Print this page
Saturday, 14 December 2019 13:06

ከ20 ዓመት በኋላ

Written by  ጌጡ ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

  የፖሊስ መኮንኑ ጎዳናውን በኩራት መንፈስ አቋርጦ አለፈ፡፡ ግርማ ሞገስ የተሞላበት አረማመዱ፣ ተፈጥሯዊ አኳኋኑ እንጂ ለታይታ ብሎ የሚያደርገው አይደለም፡፡ ሁሌም በዚህ መልኩ ነው ሲጓዝ የኖረው፡፡ ሰውየው ምን እንደሚመስል እያሰበ አልነበረም፡፡ በመንገድ ላይ እሱን የሚያዩት ጥቂት ሰዎች ነበሩ፡፡ ገና ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ገደማ ቢሆን ነው፤ ግን አየሩ ብርዳም ነው፡፡ በዚያ ላይ ጥቂት ዝናብ የተቀላቀለ ንፋስም አለ፡፡
ፖሊሱ እጁ ላይ ያለችውን አጭር የፖሊስ ቆመጥ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ከቀኝ ወደ ግራ እጁ እያሽከረከረ ይጓዛል፡፡ በእርምጃው መሀል በየበሮቹ ላይ ቆሞ፣ እያንዳንዱ በር መዘጋቱን ለማረጋገጥ፣ በእጁ ገፋ ገፋ በማድረግ ይሞክራል፡፡ አልፎ አልፎ ቀና እያለ የአውራ ጎዳናውን ላይና ታች ይቃኛል፡፡ መልከ መልካም ፖሊስ ነው፤ ንቁ፤ ለሰላም ዘብ የቆመ፡፡
በዚህኛው የከተማይቱ ክፍል ያሉ ሰዎች፣ በጊዜ ወደ የቤታቸው ሄደዋል፡፡ አልፎ አልፎ ሱቅ ወይም የትንሽዬ ምግብ ቤት መብራቶችን ልትመለከቱ ትችላላችሁ፡፡ አብዛኞቹ በሮች ግን ቀደም ብለው ከስዓታት በፊት የተዘጉት የንግድ ሥፍራዎች ናቸው፡፡
ፖሊሱ ድንገት እርምጃውን ቀነስ አድርጎ፤ ዝግ ብሎ ይራመድ ገባ፡፡ ከአንድ የጨላለመ ሱቅ በር አጠገብ አንድ ሰው ቆሞ ነበር፡፡ ፖሊሱ ወደ እሱ እየተራመደ ሳለ፣ ሰውየው ከመቅጽበት አንደበቱ ተከፈተ፤ በፍጥነት ይናገር ጀመር፡፡
‹ጌታዬ፤ ምንም ችግር የለም!›› አለ ሰውየው፤ ‹‹ጓደኛዬን እየጠበቅሁኝ ነው፤ የዛሬ ሃያ ዓመት በዚህች ምሽት እዚህ ቦታ ላይ ለመገናኘት ተቀጣጥረናል፡፡ ለአንተ ግር ሊልህ ይችላል፤ ግር ብሎሃል አይደል? ሁሉም ነገር አማን መሆኑን ለማረጋገጥ የምትሻ ከሆነ ጉዳዩን በደንብ አስረዳሃለሁ፡፡ የዛሬ ሃያ አመት ግድም፣ ይህ ሱቅ ያለበት ቦታ ላይ አንድ ምግብ ቤት ነበር፡፡ ‹‹ቢግ ጆ  ሬስቶራት፡፡››
‹‹እስከ ዛሬ አምስት ዓመት ድረስ እዚሁ ነበረ››  ፖሊሱ መልስ ሰጠ፡፡
ሱቁ በር አጠገብ የቆመው ሰውዬ፤ አራት ማዕዘን የፊት ቅርጽና የሚያበሩ አይኖች አሉት፡፡ ቀኝ አይኑ አጠገብ ትንሽ ነጭ ምልክት አለበት፡፡ አንገቱ ላይ ትልቅ አልማዝ አስሯል፡፡
‹‹የዛሬ ሃያ አመት በዛሬዋ ምሽት›› ሲል ጀመረ ሰውየው ፤‹‹ከጂሚ ዌልስ ጋር እዚህ ራት በልቼአለሁ፡፡ እሱ ምርጥ ጓደኛዬና በአለም ላይ ምርጡ ሰው ነው፡፡ እኔና እሱ እዚሁ ኒው ዮርክ፣ እንደ ሁለት ወንድማማቾች አብረን ነበር ያደግነው፡፡ ስንለያይ እኔ 18፣ እሱ ደግሞ 20 ዓመቱ ነበር፡፡ በነጋታው ጠዋት ወደ ዌስት ተጓዥ ነበርኩ፡፡ ሥራ ማግኘትና ትልቅ ስኬት መቀዳጀት ነበረብኝ፡፡ ጂሚን ከኒው ዮርክ ማስወጣት የማይሞከር ነው፤ ልታደርገው አትችልም፡፡ ኒው ዮርክ በምድር ላይ ብቸኛዋ ስፍራ ነበር የምትመስለው፡፡
