Saturday, 21 December 2019 11:44

የወላይታ የክልልነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚጠይቁ ሰልፎች በሳምንቱ ሲካሄዱ ሰንብተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)


                          ወላይታ ዞን ላይ የተጠናከረ የፀጥታ ቁጥጥር እየተደረገ ነው

                ለወላይታ የክልልነት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ ባሳለፍነው ሳምንት በነበሩ ተከታታይ ቀናት የአገር ሽማግሌዎች፣ ነጋዴዎች፣ ሴቶች፣ የታክሲና ባጃጅ አሽከርካሪዎች፣ ወጣቶች በተናጠል በወላይታ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ የሰነበቱ ሲሆን ከረቡዕ ጀምሮ አካባቢው በተጠናከረ የኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ስር መዋሉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ ተከታታይ ሰላማዊ ሰልፎች ሲካሄዱ የነበሩት የወላይታ የክልልነት ጥያቄ በሕገ መንግስቱ መሰረት ለክልሉ ም/ቤት ከቀረበ 1 አመት መሙላቱን በማስመልከት መሆኑን በዋናነት የክልልነት ጥያቄውን በኮሚቴነት የሚያንቀሳቅሱ ምንጮች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የወላይታ የክልልነት ጥያቄ ከቀረበ ትናንት ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም አንድ ዓመት ቢሞላውም ከየትኛውም አካል በጉዳዩ ላይ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ  ምላሽ አለመገኘቱን የገለፁት ምንጮች ይህም በሕገ መንግስቱ መሠረት ለጥያቄው ምላሽ የሚሆን ሕዝበ ውሳኔ እየተደራጀ አለመሆኑ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ሕገ መንግስቱ ‹‹ጥያቄው በቀረበ በ1 ዓመት ውስጥ ምላሽ ማግኘት አለበት ቢልም ምላሽ አለመገኘቱን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት የእንቅስቃሴው መሪዎች በዚህ መነሻ ወላይታ ከዛሬ ቅዳሜ ጀምሮ ከደቡብ ክልላዊ መንግስት ጋር ግንኙነት አይኖረውም ቀጥተኛ ግንኙነት የሚኖረው ከፌዴራሉ ጋር ይሆናል›› ብለዋል፡፡
የወላይታ የክልልነት ጥያቄ ሕግን የተከተለና በጨዋነት የተሞላ ነው ያሉት ምንጮች ከሁለት ሳምንት በፊት ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ሕዝቡን ወክለው ላደረጉት ውይይትም ጠ/ሚኒስትሩ የወላይታ ሕዝብ ክልል መሆን ከፈለገ የሚያግደው ነገር እንደሌለ ማስገንዘባቸውን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል:: ከሕዝቡ ጋር በተደረገ ውይይትም ጥያቄውን እስከ መጨረሻው በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለማቅረብ ቃል ኪዳን መታሰሩን ምንጮች አስረድተዋል፡፡  
በአንጻሩ ሶዶ ከተማን ጨምሮ በዞኑ የተለያዩ ከተሞች ጠንካራ የኮማንድ ፖስት የፀጥታ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ሀሙስ ምሽት የተወሰኑ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮችና ወጣቶች ታስረው የነበረ ቢሆንም ምክር ተሰጥቷቸው በርካቶቹ ትናንት መለቀቃቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡  
የወላይታ የክልልነት ጥያቄን አስመልክቶ ሕዝቡ ሙሉ ለሙሉ እንደተስማማና ሰፊ ውይይት እንደተደረገበት ለጠ/ሚኒስትሩ ገለጻ መደረጉን የጠቆሙት ምንጮች ሕዝቡ ክልል መሆንን የሚመርጥ ከሆነ ሕጋዊ ሂደትን ተከትሎ ነገሩ መቋጨት እንዳለበት ማስረዳታቸውንም በውይይቱ የተሳተፉ ምንጮች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ ኮሚኒኬሽን ኃላፊዋ ሶሊያና ሽመልስ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ስልካቸው ባለመነሳቱና ስብሰባ ላይ ነን የሚል አጭር መልዕክት በመመለሳቸው ሊሳካልን አልቻለም፡፡  

Read 1356 times