Tuesday, 24 December 2019 00:00

የቀድሞውን የፓኪስታን መሪ የሞት ፍርድ የአገሪቱ መንግስት ተቃወመው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የፓኪስታን መንግስት በቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና የጦር መሪ ጄኔራል ፔርቬዝ ሙሻራፍ ላይ ባለፈው ማክሰኞ የተላለፈውን የሞት ፍርድ ቅጣት እንደሚቃወምና ውሳኔውን ለማስቀየር እንደሚሰራ ማስታወቁን ዴይሊ መይል ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ልዩ ፍርድ ቤት በስልጣን ዘመናቸው ባልተገባ ሁኔታ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ አገሪቱን ወደ ቀውስ አስገብተዋታል ተብለው በተከሰሱት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔርቬዝ ሙሻራፍ ላይ በሌሉበት የሞት ፍርድ መወሰኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት ግን ተከሳሹ ምላሻቸውን ባልሰጡበትና በከፍተኛ ህመም እየተሰቃዩ ባሉበት ሁኔታ በጥድፊያ የተላለፈው ፍርድ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ይግባኝ ለመጠየቅና ውሳኔውን ለማስቀየር መዘጋጀቱን እንዳስታወቀ አመልክቷል፡፡
በ2008 አገራቸውን ጥለው ወደ ዱባይ የተሰደዱትና በአሁኑ ወቅት በዱባይ በሚገኝ ሆስፒታል የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙት የ76 አመቱ ሙሻራፍ፤ በ2007 ባልተገባ ሁኔታ ጥለውታል በተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተባበሯቸው ባለስልጣናትና አጋሮች በክሱ አለመካተታቸውን እንደ አንድ መቃወሚያ የጠቀሱት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ “በዱባይ ህክምና የሚያደርጉላቸው ሃኪሞችም ሙሻራፍ ፍርድ ቤት መቅረብ እንደማይችሉ ባረጋገጡበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማስተላለፉ አግባብነት የለውም” ሲሉ መቃወማቸውንም ዘገባው አስረድቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1999 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን በመያዝ አገሪቱን ከ2001 እስከ 2008 በፕሬዚዳንትነት የመሩት ጄኔራል ፔርቬዝ ሙሻራፍ የሞት ፍርዱ ቢተላለፍባቸውም፣ ዱባይና ፓኪስታን ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ስለሌላቸው ዱባይ አሳልፋ አትሰጣቸውም ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው ገልጧል፡፡ ሙሻራፍ፤ወደ አገራቸው ተመልሰው በፍርድ ቤት ለመቅረብ ፈቃደኛ ቢሆኑም ሃኪሞቻቸው እንዳልፈቀዱላቸው ነግረውኛል ሲሉ የተናገሩት የሙሻራፍ ጠበቃ አክታር ሻፍ በበኩላቸው፣ ደምበኛቸው በዱባይ ከሚገኙበት ሆስፒታል በቪዲዮ መልዕክት ለፍርድ ቤቱ ምላሻቸውን እንዲሰጡ ቢጠይቁም፤ ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀበላቸውና በዚህ ሁኔታ የሞት ፍርዱ መተላለፉ አግባብ አለመሆኑን እንደገለጸ ዘገባው አመልክቷል፡፡ ሙሻራፍ ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤናዚር ቡቶ በተገደሉበት ሴራ ውስጥ እጃቸው አለበት በሚል ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1355 times