‹‹የዚያን እለት ምሽት፤ በሃያኛው ዓመታችን፣ በዚሁ ሥፍራ በድጋሚ ለመገናኘት ተስማምተን ነበር፡፡ በሃያ አመት ጊዜ ውስጥ ምን አይነት ሰዎች እንደምንሆንና የወደፊት እጣ ፈንታችን ምን እንደሚመስል እንደምናውቅ ተማምነናል::”   
‹‹ጉዳዩ የሚማርክ ይመስላል›› አለ ፓሊሱ፤
‹‹ከተለያያችሁ ረዥም ጊዜያችሁ ይመስለኛል:: ወደ ዌስት ከሄድክ ወዲህ ስለ ጓደኛህ ሰምተህ  ታውቃለህ?››
“አዎ፤ ለተወሰነ ጊዜ እንፃፃፍ ነበር›› አለ ሰውየው፤ ‹‹ከዓመት ወይም ከሁለት ዓመት በኋላ ግን ተውነው፡፡ ዌስት ትልቅ አገር ነው፡፡ እኔ ደግሞ አንድ ቦታ አልቀመጥም፡፡ በየቦታው እዟዟር ነበር፤... ግን ጂሚ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ካልገጠመው በቀር እዚህ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በዓለም ላይ የማውቀው ብቸኛው ሀቀኛ ነው፡፡ ቀጠሮአችንን ፈፅሞ ሊረሳው አይችልም፡፡ ዛሬ ማታ እዚህ ለመቆም አንድ ሺህ ማይሎች አቋርጬ ነው የመጣሁት:: ይህን በማድረጌ ግን ደስተኛ ነኝ፡፡ ግን የድሮ ጓደኛዬም የሚመጣ ከሆነ ነው››
ጠባቂ ሰውዬ፤ በትንሽዬ አልማዝ የተለበጠ ሰዓት አወጣና፤ ‹‹ለአራት ሰዓት ሦስት ደቂቃ ጉዳይ ነው››አለ፤ ‹‹የዚያን ዕለት ማታ ምግብ ቤቱ በር ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ስንሰናበት አራት ሰዓት ነበር፡፡››
‹‹በዌስት ሳይሳካልህ አልቀረም፡፡ ተሳሳትኩ እንዴ?›› ፖሊሱ ጠየቀው፡፡
 ‹‹እንዴታ ተሳክቶልኛል እንጂ! ጂሚ የእኔን ግማሽ ያህል እንደተሳካለት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እሱ ቀሰስተኛ ነው፡፡ እራሴን የስኬት ማማ ላይ ለማውጣት መታገል ነበረብኝ፡፡ በኒው ዮርክ ሰው ብዙም አይለወጥም፡፡ በዌስት ማግኘት ለምትፈልገው ነገር እንዴት መታገል እንዳለብህ ትማራለህ፡፡››
 ፖሊሱ  ሁለት እርምጃ ተራመደና፡-
‹‹እኔ እንግዲህ ልሂድ›› አለ ‹‹ጓደኛህ በሰላም እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በ4 ሰዓት እዚህ ካልደረሰ ትሄዳለህ ማለት ነው?››
‹‹አልሄድም!›› አለ ሰውየው፤ ‹‹ቢያንስ ለግማሽ ሰዓት እጠብቀዋለሁ፡፡ ጂሚ በህይወት ካለ፣ በዚያ ሰዓት እዚህ ይገኛል፡፡ ይህና ደር፤ ጌታዬ››
‹‹ደህና ደር›› አለና ፖሊሱ መንገዱን ቀጠለ፤ በሮቹ መዘጋታቸውን እያረጋገጠ፡፡
አሁን በረዷማ ዝናብ እየጣለ ሲሆን ንፋሱም አይሏል፡፡ በጎዳናው ላይ የሚጓዙት ጥቂት ሰዎች እየተጣደፉ ነበር፤ሰውነታቸውን ለማሞቅ እየሞከሩ፡፡ በሱቁ በር ላይ ደግሞ ጓደኛውን ለማግኘት አንድ ሺህ ማይሎች አቋርጦ የመጣው ሰውዬ ቆሟል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ቀጠሮ እርግጠኛ መሆን አይቻልም:: እሱ ግን እየጠበቀ ነው፡፡ 20 ደቂቃ ገደማ ጠበቀ:: ከዚያም አንድ ረዥም ኮት የለበሰ ሰውዬ ከመንገዱ ማዶ እየተጣደፈ መጣ፡፡ በቀጥታ ቆሞ ወደሚጠብቀው ሰውዬ አመራ፡፡
