Saturday, 21 December 2019 13:09

‹‹አማራ በአማራነቱ እንዲኮራ›› እታገላለሁ? (ህዳር 16 ቀን 1993 ዓ.ም)

Written by  ሳምሶን
Rate this item
(2 votes)


                የማይጠየቅ ጥያቄ እያነሳሁ ከሆነ እንጃ:: ብቻ ባስበው ባስበው፣ ትርጉም ላገኝለት ስላልቻልኩና ስላልገባኝ፣ በቅንነት መልስ የሚሰጠኝ ሰው ይኖር እንደሆነ ተስፋ በማድረግ ጽፌዋለሁ፡፡ ከሳምንት በፊት በ2ኛው የብአዴን ምስረታ በዓል ዋዜማ ላይ፣ ከድርጅቱ የተሰጠ መግለጫ ሰማሁ፡፡ ‹‹ትምክህተኝነትን›› ታግያለሁ ይላል፡፡ እሺ - ‹‹እኔ ነኝ›› ማለት ከሆነ ትምክህተኝነትን ቢዋጋው መልካም ነው፡፡ ዘር በኑሮአችን ውስጥ ቦታ ሊሰጠው አይገባም፡፡ አብዛኛው ሰው በዚህ አስተሳሰብ የሚስማማ ይመስለኛል፡፡
ቀኑንና ፀሐፊውን ባላስታውሰውም፣ በእናንተው ጋዜጣ ያነበብኳት አንዲት ነገር ትዝ ትለናለች፡፡ ድንችና ሽንኩርት ስንገዛ የሻጩን ዘር እያየን በመጥቀስ፣ በእለት ተዕለት ኑሯችን የዘርን ጉዳይ ከቁም ነገር እንደማንቆጥር የምትገልጽ ጽሑፍ ነበረች፡፡ እውነት ነው፡፡ ታክሲ የምንሳፈረው፣ ልብስ የምንገዛው፣ ብቻ ምን አለፋችሁ --- በሕይወት እንቅስቃሴአችን ዘርን አንመርጥም፡፡ ከአንዳንዶቹ በስተቀር ጓደኛ የምንመርጠውና፣ ፍቅር የሚይዘንም በዘር አይደለም፡፡ በዚህ በዚህ የዘር ነገር በግልጽ የሚያነሳም ሰው የለም፤ ካነሳ ግን በጣም አሳፋሪ አድርገን ነው የምንወስደው፡፡
ታዲያ ይህች ጽሑፍ ደስ ያለችኝ፣ እለት ተእለት ሕይወታችን እንዲህ ሆኖ ሳለ፣ ወደ ፖለቲካ ስንሄድ በዘር ላይ የተመሰረተ አቋም መያዝ፣ ለምን አሳፋሪ እንደሚሆን በማውሳቷ ነው፡፡ አዘውትሬ ስለማልጽፍ፣ የጀመርኩትን ትቼ ወደ ሌላ ነገር ከገባሁ ይቅርታ አድርጉልኝ:: የችሎታ ነገር ነው፡፡ ጥያቄዬን ግን አቃልላችሁ አትዩብኝ፡፡ ፈጽሞ የማይገባኝና በጣም የሚያስጨንቀኝ ጉዳይ ነው፡፡ በሬዲዮ ‹‹ትምክህተኝነትን ታግያለሁ፣ ተዋግቻለሁ›› ሲል የሰማሁት ድርጅት፤ ‹‹አማራ በአማራነቱ እንዲኮራና ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲሰርጽ›› እየታገለ መሆኑን ተናግሯል:: ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ብሔር ብሔረሰቦች  ማንነታቸው ተረጋግጦና ተከብሮ…›› ነው:: አንድ ሰው በፀባዩና ተግባሩ ታይቶ መከበር ያለበት ሲባል፣ ይገባኛል፡፡ አንድ ሰው “በፀባዬና በስራዬ እኮራለሁ” ሲለኝ ምን እያለ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ከተጠራጠርኩም ምን ሰራ? ጸባዩስ ምን ይመስላል? ብዬ አይና  የሚያኮራ እንደሆነ አረጋግጣለሁ፡፡ አንድ ሰው ‹‹በአማራነቴ እኮራለሁ›› ሲለኝ ግን ምን እያለ እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ለምሳሌ ፤‹‹እኔ የጉራጌና ኦሮሞ ወላጆች ስላሉኝ እኮራለሁ›› ብል ምን ትርጉም ይሰጣችኋል? ወይም የስራ ባልደረባዬ፤ በስራው ጥራትና ቅልጥፍና መኩራቱን ትቶ ‹‹በወላጆቼ እኮራለሁ›› የሚለኝ ከሆነ ምን እመልስለታለሁ? ምን ማለቱ ነው? ቤት ያከራዩኝ ሴትዮ ‹‹በሃድያነቴ እኮራለሁ››፣ ጎረቤቴም ‹‹በሶማሌነቴ እኮራለሁ››፣ ፍቅረኛዬም ‹‹በኦሮሞነቴ እኮራለሁ››፣ ጓደኛዬም ‹‹በትግራይነቴ እኮራለሁ›› ማለት ቢጀምሩ ብዬ ሳስበው የማብድ ይመስለኛል፡፡
‹‹በአማራነቴ እኮራለሁ›› የሚለኝ ሰውዬ፤ አማራ ባይሆን ኖሮስ? ምን ሊል ነው? ምርጫና የግል ጥረት በሌለበት ጉዳይ እንዴት መኩራት ይቻላል? መቼስ በግል ደረጃ ‹‹እኔኮ የእንትን ዘር ነኝ›› ብሎ ለመኩራት የሚፈልግ ቢኖር፣ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ልንስቅበት፣ ልንንቀው ወይም አሹፈንበት እናልፍ ይሆናል፡፡ የእንትን ዘር ተወላጅ ሆነና ምን? ዝም ብሎ ነው፡፡ ‹‹እኔማ የእንትን ዘር ነኝ›› ብሎ የበታችነት የሚሰማው ካለም፣ እሱንም እንዲሁ፡፡ እንዴት በዘር ለመኩራትና ለማፈር ይቻላል? ግን ያጋጥማል:: ሞኝነት መሆኑን አውቀን እንለፈው እንበል፡፡ ግን፣ አንድ ትልቅና የተከበረ የፖለቲካ ድርጅት፣ “በአማራነትህ እንድትኮራ፣ በትግሬነትህ እንድትኮራ፣ በጋሞነትህ እንድትኮራ፣” ብሔር ብሔረሰብ የተባሉትን በሙሉ በዝርዝር እየጠራ፣ “በማንነታችሁ እንድትኮሩ እታገላለሁ” ሲል ግን በጣም ግራ ግብት ይለኛል፡፡
“አማራ በመሆኔ ወይም ኦሮሞ በመሆኔ አሊያም ጉሙዝ በመሆኔ ምንም የሚያኮራ ነገር አይታየኝም” ብልስ? ደግሞም፣ ምንም የሚያኮራም የሚያሳፍርም ነገር የለውም፡፡ ከኦሮሞና ከጉራጌ የተወለድኩትስ? አንድ ሰው “ኦሮሞ ነኝ” ብሎ ወይም “ትግሬ ነኝ ብሎ ኩራት በኩራት ሆኖ ከርሞ፣ በኋላ ጉራጌ ወይም አማራ መሆኑን ቢያውቅ፣ ሀፍረት ሊሰማው ነው ማለት ነው? ወይስ ደግሞ ‹‹በጉራጌነቴ እኮራለሁ…›› ማለት ሊጀምር ነው? ነገርዬው ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻልም፡፡  
‹‹በማንነታቸው ኮርተውና ተከብረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ›› የሚል አንቀጽ በሕገ መንግስቱ ቢኖርስ? እኔ ግን “ስራዬና ፀባዬ እንጂ የዚህ ወይም የዚያ ብሄር በመሆኔ የምኮራበትም፣ የማፍርበትም፣ የምዋረድበትም ምንም ምክንያት የለም” ብል፣ ሕገ ጥሰሃል ልባል ነው? ብአዴን ‹‹አማራ በአማራነቱ ኮርቶ እንዲኖር እታገላለሁ›› ሲል “አማራነት የሚያኮራም የሚያሳፍርም አይደለም፤  ትርጉምም የለውም” ብል ‹‹ፀረ አማራ›› ተብዬ ልወገዝ ነው? እንደኔ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው አማሮችስ ምን ሊባሉ ነው? ከሃዲ አማራ!?
