Monday, 16 December 2019 00:00

ሳተላይቶች በመብዛታቸው እርስ በእርስ እንዳይጋጩ ተሰግቷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በጠፈር ላይ ከ5 ሺህ በላይ ሳተላይቶችና 20 ሺህ ስብስባሪ አካላት ይገኛሉ

          የአለማችን አገራት ለጠፈር ምርምር ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸውንና በርካታ ቁጥር ያላቸው ሳተላይቶችን ወደ ጠፈር መላካቸውን ተከትሎ፣ ጠፈር በሳተላይቶች መጨናነቁንና ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል መባሉን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በጠፈር ላይ የሚገኙ ሳተላይቶች ቁጥር እጅግ እየተበራከተ ከመሄዱ ጋር በተያያዘ፣ በዘርፉ ተመራማሪዎች ዘንድ ሳተላይቶች እርስበርስ ሊጋጩ ይችላሉ የሚል ስጋት መፈጠሩን የጠቆመው ዘገባው፤ አገራት የሳተላይቶችን እንቅስቃሴ በአግባቡ የሚቆጣጠሩበትንና ያረጁ ሳተላይቶችን በአግባቡ የሚያስወግዱበትን መንገድ መፍጠር እንደሚገባቸው መነገሩን አመልክቷል፡፡
ሩስያ እ.ኤ.አ በ1957 ስፑትኒክ የተባለችውን የመጀመሪያዋን የአለማችን ሳተላይት ወደ ጠፈር ካመጠቀችበት ጊዜ አንስቶ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሳተላይቶች ወደ ጠፈር መምጠቃቸውንና በአሁኑ ወቅት በጠፈር ላይ 5 ሺህ ያህል ሳተላይቶች እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፤ በዚህም እርስ በእርስ ለመጋጨት የሚችሉበት ዕድል መፈጠሩን አውስቷል፡፡
ከአስር አመታት በፊት የተከሰተውና በታሪክ ሳተላይቶች እርስ በእርስ የተጋጩበት አጋጣሚ አንድ ጊዜ ብቻ ቢሆንም፣ አሁን አሁን ግን ከሳተላይቶች ቁጥር መበራከትና በቀጣይም የተለያዩ አገራትና የዘርፉ ኩባንያዎች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ሳተላይቶችን ለማምጠቅ  ከማቀዳቸው ጋር በተያያዘ፣ የግጭት ስጋቱ በፍጥነት እያደገ መምጣቱን ገልጧል፡፡
በጠፈር ላይ ያረጁ የመንኮራኩር አካላትንና አገልግሎት ያቆሙ ሳተላይቶችን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ ስብርባሪ አካላት ተበትነው እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፤ መሰል አካላት እየበዙ መምጣታቸውም የሳተላይቶች ግጭት ስጋቱን እያባባሰው እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡


Read 3335 times