Tuesday, 17 December 2019 00:00

ቻይና ጋዜጠኞችን በማሰር ዘንድሮም አለምን ትመራለች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 በዓለም ላይ ከ250 በላይ ጋዜጠኞች ታስረዋል

             በመገባደድ ላይ በሚገኘው የፈረንጆች 2019 ብቻ በመላው አለም ከ250 በላይ ጋዜጠኞች መታሰራቸውንና ላለፉት አመታት ከአለማችን አገራት መካከል በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚነቱን ይዛ የዘለቀችው ቻይና፤ ዘንድሮም በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧ ተነግሯል፡፡
ተቀማጭነቱ በኒው ዮርክ የሆነው አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርቱ እንዳለው፤ ባለፉት 11 ወራት ጊዜ ውስጥ 48 ያህል ጋዜጠኞችን ያሰረችው ቻይና፣ ብዛት ያላቸው ጋዜጠኞች በማሰር ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን ይዛለች፡፡
በአመቱ 47 ጋዜጠኞችን በማሰር በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ቱርክ መሆኗን የጠቆመው የሲፒጄ ሪፖርት፤ ያም ሆኖ ግን በአገሪቱ የታሰሩት ጋዜጠኞች ቁጥር አምና ከነበረው በ68 መቀነሳቸውን አመልክቷል፡፡ ሳዑዲ አረቢያና ግብጽ እያንዳንዳቸው በተመሳሳይ 26 ጋዜጠኞችን በማሰር በሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፣ ኤርትራ 16 እንዲሁም ቬትናም 12 ጋዜጠኞችን በማሰር የአራተኛና የአምስተኛ ደረጃን መያዛቸውንም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡
በአመቱ በመላው አለም ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞች ቁጥር አምና ከነበረው 255፣ በ5 ብቻ የቀነሰ ሲሆን በመላው አለም ለእስር ከተዳረጉት 250 ጋዜጠኞች መካከል 20ዎቹ ሴቶች መሆናቸውንና የሴት ጋዜጠኞች ድርሻ ከአምናው በ13 በመቶ መቀነሱን ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ ሃሰተኛ ዜናዎችን አሰራጭተዋል በሚል በመንግስታት ለእስር የሚዳረጉ ጋዜጠኞች ቁጥር ባለፉት አራት ተከታታይ አመታት እያደገ መምጣቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአመቱ በዚህ ሰበብ 30 ጋዜጠኞች ለእስር መዳረጋቸውንም አመልክቷል፡፡ ሲፒጄ በየአመቱ ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞችን ዝርዝር በማጥናት ሪፖርት ማውጣት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች የታሰሩበት አመት 2016 እንደነበር የተነገረ ሲሆን፣ በአመቱ 273 ጋዜጠኞች መታሰራቸውንም ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡

Read 8057 times