Saturday, 21 December 2019 12:58

‹‹የቃል ኪዳን ወላጆች›› - ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

        - ተማሪዎችንም ሆነ ማህበረሰቡን ያነቃቃ ፕሮጀክት ነው
            - ‹‹ሁለት ተማሪዎችን በቃል ኪዳን ወላጅነት ተረክቤአለሁ››

        ጎንደር ዩኒቨርሲቲ “የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት” የሚል አዲስ አሰራር መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮው ዓመት ከተቀበላቸው 5 ሺህ ገደማ አዳዲስ ተማሪዎች መካከል 99 በመቶው፣ ከሌሎች የአገራችን ክፍሎች የመጡ መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን ይናገራሉ፡፡ የፕሮጀክቱ ዓላማ ከሌሎች አካባቢዎች ለመጡ ተማሪዎች ‹‹የቃል ኪዳን ቤተሰብ›› በማገናኘት፣ ተማሪዎቹ ከአዳዲስ ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው በጥሩ መንፈስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) ጋር ተከታዩን ቃለ
ምልልስ አድርጋለች፡፡

                “የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት” ሀሳብ እንዴትና በማን ተወጠነ?
ይህ ፕሮጀክት በቅርቡ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው በተሾሙት፣ ኢ/ር ማስተዋል ስዩም፣ ከአንድ አመት በፊት የመነጨ ሀሳብ ነው፡፡ ይህን ሀሳብ እንድንተገብረው የነገሩን ከአንድ ዓመት በፊት ቢሆንም፣ በተለያዩ ጉዳዮችና በአገሪቱም ወቅታዊ ሁኔታ ሳንተገብረው ቆይተን ነበር:: ከወራት በፊት ግን ከከተማው ማህበረሰብ በኩል አንድ ኮሚቴ፣ ከዩነቪርሲቲው ማህበረሰብ በኩል ደግሞ አንድ ኮሚቴ በማዋቀር የከተማው ኮሚቴ ሀላፊነት የሚሰማቸው የቃል ኪዳን ወላጆችን የመለየት ሥራ፣ የዩኒቨርስቲው ኮሚቴ ደግሞ ፈቃደኛ የሆኑና ዓላማውን የሚደግፉ ተማሪዎችን የመለየት ሥራ ስንሰራ ቆየን፡፡
ከማህበረሰቡና ከተማሪው በኩል የታየው ምላሽ ምን ይመስላል?
እውነት ለመናገር፤ እጅግ የሚያስደስት ምላሽ ነው ያገኘነው። አየሽ፣ አሁን ያለውን ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ ስትመለከቺው አስቸጋሪ በመሆኑ በተለይ በየዩኒቨርሲቲው በርካታ ስጋቶች አሉ። ይህ አሰራር ግን ተማሪዎች ተረጋግተው፣ ከአዲሶቹ ቤተሰቦቻቸው ጋር እየተገናኙና እየተወያዩ፣ ትምህርታቸውን በውጤት እንዲያጠናቅቁ በእጅጉ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ እኛ ‹‹የቃል ኪዳን ወላጅ›› እንዲያገኙ ያደረግነው፣ ዘንድሮ የተቀበልናቸውን ፍሬሽ ተማሪዎች ነው፡። ዘንድሮ 5 ሺህ አዳዲስ ተማሪዎችን የተቀበልን ሲሆን 99 በመቶ ያህሉ፤ ከሌሎች የአገራችን አካባቢዎች የመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ለአካባቢው እንግዳ እንደመሆናቸውና አዳዲስ ወላጅ ማግኘታቸው፣ አካባቢውን… ባህሉን… አመጋገቡን… እንዲለምዱ ይረዳቸዋል። ‹‹የቃል ኪዳን ወላጆችም›› ከእነዚህ ልጆቻቸው አዳዲስ ባህሎችን ያውቃሉ፣ ይማራሉ፡፡ ይሄ ትልቅ አሰራር ነው:: በቀጣይም በየዓመቱ የሚመጡትን ከወላጆች ጋር እያገናኘን፣ መጨረሻ ላይ ሁሉም ተማሪ፣ የቃል ኪዳን ወላጅ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡
ከ5 ሺህ ተማሪዎች በህዳር 27ቱ ስነ ሥርዓት ‹‹የቃል ኪዳን ወላጅ›› ያገኙት 1 ሺህ 500 ያህሉ ናቸው፡፡ እነዚህ እንዴት ቀድመው አገኙ? የቀሪዎቹ 3 ሺህ 500 ተማሪዎችስ ጉዳይ እንዴት ይሆናል?
እኛ ያስቀደምነው፤ ከወላጆችም ከተማሪዎችም ፈቃደኞች የሆኑትን በመለየት ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልሽ፤ አብዛኛው ሕዝብም ተማሪዎችም ሀሳቡን በደስታ ተቀብለውታል፡። የዩኒቨርሲቲውን ማህብረሰብ፣ ተማሪዎችንም ሆነ የከተማውን ማህበረሰብ በእጅጉ ያስደሰተና ያነቃቃ ፕሮጀክት ነው:: ስለዚህ ቀድመው ‹‹የቃል ኪዳን ልጅ እንፈልጋለን ሀላፊነት እንወስዳለን›› ብለው የጠየቁና የቃል ኪዳን ወላጅ እንፈልጋለን ያሉ ተማሪዎች ናቸው በመጀመሪያው ትግበራ ይፋ የሆኑት፡፡ ከዚያ በኋላም ብዙ ወላጆችም ብዙ ተማሪዎችም ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ እኔም ‹‹ልጅ እፈልጋለሁ›› የሚሉ እየበዙ ነው፡፡ ‹‹ለእኔም ወላጅ ይፈለግልኝ›› የሚሉ ተማሪዎችም አሉ:: ቀጣይ ተግባራችን 3 ሺህ 500ዎቹን ከቃል ኪዳን ወላጆቻቸው ጋር ማገናኘት ነው፡፡ በዚህ ላይ ሁለቱም ኮሚቴ እየሰራበት ይገኛል። አጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው 25 ሺህ ያህል ተማሪዎች አሉን፡፡ ለአዲሶቹ ቅድሚያ የሰጠነው፣ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ከሌሎች አካባቢዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡ እንደመሆናቸው፣ እንግድነት እንዳይሰማቸው አካባቢውንና ባህሉን እንዲላመዱና፣ በራስ የመተማመን ስሜት እንዲፈጠርባቸው ለማድረግ ነው፡፡
በቃል ኪዳን ወላጆቹና በተማሪዎቹ መካከል የሚኖረው ግንኙነት ምን ይመስላል?
አሁን ትግበራው በተጀመረ ዕለት እንኳን፣ ወላጆቹ የተረከቧቸውን ልጆች ወደ ቤታቸው ወስደው፣ ከልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር ያስተዋወቁ አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ሁለት ተማሪዎችን በቃል ኪዳን ወላጅነት ተረክቤያለሁ፡፡ በዚያኑ ዕለት ወደ ቤቴ ወስጃቸው፣ ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር አስተዋውቄ “ቤቴ ይሄ ነው” ብዬ ወላጅነቴን ጀምሬያለሁ:: ልጆቼም ቤተሰቤም በዚህ ደስተኛ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ወላጆች “የተረከብኩት ልጄ ተምሮ እስኪመረቅ የምግብና ትራንስፖርቱን ወጪ እሸፍናለሁ” በማለት ቃል ገብተዋል፡፡ ይሄ ምን ማለት መሰለሽ… ለምሳሌ ተማሪው፤ ዩኒቨርስቲ ካፌ ውስጥ መመገቡን ያቆምና፣ የቃልኪዳን ወላጆቹ ቤት ይመገባል፡፡ ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም ባለው ትርፍ ጊዜ ሁሉ ከወላጆቹ ጋር ያሳልፋል፡፡  ክረምት ላይና ዓመቱ መሀል ላይ ትምህርት ሲዘጋ፣ ወደ ወላጆቹ የሚሄድበትንና የሚመለስበትን