Saturday, 21 December 2019 12:29

ኢትዮ ቴሌኮም አንድነት ፓርክን ለሚጎበኙና በውጭ ለሚገኙ ትኬት በኦን ላይን መሸጥ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

     ኢትዮ ቴሌኮም በውጭ አገር ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ አገር ዜጎች ባለቡት አገር ሆነው አንድነት ፓርክን ለመጎብኘት የሚያስችል የመግቢያ ትኬት በኦንላይን መግዛት የሚያስችል አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ፡፡
አገልግሎቱ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ የሌላ አገራት ዜጎች፣ ፓርኩን ለመጎብኘት ባሰቡ ጊዜ ባሉበት ቦታ ሆነው የመግቢያ ትኬቱን ለመግዛት ወይም አገር ቤት ለሚገኙ ዘመድ ወዳጆቻቸው ለስጦታ ለማበርከት ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን አሰራር ለመተግበር ዓለም አቀፍ የአየር ሰዓት አስተላላፊ ከሆኑ አጋር ድርጅት ጋር በትብብር መስራት መጀመሩንና አገልግሎቱን በይፋ መጀመሩን የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር የሆኑት ወይዘሮ ጨረር አክሊሉ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በውጭ የሚገኙ ሰዎች ፓርኩን ራሳቸው ለመጎብኘትም ሆነ መግቢያውን ለወዳጅ ዘመድ ገዝተው በስጦታ መልክ ለመስጠት ሲፈልጉ ወደ ኢትዮ ቴሌኮም አጋር ድርጅት ድረ ገጽ WWW.remit.et. በመግባትና ቀጣይ መመሪያዎችን በመከተል የመግቢያ ትኬቱን የፓርኩ አስተዳደር በተመነው ዋጋ በቀላሉ መግዛት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ቀደም ሲል አገር ቤት የሚገኙ የፓርኩ ጎብኚዎች ሰልፍ መያዝና መጉላላት ሳይጠበቅባቸው በአጭር የጽሑፍ መልዕክት (SMS) ወደ ‹‹6030›› ‹‹አ›› ወይም በእንግሊዝኛው ‹‹ሀ›› ብለው በመላክ ወይም በፓርኩ ድረ ገጽ አማካኝነት በቀላሉ ትኬት መግዛት የሚችሉበትን አሰራር ተግባራዊ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ኢትዮ ቴሌኮም ለአገር ቤትም ሆነ ለውጭ ጎብኚዎች ዘመናዊና ቀልጣፋ አሰራርን አመቻችቶ ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ መጀመሩን ኩባንያው ጨምሮ ገልጿል፡፡


Read 1971 times