Print this page
Saturday, 21 December 2019 12:56

ያለ ዕድሜ ጋብቻ - የኢትዮጵያውያን ታዳጊ ሴቶች ፈተና

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)


               - በኢትዮጵያ ከሦስት ሴቶች በአንዷ ላይ ጾታዊ ጥቃት ይፈጸማል
              - 70 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው 18 ዓመት ከመሆኑ በፊት ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል
              - በኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን ያህል ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው ተድረዋል
                    
              የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት በ2016 ዓ.ም ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ ከሶስት ሴቶች መካከል በአንዷ ላይ ጾታዊ ጥቃት ይፈጸምባታል፡፡ ጥናቱ እንደሚጠቁመው፤ 40.3 በመቶ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው ይዳራሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም 16 በመቶ የሚሆኑት የሚዳሩት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ሆኖ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ልጃገረዶች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው 18 ዓመት ከመሆኑ በፊት ቢያንስ አንድ ጊዜ ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል የሚለው ጥናቱ ከእነዚህ መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ተገደው ተደፍረዋል ብሏል፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን የማውገዝ ወይም የነጭ ሪባን ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ28ኛ ጊዜ፣ በአገራችን ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ ከህዳር 16 እስከ ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ፕሮግራሞች ተከብሯል፡፡ የዘንድሮው በዓል ያለ ዕድሜያቸው የሚዳሩ ታዳጊ ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከልና ይህንን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቀረት በሚያስችሉ በተለያዩ ፕሮግራሞች ሲከበር ሰንብቷል፡፡
‹‹ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ›› ከትግራይ ክልል ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ጋር በመተባበር፣ በትግራይ ክልል የሚያካሂደው የአስራ ስድስቱ ቀናት የፀረ ጾታ ጥቃት ወይም ያለ ዕድሜ ጋብቻን የማስወገድ ዘመቻ የነጭ ሪባን ቀን የንቅናቄ የመክፈቻ ፕሮግራም በመቀሌ ከተማ ያካሄደ ሲሆን በዚህ ፕሮግራም ላይ ያለ ዕድሜ ጋብቻ በክልሉ በሚገኙ ሴት ታዳጊ ሕጻናት ላይ እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች የሚያሳዩ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችና ፕሮግራሞች ቀርበው ነበር፡፡
ድርጅቱ በክልሉ ውስጥ የሚያካሂደውን ጸረ - ያለዕድሜ ጋብቻ ዘመቻ አስመልክቶ በመቀሌ ከተማ አዘጋጅቶት በነበረው ፕሮግራም ላይ የትግራይ ክልል ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር የትምወርቅ ገብረ መስቀል እንደተናገሩት፤ ክልሉ በሴት ታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች በተለይም ያለ ዕድሜ ጋብቻ በስፋት ከሚፈጸምባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንደኛው ነው፡፡
በክልሉ ከፍ ያሉ ቁጥር ያላቸው ታዳጊ ሴት ልጆች፣ ይህንኑ ችግር ሲጋፈጡት ኖረዋል፤ ችግሩ በአገር ደረጃም የምንታወቅበት ትልቁ ችግራችን ሆኖ ቆይቷል ያሉት ዶ/ር የትም ወርቅ፤ የትግራይ ክልል ይህንኑ ስር የሰደደ ችግር ለማስወገድና ህብረተሰቡ ያለ ዕድሜ ጋብቻ የሚያስከትለውን አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊና አገራዊ ችግር ተገንዝቦ፣ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል፡፡ አክለውም፤ ከዚሁ ከዕድሜ በታች ጋብቻ ጋር በተያያዘ በታዳጊ ሴት ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያስችል ጥናት ማድረጋቸውንና በጥናቱም ከ5ኛ እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ ያሉ ታዳጊ ሴት ሕጻናት በብዛት ትምህርታቸውን እያቋረጡ እንደሆነ ማወቃቸውን፣ ይህም ዕድሜ ልጆቹ ለጋብቻ የሚታጩበትና የሚዳሩበት ዕድሜ በመሆኑ ታዳጊ ሴት ሕጻናቱ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡት በግዳጅ በሚደረገው ያለ ዕድሜ ጋብቻ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል:: ይህንን ችግር ለመከላከልም ክልሉ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፋ ያለ ሥራ እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
‹‹ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ›› በትግራይ ክልል ከሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ቀዳሚው መሆኑን የገለፁት ዶ/ር የትም ወርቅ፤ ድርጅተ በሚንቀሳቀስባቸው ወረዳዎችና አካባቢዎች ያለ ዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በከፍተኛ መጠን ቀንሰው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ክልሉ ይህንን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስወገድ በሚያደርገው እርብርብ የወርልድ ቪዥን ድጋፍና እገዛ ከፍተኛ ጉልበት ይሆናልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2025 የሴት ልጅ ያለዕድሜ ጋብቻን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት መስማማቷን ያስታወሱት ዶ/ር የትም ወርቅ፤ ይህንን ዕቅድ ለማሳካትና ያለ ዕድሜ ጋብቻን የተጠቀሰው ጊዜ ከመድረሱ በፊት ከክልላቸው ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ናሽናል ዳይሬክተር ሚስተር ኤዲ ብራውን በመቀሌ ከተማ ውስጥ በተከናወነው የፀረ ጾታ ጥቃት ንቅናቄ መክፈቻ ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት፤ ያለ ዕድሜያቸው የሚዳሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ የግንዛቤ ማነስና ድህነት ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል:: እነዚህን ችግሮች ማስወገድ ከተቻለ ያለ ዕድሜያቸው የሚዳሩ ሴት ታዳጊ ልጆችን ቁጥር በእጅጉ መቀነስ እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡  ለዚህም ‹‹ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ›› ከክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመተባበር፣ ለለውጥ ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ያለ ዕድሜ ጋብቻ በአገራችን ዘመናትን ያስቆጠረ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሲሆን ድርጊቱ በአገሪቱ የወንጀልም ሆነ የፍትሃ ብሔር ሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ወንጀል ሆኖ ተደንግጓል፡፡  
ይህንኑ የፀረ ጾታ ጥቃት የማውገዝ ንቅናቄ ወይም የነጭ ሪባን ቀንን አስመልክቶ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው አንድ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው ተድረዋል ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ከአስር ሴቶች አራቱ ዕድሜያቸው ለጋብቻ ሳይደርስ ተገደው ተድረዋል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለ ዕድሜ ጋብቻ በከፍተኛ መጠን ይታይባቸዋል ከተባሉ 20 አገራት መካከል አስራ ሰባቱ የአፍሪካ አገራት ናቸው፡፡
ይህንን ስር የሰደደ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ቢቻል ለማስወገድ፣ ካልተቻለም በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የአንበሳውን ድርሻ መያዝ ያለበት ህብረተሰቡ እንደሆነ ያመለከተው የፀረ ጾታ ጥቃት ንቅናቄን ቀን አስመልክቶ የወጣው መረጃ፤ ህብረተሰቡ ያለ ዕድሜ ጋብቻ የሚያስከትለውን ማህበራዊ ቀውስና ድርጊቱ በሴት ታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጥረውን አካላዊና ስነ ልቦናዊ ችግር በመገንዘብ ድርጊቱን አጥብቆ ሊያወግዝና ከድርጊቱ ሊቆጠብ እንደሚገባ  አሳስቧል፡፡    

Read 3644 times