የትራንስፖርት ወጪ የቃልኪዳን ወላጅ ይሸፍናል ማለት ነው፡፡ ይሄ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ልክ እንደወለዷቸው ልጆች ልብስና ጫማ እየገዙ፣ አስፈላጊውን ነገር እያደረጉ፣ ፍቅር እየሰጧቸው አብረው ይቀጥላሉ፡፡ ይሄ ዝምድና ተማሪዎቹ ተመርቀው ሲሄዱ የሚቋረጥ አይሆንም፡፡ ቃልኪዳን በቃ - ቃል ኪዳን ነው:: ይጠያየቃሉ፡፡ ግንኙነቱ የወላጅና የልጅ ከመሆን ያልፍና ቤተሰብ ለቤተሰብ ይሆናል፡፡ የልጁ የቃል ኪዳን ወላጆችና እውነተኛ ወላጆች ዝምድና ይጀምራሉ፡፡
ይህ አገራዊ አንድነትን ያጠናክራል፤ የባህል ልውውጥን ይፈጥራል፡፡ ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን ያዳብራል፡፡ ከምንም በላይ ልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲያችን የላኩ ወላጆች ሥጋት ይቀንሳል፡፡ ለምሳሌ አንድ ነገር ልንገርሽ:: ይህንን ፕሮጀክት ይፋ ያደረግነው ባለፈው ህዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያ አንድ ልጅ የተረከበ ወላጅ፣ ሰሞኑን ደወለልኝና “እኔ የተረከብኩት ልጅ ሥጋት እንዳለበት ስለነገረኝ፤ ያለበት ስጋት ታይቶ፤ ከስጋት እንዲወጣ እፈልጋለሁ” አለኝ፡፡ እኔም የፀጥታ ሰራተኞች ልጁን እንዲያነጋግሩና ከስጋት እንዲያላቅቁት ጠቆምኳቸው፡፡ እነሱም ልጁን ጐብኝተው አረጋግተውታል፡፡ አየሽ ይሄ ልጅ ስጋቱን እንኳን ከእኛ ይልቅ ለወላጆቹ ነው የተነፈሰው፡፡
በዚህ “የጐንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት”፣ የተማሪዎቹ እውነተኛ ወላጆች ስሜት ምን እንደሚመስል ቢነግሩኝ?
እውነት ለመናገር የተሰማቸውን ደስታ በቃላት ለመግለጽ ያስቸግራል፡፡ ደስታቸውን ሲገልፁ፤ ሲመርቁ ነው የሰነበቱት፡፡ በጣም ደስተኞች ናቸው፡፡ በቃልኪዳን ወላጆች ላይ እምነት መጣላቸውንም ተናግረዋል፡፡ ይህ እጅግ የሚያስደስት፣ ይበልጥ ሃላፊነትና መነቃቃት እንዲሰማን የሚያደርግ ተግባር ነው፡፡ አየሽ ቅድም እንደገለጽኩልሽ፤ እነዚህ ልጆቻቸውን ከሩቅ አካባቢ የላኩ፣ እውነተኛ ወላጆች ከስጋት ያርፋሉ፡፡ ልጃቸውን የሚጠብቅ ሌላ ወላጅ አለ፡፡ ወላጅ ለወላጅ ትውውቅና ትስስር ለመፍጠር ደግሞ ከዚህ በላይ መንገድ የለም:: ተማሪዎቹም ከወላጅ ቤት ወጥተው፣ ወደ ሌላ ወላጅ ቤት ሲገቡ፣ በትምህርት ጥራታቸው ላይ የሚጨምረው ትልቅ እሴት አለ፡፡ ይሄ በቀላሉ የሚታይ አደለም፡፡ የጐንደር ከተማ ህዝብም፣ ቃልኪዳኑን ጠብቆ ልጆቹን ለውጤት እንደሚያበቃ ትልቅ እምነት አለኝ፡፡ እኔም የተረከብኳቸውን ልጆቼን፣ በጥሩ እንክብካቤና ፍቅር ለውጤት በማብቃት፣ ሃላፊነቴን እወጣለሁ፡፡
ከጐንደር ዩኒቨርሲቲ “የቤተሰብ ፕሮጀክት” ሌሎች የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ምን ተሞክሮ ይወስዳሉ?