ቆይቷል እንጂ ‹‹ጥሩ ትግሬ ሆኖ ጥሩ ኢትዮጵያዊ መሆን ይቻላል፤ ጥሩ አማራ ሆኖ ጥሩ ኢትዮጵያዊ መሆን ይቻላል፤ ጥሩ ከንባታ ሆኖ፣ ጥሩ ኦሮሞ…. ሆኖ ጥሩ ኢትዮጵያዊ መሆን ይቻላል›› ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ በብአዴን መግለጫ ላይም ሰምቸዋለሁ፡፡
ጥሩ አማራ ምንድነው? ጥሩ ሐረሬ ምንድነው? ፈጽሞ አይገባኝም፡፡ በፀባይ ከሆነ በየብሔሩ የተለያየ ፀባይ አለ፡፡ አንዱ ብሔር ጥሩ ፀባይ ያለው አይሆንም፡፡ ‹‹እኔ የወለጋ ልጅ ነኝ›› ብሎ የሚኮራ፣ የእገሌ ዘር ነኝ ብሎ የሚመካ ትግሬ ይኖራል፡፡ ትህትና የበዛበት ሰውም እናገኛለን፡፡ ‹‹የሚመካ ቢኖር በእግዚአብሔር ይመካ›› ብሎ ከዘር ይልቅ እሱነቱን የሚከተል ደግሞ አለ፡፡
እንደዚሁ ‹‹ጥሩ ኢትዮጵያዊ›› ሲባልም ምን ለማለት ተፈልጎ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም:: ጥሩ ኢትዮጵያዊ ሲባል የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ የወጣን ሕግ የሚያከብር፣ ሕጉ መብትን የሚያስጠብቅ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ እንዲቀየር የሚጥር ከሆነ ትክክል ነው፡፡ ጥሩ ትግሬ፣ ጥሩ ኦሮሞ፣ ጥሩ አገው፣ ጥሩ ስልጤ ሲባል ግን ትርጉሙ አይገባኝም፡፡ ሊገባው የሚችል ሰው ያለ ስለማይመስለኝም፣ እንደዚያ ሲባል ስሰማ አገር ሁሉ ያበደ ይመስለኛል፡፡
ጥሩ ኦሮሞ የሚባለው ‹‹ለኦሮሞ ጥቅም›› የሚታገል ነው?‹‹አይ እኔ የኦሮሞ ጥቅም፣ የሲዳማ ጥቅም የሚባል ነገር አላውቅም፤ ሁሉም ሰው እንደ ስራውና እንደ ፀባዩ መመዘን አለበት›› የሚል ኦሮሞስ? ‹‹አንድ አገር ውስጥ እስከኖርን ድረስ ሁሉም እኩል መብት አለው፤ በኦሮሞነቴ የማገኘው ወይም የማጣው ነገር መኖር የለበትም›› የሚለውስ? እና ጥሩ ኦሮሞነት ምንድን ነው?  ጥሩ ትግሬነት? ጥሩ አማራነትስ?