‹‹ቦብ፤ አንተ ነህ?›› ሲል ጠየቀ፤ እየተጠራጠረ::
‹‹አንተ ነህ፤ ጂሚ ዌልስ?›› አለ፤በሩ ላይ የቆመው ሰውዬ፡፡   
አዲሱ ሰውዬ፤ የሌላኛውን እጅ በእጁ መዳፍ ውስጥ አስገባው፡፡
‹‹ቦብ ነህ! በእርግጠኛነት ነህ፡፡ በህይወት ካለህ እዚህ ቦታ ላይ እንደማገኝህ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ 20 ዓመት ረዥም ጊዜ ነው፡፡ የድሮው ምግብ ቤት ተዘግቷል፡፡ ቦብ፤ ያ ምግብ ቤት ቢኖር ደስ ይለኝ ነበር፤ ሌላ እራት እንመገብበት ነበር፡፡ በነገራችን ላይ እንዴት ነው፣ ዌስት ተስማማህ?››
‹‹የፈለግሁትን ሁሉ ሰጥቶኛል፡፡ ጂሚ አንተ ግን ተለውጠሃል፤ እንዲህ ትረዝማለህ ብዬ አልጠበቅሁም፡፡››  
‹‹ኦህ፤ 20 ዓመት ከሞላኝ በኋላ ጥቂት አድጌአለሁ››
‹‹ኒው ዮርክ ተስማማህ፤ ጂሚ?››
‹‹በሚገባ፡፡ ለመንግስት ተቀጥሬ እየሰራሁ ነው፡፡ በል አንድ የማውቀው ሥፍራ እንሂድና፣ የሆድ የሆዳችንን እናውጋ፡፡”
 ሁለቱ ሰዎች እጅ ለእጅ ተያይዘው መንገድ ጀመሩ፡፡ የዌስቱ ሰውዬ የህይወት ታሪኩን እየተረከ ነው፡፡ ሌላኛው ኮቱን እስከ ጆሮው ድረስ አቁሞ በትኩረት ያዳምጠው ነበር፡፡ አንድ ጥግ ላይ በኤሌክትሪክ መብራት የደመቀ አንድ ሱቅ ይታያል፡፡ እዚያ ሲደርሱ ሁለቱም ቀና ብለው ፊት ለፊት ተያዩ፡፡
ከዌስት የመጣው ሰውዬ፤ ድንገት ቆም አለና እጁን መንጭቆ አስለቀቀ፡፡
‹‹አንተ ጂሚ ዌልስ አይደለህም›› አለ ኮስተር ባለ የድምጽ ቃና፤ ‹‹20 ዓመት ረጅም ጊዜ ነው፤ ነገር ግን የሰውን የአፍንጫ ቅርጽ ግን አይለወጥም››
‹‹አንዳንድ ጊዜ ግን ጥሩ ሰውን ወደ መጥፎ ሰው ይለውጣል›› አለ ረዥሙ ሰውዬ፤ ‹‹ቦብ፤ ለአሥር ደቂቃ ያህል በቁጥጥር ሥር ነበርክ፤ የቺካጎ ፖሊሶች ወደ ኒው ዮርክ ልትመጣ እንደምትችል ገምተው ነበር፡፡ በዓይነ ቁራኛ እንድንጠባበቅህም ነግረውናል፡፡ አሁን ከእኔ ጋር ድምጽህን አጥፍተህ ትመጣለህ?! … ያንን ማድረግ ብልህነት ነው፡፡ በመጀመሪያ ግን ይህንን ደብዳቤ ስጠው ተብያለሁ፡፡ እዚህ መብራቱ ጋ ልታነበው ትችላለህ፡፡ ዌልስ ከተባለ ፖሊስ ነው የተላከልህ፡፡››
ከዌስት የመጣው ሰውዬ፤ትንሿን ቁራጭ ወረቀት ገለጣት፡፡ ወረቀቱ ላይ የሰፈረውን ሲያነብ እጁ ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡  
‹‹ቦብ፤ በቀጠሮአችን መሰረት፣ በተባባልንበት ቦታ፣ በሰዓቱ ተገኝቼ ነበር፡፡ በቺካጎ ፖሊሶች የሚፈለገውን ሰውዬ ፊት አየሁት፡፡ እኔ ራሴ በቁጥጥር ሥር ላውልህ አልፈለግሁም፡፡ ስለዚህ ተመልሼ ሄድኩና፣ ሌላ ፖሊስ እንዲይዝህ ላኩት፡፡
 ጂሚ››
ምንጭ፡- (ከኦ ኸነሪ “After Twenty Years” የተሰኘ አጭር ልብወለድ የተተረጎመና
በቅርቡ ለህትመት ከሚበቃ
የጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን መጽሐፍ የተወሰደ)

Read 3019 times