Saturday, 28 December 2019 13:19

ብሔራዊ ደህንነት የራሱን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ከፈተ የቀድሞ ደህንነት መስሪያ ቤት ይጠቀምባቸው የነበሩ ንብረቶች የደረሱበት አይታወቅም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

      “የቀድሞ ደህንነት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣን ይጋፉ ነበር”

              “የፀጥታ ተቋማት በፖለቲካ ሽግግር ውስጥ” በሚል ርዕስ፤ በስትራቴጂያዊ ጥናት ተቋም አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በተካሄደው ሴሚናር ላይ ከለውጡ በኋላ ሁሉም የፀጥታ ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆነው እንዲሠሩ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን፤ ብሔራዊ ደህንነትም የራሱን የደህንነት ማሠልጠኛ ኮሌጅ መክፈቱ ተነግሯል፡፡
የሀገሪቱ የፀጥታ ተቋማት ከሪፎርሙ በፊትና በኋላ ያላቸውን ጥንካሬና አሠራር በገመገመው በዚህ ሴሚናር ላይ፤ ምሁራን፣ የመንግስት አማካሪዎችና ወታደራዊ አመራሮች ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጐበዛይ፤ ከሪፎርሙ በኋላ በፀጥታ ተቋማት ላይ የተደረጉ ለውጦችን በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን፤ ስለ ብሔራዊ ደህንነት ያለንን የአመለካከትና የአስተሳሰብ መዛባት በማረቅ ላይ ያተኮረ ለውጥ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በቀድሞ የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፈፀሙ እንደነበር፣ ከህግና መመሪያ ውጪ በርካታ ተግባራት ይከናወኑ እንደነበር እንዲሁም ዝቅተኛ ሙያዊ ብቃት እንደነበርና በዋናነትም መንግስትን ከህዝብ የመጠበቅ ተልዕኮን አንግበው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ሠነዶችም ሠራዊቱን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጠባቂ አድርጐ የሚያስቀምጡ ነበሩ ብለዋል - ሚኒስትር ዴኤታው፡፡
እነዚህን ግምገማዎች መነሻ ባደረገው የሪፎርም ሂደትም፤ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ መሠራቱን በዚህም መንግስት ዜጐችን ሊያጠቃ ይችላል ከሚል መነሻ ዜጐችን ከመንግስት ጭቆና ማዳንን የአስተሳሰቡ ማዕከል ያደረገ የደህንነት ተቋም ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊቱም ሀገርን ከውጭ ጠላት መከላከል ብቻ ሳይሆን ዜጐችን ከመንግስት ጭቆና የመታደግ ኃላፊነት እንዳለበት ግንዛቤ መያዙንም አማካሪው ገልፀዋል፡፡
ከዚሁ ጐን ለጐን የተቋማት አደረጃጀትና አወቃቀር የሰው ሃይል ሪፎርሞችና የደህንነት ባለሙያዎችን የሙያ ብቃት የማሻሻል ተግባራት መከናወናቸውን የጠቆሙት አማካሪው፤ በቀጣይም በደህንነት ሙያ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ የሚያሰለጥን የደህንነት ኮሌጅ መቋቋሙን አማካሪው ተናግረዋል፡፡
የግጭትና የደህንነት ስጋቶችን ቀድሞ ለመለየት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት አማካሪው፤ የአደጋ ጊዜን ማስተዳደር የሚቻልበት ማዕቀፍም እየተዘጋጀ መሆኑንን አስታውቀዋል፡፡
የቀድሞ የጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሣይ፤ በፖለቲካ ሽግግር ወቅት የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት ሊኖራቸው ስለሚገባው ሚናና አሠራር አለማቀፍ ተሞክሮዎችን መነሻ በማድረግ አብራርተዋል፡፡
በፓርላማው ለ10 አመታት የውጭ ግንኙነቶችና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን ሲመሩ መቆየታቸውን የገለፁት አቶ ተስፋዬ ዳቦ በበኩላቸው፤ የብሔራዊ ደህንነት ተቋሙ ላለፉት አመታት ለህግ ተገዢ እንዳልነበርና ከሁሉም የመንግስት አካላት በላይ አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
የብሔራዊ ደህንነት ተቋሙ በህገመንግስትና በህግ ከተሰጠው ስልጣን ውጩ የፓርቲ አባላት በሆኑ ፖለቲከኞች የሚመራ ከመሆኑም ባሻገር ዜጐች ከሀገር እንዳይወጡ እንዲሁም ወደ ሀገር እንዳይገቡ ይከላከልና ፤ ከፓርላማውም ሆነ ከስራ አስፈፃሚው እውቅና ውጪ የሆኑ ምርመራዎችን ያደርግ እንደነበር፣ አልፎ ተርፎም ድብቅ እስር ቤቶችም እንደነበሩት አስረድተዋል - አቶ ተስፋዬ፡፡
ተቋሙ የሚያንቀሳቅሰውን በጀት ለምን ተግባር ይጠቀምበት እንደነበር ካለመታወቁም በላይ እስካሁን ድረስ በመንግስት ውጪ የተገዙ የደህንነት ተሽከርካሪዎችና መኖሪያ ቤቶች በግለሰቦች እጅ እንደሚገኙ እንዲሁም ንብረቶቹ በትክክል እንደማይታወቁም አስረድተዋል - አቶ ተስፋዬ፡፡
ባለፉት 10 አመታት ፓርላማው በሀገሪቱ ምን የደህንነት ስራ እየተሠራ እንዳለ ያውቅ እንዳልነበር ያስረዱት አቶ ተስፋዬ፤ የተቋሙ ዳይሬክተርም በህጉ መሠረት በፓርላማው ሪፖርት ማቅረብ ሲገባቸው፤ አንድም ቀን በአካል ቀርበው ሪፖርት አቅርበው እንደማያውቁና ፓርላማውም በመልክ እንደማያውቃቸው አስረድተዋል፡፡
የደህንነት ተቋሙ በፓርላማውም ሆነ በስራ አስፈፃሚው ውስጥ በነበሩት ረጃጅም እጆች፣ የመንግስትን ስልጣን እንዳሻው ይወስን እንደነበርም ያስታወሱት አቶ ተስፋዬ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የራሱን ሚኒስትሮች የማቋቋም ስልጣን በመጋፋት ጭምር ለሚሾሙት እያንዳንዱ ሚኒስትር እውቅና ሰጪና ነሺ ሆኖ እንደነበርም አስረድተዋል፡፡
ተቋሙ በቋሚ ኮሚቴው የሚሰጡ ግብረ መልሶችንም ተቀብሎ ጉድለትን ከማስተካከል ይልቅ “እንዴት እንዲህ ትላላችሁ” በሚል በስልክ ማስፈራራት ይፈፀም እንደነበርም አቶ ተስፋዬ፤ አብራርተዋል፡፡


Read 12631 times