Saturday, 21 December 2019 12:50

‘እነሱ’ በሰማይ ቤት!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ! ውድ ልጆችህ መጥተናል፡፡
አንድዬ፡— ብላችሁ፣ ብላችሁ ተደራጅታችሁ መጣችሁብኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ መደራጀታችን እኮ አይደለም፡፡ ሁልጊዜ ለየብቻችን እየመጣን ከምናስቸግር ለምን ሁለት፣ ሶስት ሆነን አንሄድም ተባብለን ነው፡፡
አንድዬ፡— ስማኝ፣ መጀመሪያ ነገር፣ ለየብቻችሁ መች ቻልኳችሁና ነው፣ ጭራሽ በቡድን የምትመጡት!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ካስከፋንህ ይቅርታ፡፡ ደግሞ እኔ እንጂ እነኚህ ሁለቱ መጥተው ስለማያውቁ፣ ደጃፍህ መቅረብ ምን ስሜት እንደሚሰጥ እንዲያውቁት ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— ተው አታስቀኝ፣ አንተ ደጃፌ ተመላልሰህ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረና ነው? እንደማይህ ያው ነህ፡፡ እንደውም አንዳንዴ ይብስብሀል፡፡ ከእኔ ምክር የተቀበልክ ይመስላቸዋል እያልኩ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ፤ እንደሱ አትበል! አንድ የቀረኸኝ ተስፋ አንተ!
እሱ አንድ፡— እኛ በመምጣታችን አስከፋን እንዴ!
አንድዬ፡— እኔንማ ምን ታስከፉኛላችሁ! የገረመኝ ነገር ምድር ላይ ጎን ለጎን ለመሄድ እንኳን የምትጠየፉ ሰዎች፤ ምን ተአምር አገናኛችሁ ብዬ ነው፡፡ ከእኔ በኩል የተላከ ተአምር እንደሁ የለ! ግን በጤናችሁ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እያየኸን፣ በጣም ጤነኞች ነን፡፡
አንድዬ፡— በማየትማ መፍረድ ትቻለሁ:: እናንተን በማየትና በመስማት ብቻ መፍረድ ከተውኩ እኮ ሰነበትኩ፡፡
እሱ አንድ፡— በምን ምክንያት?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንተ! ምድር የለመድከውን፣ ያመጣልህን ዝም ብለህ ትዘረግፋለህ! አንድዬን ነው እንዲህ በእብሪት የምትናገረው፡፡
አንድዬ፡— ተወው፣ ምን አጠፋ፡፡ ራሱን ነው የሆነው፡፡ ስሜን እየጠሩ ሰዉን ስላጭበረበሩ፣ እኔንም ያጭበረበሩኝ ከሚመስላቸው፣ እንዲህ የሚናገረው ይሻላል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ቢሆንም፣ አንድዬ! ቢሆንም፡፡ እኔ እንዲህ አይነት ማን አለብኝነት ንግግር መታገስ አልችልም፡፡
አንድዬ፡— ታገስ ግዴለም፣ ታገስ፡፡ ይኸው እኔ ስንት ዘመን አንተን ስታገስ ኖሬ የለም! ማነህ… አንተኛው ምን ነበር ያልከኝ?
እሱ አንድ፡— እናንተን በማየትና በመስማት መፍረድ ትቻለሁ ስትል ስላልገባኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ይሄ ሰውዬ! ደግመህ አንድዬን እንዲህ አፍንጫህን ነፍተህ እናገራለሁ ብትል አናትህን…ይቅርታ አንድዬ፣ በጣም ይቅርታ፡፡
አንድዬ፡— አየህ ችግራችሁ እኮ ይሄ ነው:: ደጃፌ ድረስ መጥታችሁም አናት ስለ ማፍረስ ነው የምታወሩት፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ስሀትት ነው፡፡
አንድዬ፡— ስማኝ ጌታው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ተው አንጂ፡፡ እንዲሁም እብሪቱ አላስቀመጠን ደግሞ ጌታ ብለኸው መቆሚያ መቀመጫ ነው የሚያሳጣን::
አንድዬ፡— እንግዲህ እኔም በበኩሌ ስፈጥራችሁ፣ ሁላችሁን በእኩልነት ነው እንጂ አንዳችሁን ከአንዳችሁ   አላበላለጥኩም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ይህ አልገባ ያለው ተሰብስቦ ነው እኮ መከራ እያበላን ያለው፡፡ ከጫፍ ጫፍ እኮ በእብሪተኞች ተሞላን፡፡
እሱ ሁለት፡— ከአናንተ የባሰ እብሪተኛ አለ እንዴ!
አንድዬ፡— ጭራሽ እዚሁ ልትጀምሩ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ስማ በራስ መተማመንና እብሪተኝትን አታምታታው፡፡
እሱ ሁለት፡— እናንተ አይደላችሁ እንዴ፣ ካለ እኛ ሰው የለም እያላችሁ..
አንድዬ፡— ቆይ ቆይ፣ ተረጋጋ፡፡ ለእሱ እዛው ምድር ስትመለሱ ትደርሱበታላችሁ፡፡ እኔም ይውጣላችሁ ብዬ ትቻችኋለሁ፡፡ አሁን ወደ ጉዳያችን እንግባ፣ ወደ እኔ የመጣችሁበት ዋና ምክንያት ምን ነበር?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ያው እናማክርህ ብለን ነዋ!
