበት?” ይለዋል፡፡ ጓደኛ ሆዬም…
“አሁን የእኔ ምን ሆነና ነው!” ይላል፡፡ ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው…
“ሰው አገጭ ላይ የበቀለ ሳይሆን እኮ ልክ የችግኝ ጣቢያ ነው የሚመስለው፡፡”
አሁን ይሄ ትንኮሳ አይደል፡፡ አገጭን ከስንት ነገር ጋር ማመሳሰል እየተቻለ “ችግኝ ጣቢያ” ምናምን እየተባለ በተዘዋዋሪ “አፈር ትመስላለህ፣” ሲባል ትንኮሳ ያልሆነ ምን ሊሆን ነው!
ታዲያላችሁ…አንድ ፈላስፋ ነው መሰለኝ እንዲህ አለ አሉ… “ወንዶች ሴቶችን የሚያገቡት ከተጋባን በኋላ ጠባይዋ አይለወጥብኝም ብለው ነው፡፡ ሴቶች ወንዶችን የሚያገቡት ከተጋባን በኋላ ጠባዩን አስተካክዬ እለውጠዋለሁ ብለው ነው፡፡ ሁለቱም ግን በመጨረሻ ኩም ነው የሚሉት፡፡”
አሪፍ አይደል…ልክ ነዋ፣ “አንዴ ከተጋባን በኋላ እየጠጣ የሚያመሸውን ነገር ትቶ በጊዜ ይከተታል፣” ከተባለ በኋላ ጭራሽ እኩለ ሌሊት ላይ በሸክም መግባት የጀመረ መአት ነዋ!
“አንዴ እማወራ ስትሆን ይሄ ‘ጓደኛዬን ልጠይቅ ሆስፒታል ሄጄ፣ ሰልስት አምሽቼ’ የምትለውን ነገር ትታወቃለች ከተባለ በኋላ፣ ጭራሽ ጓደኛዬ ሆስፒታል የሚያስተዳድራት ስለሌለ እዛው ነው የማድረው፣” የምትል መአት አይደለች እንዴ!
እናማ…ሰርግ ላይ የምትዘፍኑ ሰዎች፣ ዘንድሮ አተረጓጎም ተለውጧልና ጥንቃቄ ይደረግማ!  ገና ለገና “ዜማው ደስ ይለኛል፣” በሚል…አለ አይደል… “የመቃብር እጮኛዬ…” እያላችሁ የሰርግ አዳራሹን፣ ለቅሶ ቤት እንዳታደርጉትማ!
ስሙኝማ...የዘፈን ነገር ሲነሳ አንድ ሁልጊዜ የምትገርመኝ ዘፈን አለች፡፡ ይቺ… “አንዳንድ ቀንማ፣ ይሻላል ውሽማ…” የምትል፡፡ ጥቅሻ የለ፣ ጉንተላ የለ፣ ምን የለ… በቃ ፊት ለፊት “ውሽማ ይሻላል፣” ተብሏል፡፡ እናላችሁ …ይህን ዘፈን ስሰማ ልቤ ጥፍት ነው የሚለው፡፡ ሰው…ባለትዳር ከሆነ ምን ዓይነት እርኩስ መንፈስ ቤቱ ቢገባ ነው፣ በአደባባይ ውሽማ ማወደስ የሚገባው፡፡ ባለትዳር ካልሆነ… “ዌል፣ ባለትዳር ካልሆነ ሁሉም ውሽማ ነው፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) እነ እንትና አይዟችሁማ…ሳተላይቷ ፔኒሲዮኖች ላይ ለማተኮር ገና ፕሮግራም አልተደረገችም፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…)
እናላችሁ…አለ አይደል… እዚህ ከተማ ውስጥ እንደ ለንደን፣ ስድስት ሺህና ሰባት ሺህ የመንገድ ላይ ካሜራዎች የተገጠሙ ለታ ምን የሚሆን ይመስለኛል መሰላችሁ…ባርኔጣ የሚያደርጉ ወንዶችና ነጠላ የሚያጣፉ ሴቶች ይበዛሉ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2246 times