Saturday, 23 June 2012 08:30

“የአቡጊዳ ስሌትና የዘመን አቆጣጠር ማሻሻያ” ዛሬ ይመረቃል

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

“የአመፃ ብድራት” ነገ ይመረቃል                  “የጊዜ ጨረታ” ተመረቀ

ስንታየሁ ታደሰ ወልደኪሮስ ያዘጋጁት “የአቡጊዳ ስሌትና የዘመን አቆጣጠር ማሻሻያ” የተሰኘ መፅሐፍ ዛሬ ይመረቃል፡፡ በሐገር ፍቅር ትያትር ቤት ትንሿ አዳራሽ የሚመረቀው መፅሐፍ፤ የአቡጊዳ ፊደል የሙዚቃ ኖታ ባህርይ እንዳለው የሚያሳይ ሲሆን የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠርም ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረው ይጠይቃል፡፡ የመፅሐፉ ዋጋ 50 ብር ነው፡፡

በአቶ ጌቱ ሶሬሳ የተፃፈው “የአመፃ ብድራት” የተሰኘ ረዥም ልቦለድ መፅሐፍ ነገ ከጧቱ 2፡30 ሐረር ከተማ በሚገኘው ራስ ሆቴል ይመረቃል፡፡ ባለ 274 ገፆች ያሉትን መፅሐፍ ለመፃፍ አምስት ዓመት እንደፈጀባቸው ደራሲው ገልፀዋል፡፡በዕለቱ የአክሱም ዩኒቨርስቲ መምህርና የሥነፅሁፍና ፎክሎር የዶክትሬት ተማሪ የሆኑት ገዛኸኝ ፀ. (ፀጋው) ሙያዊ አስተያየት የሚሰጡ ሲሆን መምህሩ በመፅሃፉ የጀርባ ሽፋን ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “በዚህ መፅሃፍ፣ ህይወት በአማራጮች የተከበበች አትመስልም፤ አንድ ቀጥተኛ መንገድ የመረጠች አይነት ናት!... እናም በአሁኑ ጊዜ በእኛ አገር ላይ የተሻለ ለመኖር ያለው የሕይወት አማራጭ አንድ ብቻ ይመስላል - ሕገወጥነት…” ብለዋል፡፡ በምርቃቱ ላይ ከአቶ ገዛኸኝ በተጨማሪ ገጣሚና ጋዜጠኛ አበባው መላኩም ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሌላም በኩል በብሩክታይት ፀጋው የተዘጋጁ 53 ግጥሞች የተካተቱበት “የጊዜ ጨረታ” የግጥም መፅሐፍ ትናንት ተመረቀ፡፡ አውቶብስ ተራ በሚገኘው አዲስ ከተማ መሰናዶ ትምህርት ቤት አዳራሽ መፅሐፉ ሲመረቅ በባለሙያዎች ውይይት ተደርጓል፡፡ ከቀኑ 9 ሰዓት በተጀመረው ውይይትና ምረቃ በጀርመን የባህል ተቋም ባለሙያዎች አስተናባሪነት የንባብ ባህል እና ልምድ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ “የጊዜ ጨረታ” ለሀገር ውስጥ በ15 ብር፤ ለውጭ ሀገራት ደግሞ በ10 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

 

 

 

Read 929 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 08:32