Saturday, 28 December 2019 13:07

መገናኛ ብዙኃን አቋም አራማጅነታቸው እየበረታ መምጣቱ ተገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 “ለፖለቲካ ጐራዎች የመታገያ ሜዳ እየሆኑ መጥተዋል”

              የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ለተለያዩ የፖለቲካ ጐራዎች የመታገያ ሜዳ እየሆኑ መምጣታቸው የተገለፀ ሲሆን፤ አቋም አራማጅነታቸው እየበረታ ነው ተብሏል ሰሞኑን በቀረበ ጥናት፡፡
ለሚዲያዎች የተለያዩ ስልጠናዎችንና የህግ ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን በመስጠት የሚታወቀው ደበበ ኃ/ገብርኤል የህግ ቢሮ (DHLO) “የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ የተጀመረውን የዲሞክራሲ ሂደት በማጥበቅ በኩል ያላቸው ሚና” በሚል ባካሄደው ጥናት፤  የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ከገለልተኛነታቸው ይልቅ የፖለቲካ አቋም አራማጅነታቸው ማመዘኑን አረጋግጧል፡፡
ጥናቱን ያቀረቡት የሃዋሣ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚሁ የትምህርት መስክ የፒኤችዲ ተማሪ የሆኑት አቶ ፍሬዘር እጅጉ፤ ጥናቱ በዋናነት ተጽእኖ ፈጣሪ የብሮድካስትና የህትመት መገናኛ ብዙሃንን ማዕከል አድርጐ መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡
የሚዲያ ተቋማቱ “በሀገሪቱ የተፈጠሩ ስድስት የግጭት አጋጣሚዎችን እንዴት ነበር የዘገቡት በሚል በ88 የዜና ውጤቶች ላይ መሠረት አድርጐ ጥናቱ መካሄዱ ታውቋል፡፡
በጥናቱ ከተካተቱት የግል ሚዲያዎች 50 በመቶ ያህሉ የግል ትምህርት ክፍል የግጭቶቹ መንስኤ የፖለቲካ ተቋማት ችግር ነው ያሉ ሲሆን፤ 40 በመቶዎቹ ደግሞ በሀገሪቱ የህግ ማስከበር ችግር በመኖሩ የተፈጠረ ነው የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አጥኚዎቹ ጠቁመዋል፡፡
የህዝብ (መንግስት) መገናኛ ብዙሃን ደግሞ የግጭቶቹ መንስኤ 20 በመቶ ብቻ መሆኑን እና የህግ ክፍተት ደግሞ 25 ሰመቶ ብቻ ድርሻ እንዳለው ማመላከታቸውን በጥናቱ ተለይቷል - ብለዋል አጥኚው፡፡
ለግጭቶቹ መፍትሔ ተብለው በመገናኛ ብዙሃኑ የተቀመጡ ሃሳቦች መካከል ደግሞ 54 በመቶ የሚሆኑት “ተቋማዊ መፍትሔ” ያስፈልገዋል ሲሉ፤ “ለግጭቶቹ መንስኤ የሌላ ግጭት መፍትሔ ነው” ብለዋል፡፡ አባባሽ ዘገባን እንደ ሌሎች ሀገራት ሚዲያዎች የዘገቡ ግን እንደሌሉ ጥናቱ አረጋግጧል፡፡
መገናኛ ብዙኃኑ ከለውጡ ሂደት በኋላ አንፃራዊ ነፃነት እየተሰማቸው ቢሆንም፤ በተለይ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘንድ አሁንም አነስተኛ ተቋማዊ ነፃነት እንዳለ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡  
እንደውም በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ አገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የአቋም አራማጅነት ጋዜጠኝነት የሚተገበርባቸው እየሆኑ መምጣታቸውንና በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችም የመታገያ ሜዳ መሆናቸው በጥናቱ ተመልክቷል፡፡
በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ ዘገባዎችም በአመዛኙ ፖለቲካዊነታቸው (ለፖለቲካ ትርጉም የተጋለጡ) እንደሚያመዝን የጠቆመው ጥናቱ፤ ጋዜጠኞች ራስን ሳንሱር በማድረግ ፈተና ውስጥ መውደቃቸው አመልክቷል፡፡
መገናኛ ብዙሃኑ በአመዛኙ ክፍፍልን በሚያመጡ ትርክቶችና የትናንት ታሪኮች ላይ ማተኮርና ሚዛናዊነት ማጣት እንደታየባቸውም አጥኚዎቹ ይፋ አድርገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለአገሪቱ አስፈላጊ በሆነው ብሄራዊ መግባባትና አንድነት ላይ በመገናኛ ብዙኃን የተሰሩት ዘገባዎች ከ10 በመቶ በታች መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በመረጃ እጦትና እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውን የጠቀሰው ጥናቱ፤ የመረጃ እጦቱም ስህተቶችና ያልተጣሩ ዘገባዎች እንዲበራከቱ ማድረጉን አመልክቷል፡፡
የጥናት ግኝቱን መነሻ በማድረግም የጥናቱ አቅራቢ መገናኛ ብዙኃኑ በአገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሂደት እንደያግዙ ለማስቻል ሊፈጽማቸው ያላቸውን ምክረ ሀሳቦች አቅርበዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል መገናኛ ብዙሃን ከአቋም አራማጅነት ተላቀው ከሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች በእኩል ርቀት ላይ ቆመው ቢገኙ የሚለው ምክረ ሃሳብ ተጠቃሽ ነው፡፡
በተለየ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ከማንኛውም የፖለቲካ ቡድን በእኩል ርቀት ላይ መቆም እንዳለባቸው የሚመክረው ጥናቱ፤ ለዚህም የባለሙያዎቻቸውን ክህሎት ማበልፀግና ተቋማዊ ነፃነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ጠቁሟል፡፡
ከሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች በእኩል ርቀት ቆመው ለመስራት የሚሞክሩ የግል መገናኛ ብዙኃን የፋይናንስ ማበረታቻዎች ቢደረግላቸው መልካም ነው የሚል ሃሳብም አጥኚው አቅርበዋል፡፡
መገናና ብዙሃኑ ለአገሪቱ ዴሞክራሲ አጋዥ የሆኑ ክርክሮችንና ውይይቶችን በማሰናዳት ላይ ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡  

Read 1913 times