ይሄ አይነት አሰራር በሌላው ዓለም በተለይም በአውሮፓ የቆየና የተለመደ አሰራር ነው፡፡ ምንም እንኳን በአገራችን የመጀመሪያ ቢሆንም፡፡ ሌላው ዩኒቨርሲቲ ምን ልምድና ተሞክሮ ይወስዳል ለተባለው፤ መልካም ተሞክሮ ሁሉ በሌላውም አካባቢ መለመድና መተግበር አለበት፡፡ ከጐንደር የሚሄደው ተማሪ ጅማ ወላጅ ካገኘ፣ የጂማው አፋር ወላጅ ካገኘ፣ የሶማሌው ሐዋሳ ወላጅ ካገኘ፣ የቤኒሻንጉሉ ሀረር ወላጅ ካገኘ፤ ሁሉም አካባቢ ቤተሰብነት አብሮነት፣ አገራዊ አንድነት ተፈጠረ ማለትኮ ነው፡፡ ከአንዱ አካባቢ የሄደው ተማሪ በሚሄድበት ቦታ ወላጅ ካገኘ፤ ከስጋት ነፃ ይሆናል፡፡ ወላጅም ሃላፊነት ወስዶ፣ የቃልኪዳን ልጁን ተረክቧልና፣ በንቃት ልጁን ይጠብቃል፤ ይመክራል፣ ያበረታታል፣ ችግር ሲገጥመው ችግሩን ይፈታል፡፡
ይሄ በአገር አቀፍ ደረጃ ቢተገበር የትኛውም ዩኒቨርሲቲ ላይ ችግር ያጋጥማል ብዬ አላስብም:: ስለዚህ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተግባራዊ ቢያደርጉት፣ ውጤታማ እንሆናለን የሚል እምነት አለኝ፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ወይም ባጋጣሚ ይህን ፕሮጀክት ተግባራዊ ባደረጋችሁ ማግስት፣ በዩኒቨርሲቲያችሁ አስደንጋጭ ክስተት ተፈጥሯል፡፡ አንድ ተማሪ ተገድሏል፡፡ እስቲ ስለተፈጠረው ነገር ይንገሩኝ?
እውነት ነው፡፡ ፕሮጀክቱን በተገበርን ማግስት፣ እሁድ ማለዳ ላይ አንድ ተማሪያችን መታጠቢያ ቤት ውስጥ ተጐድቶ ተገኘ፡፡ ወዲያው ወደ ህክምና ተወስዶ ሲረዳ አምሽቶ፣ ማታ 2፡00 አካባቢ ህይወቱ አለፈ፡፡ እጅግ በጣም ነው ያዘንነው፡፡ በተማሪውም በዩኒቨርሲቲውም ማህበረሰብ፤ ድንጋጤንና ሀዘንን ፈጥሯል፡፡ እጅግ በጣም ነው ያዘንነው፡፡ ተማሪው ማሾ ይባላል፡፡ ከአርሲ ነው የመጣው፡፡ በእንስሳት ህክምና ኮሌጅ ሥር የቬንትናሪ ሜዲሲን የሁለተኛ ዓመት ተማሪና የ25 ዓመት ወጣት ነው፡፡ አስከሬኑ በጳውሎስ ሆስፒታል ምርመራ ከተደረገለት በኋላ፣ ለቤተሰቦቹ እንዲደርስ አድርገናል፡፡ በዚህ ተማሪ ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ ሰባት ያህል ተማሪዎች፣ ልጁ በሞተ ዕለትና በነጋታውም ጭምር ተይዘው ታስረዋል:: ፍርድ ቤት ቀርበው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ተደርጐባቸዋል፡፡ ጉዳዩ በጥብቅ ተይዞ፣ በህግ ክትትል እየተደረገበትና በህግ የተያዘ በመሆኑ፣ ከዚህ በላይ መግለጽ ባልችልም፣ ህግ የደረሰበትን፣ የወንጀለኞቹን ማንነትና የሞቱን መንስኤ ወደፊት ግልጽ እናደርጋለን፡፡
የልጁን መገደል ተከትሎ በዩኒቨርሲቲው የተነሳ ግርግር… ረብሻ ነበር?
የተነሳ ረብሻና ግርግር ባይኖርም፣ በቤተሰብ ፕሮጀክት ትግበራው ደስታና መነቃቃት ላይ ሀዘንንና ድንጋጤን ፈጥሯል፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፤ ተማሪውም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም እጅግ አዝኗል፡፡ እኛ ግን የተማሪያችን ሀዘን ቢያንገበግበንም፣ የቤተሰብ ፕሮጀክቱን ትግበራ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ይህንን አጠናክረን በመቀጠል ነው ችግራችንን መቅረፍ የምንችለው ብለን እናምናለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- የተማሪውን ግድያ ተከትሎ ስጋት አለን የሚሉ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲውን ለቀው መውጣታቸው ተሰምቶ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ከእነዚህ ተማሪዎች አብዛኞቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሳቸውን የዩኒቨርስቲው ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሀላፊ ወ/ሮ ይዳኙ ማንደፍሮ ጠቁመው የቀሩትም እስከ ሰኞ እንዲመለሱ ቀነ ገደብ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡


Read 2246 times