ወይስ፣ ጥሩ አማራ ማለት፣ በአማራነቱ የሚኮራ ማለት ይሆን? ‹‹ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› ሲሉ ምን ማለት እንደሆነ ባይገባኝም፣ (ትርጉሙን በቀጥታ ሲገልፁ ሰምቼም አይቼም ስለማላውቅ) ዳር ዳሩን እየነካኩ ከሚናገሩት ግን፣ በራሱ ብሔር የሚኮራና ሌሎችም በራሳቸው ብሔር እንዲኮሩ (የሚፈልግ) እንደሆነ እገምታለሁ:: ከዚህ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? የራሱንም ብሔር የሚያከብር፣ የሌሎችንም የሚያከብር ይጨመርበት፡፡
በዚህ ትርጉም ከሄድን ጥሩ አማራና ጥሩ ኢትዮጵያዊ ማለት፣ በአማራነቱ የሚኮራና ሌሎችም በራሳቸው ብሔር እንዲኮሩ የሚፈልግ መሆኑ ነው፡፡ ግን ‹‹አማራነቴ አያኮራኝም፣ አያሳፍረኝም፣ ትርጉምም የለውም፡፡ ዋናው ስራዬ፣ ፀባዬና አስተሳሰቤ ነው›› የሚል አማራስ? “በዚህች አገር የሚኖር ሰውን ሁሉ በሰው ልጅነቱ መብቱን አከብራለሁ፤ ሲጣስም እንዲከበር የተቻለኝን እጥራለሁ፤ በተረፈ እያንዳንዱን ሰው ብሔር አለው በሚል ሳይሆን እንደ ሥራውና እንደ ፀባዩ አከብረዋለሁ ወይም እንቀዋለሁ” የሚል ከሆነስ ጥሩ ኢትዮጵያዊ አይደለም? አማራና ትግሬ ወላጆች ያሉትስ? ኦሮሞና ጉራጌ ወላጆች ያሉትስ? ወዘተ…
ብአዴን፣ “አማራነትን (ጥሩ አማራነትን ዲሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት) ለማስረጽ እታገላለሁ” ሲል፣ የማይገባኝ መሆኑን የአቅሜን ያህል የተገናገርኩ ይመስለኛል፡፡ አባቱ የአማራና የኦሮሞ ተወላጅ፣ እናቱ የትግሬና የአገው ተወላጅ የሆኑ የደሴ ከተማ ነዋሪ (አማርኛ ብቻ ተናጋሪ)፤ በዚህ የማይሳተፍ ከሆነስ፣ ትግሉ ይህን ሰውዬ እንዴት ይመለከተዋል?
‹‹ምን ችግር አለው? ሰውዬው ጥሩ አማራ፣ ጥሩ ኦሮሞ፣ ጥሩ ትግሬ፣ ጥሩ አገው መሆን ይችላል፡፡ ቀጥሎም ጥሩ ኢትዮጵያዊ›› የሚል መልስ እንደማይሰጠኝ እገምታለሁ፡፡ እንዴት ብሎ እነዚህን ሁሉ ይሆናል? መቼም ጥሩ አማራ፣ ጥሩ ኦሮሞ፣ ጥሩ… እየተባለ የሚዘረዘረው ልዩነት ቢኖረው ነው፡፡ ምንም ልዩነት ከሌለው ‹‹ጥሩ… ጥሩ›› አንልም ነበር:: እና ሰውዬው ምን ሊሆን ነው? ከአራቱ አንዱን ሊመርጥ ይችላል? ወይስ ሁሉንም ያጣ ይሆናል? አደጋ አልሸተታችሁም? ጥሩ አማራ- የጠራ አማራ፣ ጥሩ ትግሬ- የጠራ ትግሬ፣ ጥሩ ኦሮሞ - የጠራ ኦሮሞ… የሚል አስፈሪ፣ ዘግናኝ፣ አስቀያሚ መልዕክት ሽው አላላችሁም? አስፈሪ አደጋ የምዋጋው ነው እንደሚል፡፡ ባምናችሁ ደስ ባለኝ፡፡ እሺ ልመናችሁ፡፡ እነሱ፣ እንዲህ አይነት አደገኛ አዝማሚያ የላቸውም ብዬ ልመን፡፡ ግን “ጥሩ አማራን ለመፍጠር፣ አማራ በአማራነቱ እንዲኮራ እታገላለሁ” ማለት ምን ማለት ነው? እባካችሁ መልስ አለን የምትሉ፣ ካላችሁ ከጭንቀት ገላግሉኝ፡፡       

Read 3759 times