አንድዬ፡— እኮ ምኑን ነው የማማክራችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደው ምን ይሻለናል ትላለህ? መላ ቅጡ ጠፋብን እኮ፡፡
እሱ አንድ፡— ይቅርታ፣ እሱ የአንተ አስተሳሰብ ነው፡፡ እኛ የጠፋብን ምንም ነገር የለም፡፡
እሱ ሁለት፡— እኛም የሁሉ ነገር መጨረሻ እየታየን ስለሆነ፣ አንተ ምን እንደምታስብ ለማወቅ ስለፈለግን ነው ተወክዬ የመጣሁት፡፡
አንድዬ፡— የሁሉም ነገር መጨረሻ ያልከው አልገባኝም፡፡ ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
እሱ ሁለት፡— ማለት የፈለግሁት… በቃ፣ ያቺ ሀገር አብቅቶላታል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን! ምን! አፍህን ሞልተህ ሀገር አብቅቶላታል ትላለህ! ስማ ሀገር ሳያልቅላት በፊት አንተና መሰሎችህ ያልቅላችኋል፡፡
አንድዬ፡— ቆይ እስቲ…  ቱግ፣ ቱግ እኮ ትናትም የትም አላደረሳችሁም፡፡ ወደፊትም የትም አያደርሳችሁም፡፡ አንተኛው ግን ሀገር ያልቅላታል ያልከው - እኔ የማላውቀው ነገር ካለ ብትነግረኝ፡፡
እሱ ሁለት፡— መቼም አንተ ምናልባት አዝነህልን ካልሆነ፣ ሳታየው አልቀረህም፡፡ ሁሉም ነገር ተበላሽቷል፡፡ በዚህ አይነት ብዙ መራመድ አይቻልም የሚል አቋም አለን፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— መቆሚያህን ይስበረው! ደግሞ አቋም ይላል እንዴ!
እሱ አንድ፡— መጮህ ልማዳችሁ ነው፡፡
አንድዬ፡— እስቲ አንተኛው ሰከን በል፡፡ ስንት ዘመን እኔ ዘንድ ስትመላለስ፣ ያላየሁብህን ጭራሽ ጉልበተኛ ሆንህ መጣህ ማለት ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን ላድርግ አንድዬ፣ እነኚህ ሰዎች ሊያሳብዱኝ ነው እኮ!
እሱ አንድ፡— እሱ እኮ ቆየ፡፡ አንተ ራስህም አላወቅህም ማለት ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምኑን ነው የማውቀው?
እሱ ሁለት፡— ራስህን ነካ ካደረገህ ቆየት ማለቱ ነው፡፡
አንድዬ፡— እኔ እኮ የሚገርመኝ ---- ለእናንተ ትልቅ ጀግንነት መሰዳደብ፣ መዘላለፍ‹ በባዶ ሜዳ መፎከር ሆነና ቀረ! አንዳችሁ ሌላኛችሁን ስላንቋሸሻችሁ፣ ስለዘለፋችሁ የተሻልን ነን ብላችሁ ታስባለችሁ??
እሱ አንድ፡— መሻል ሳይሆን ያው መቼም የአስተሳሰብ መበላለጥ አለ…
አንድዬ፡— የሀሳብ መበላለጥ ብሎ ነገር የለም፡፡ ያኛው ወገን ከአንተ የተለየ ሀሳብ ስላለው ብቻ የአንተ ይበልጣል ማለት አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ሁላችሁም በተለያየ አገላለጽ ተናገሩት እንጂ ፣ጥላቻና በቀል ከማራገብ ምን የተሻለ ሀሳብ አላችሁና ነው!
እሱ አንድ፡— እሱ ላይ የተወሰነ እውነት ሳይኖረው አያቀርም…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንተ ሰውዬ፣ ተው ደሜን አታፍላው! አንድዬን በስነ ስርአት አናግር፡፡
እሱ አንድ፡— አሁን ምን አጠፋሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ላይ ነው የተወሰነ፣ ያልተወሰነ እያልክ የምትመጻደቀው! እኔ እኮ እዚህ ያመጣኋችሁ እንድትመጻደቁ ሳይሆን የሰፈረባችሁ እርኩስ መንፈስ ይለቃችኋል ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— አንተ ጣልቃ እየገባህ አታበላሽ እንጂ… የፈለጉትን ሊናገሩ አይደለም እንዴ እዚህ የመጡት!
እሱ አንድ፡— አ…አ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ‹ ስሙን ጠርተህ  ስለማታውቅ ከበደህ እንዴ!
አንድዬ፡— በሉ፣ ተጨቃጭቃችሁ ስትጨርሱ የሚዘጋ በር ባይኖርም በሩን ዘግታችሁ ሂዱ፡፡ እኔ ሌሎች አጣዳፊ ሥራዎች አሉብኝ፡፡ ጉድ እኮ ነው! (አንድዬ ሄደ፡፡)
ምስኪን ሀበሻ፡— አየህ ያደረግኸውን!
እሱ አንድ፡— ምን እኔ ላይ ታፈጣለህ፣ ራስህ አይደለህ!
እሱ ሁለት፡— ሁላችሁም አይደላችሁ እንዴ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2377 times