Sunday, 15 December 2019 00:00

የ34 አመቷ ፊንላንዳዊት የአለማችን ወጣቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአገሪቱን ጥምር መንግስት የሚመሰርቱት 5 ፓርቲዎች በሴቶች የሚመሩ ናቸው

               የ34 አመቷ ፊንላንዳዊት ሳና ማሪን፣ ባለፈው ረቡዕ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆና መመረጧን የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት፤ በአለማችን ታሪክ በአነስተኛ ዕድሜዋ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታን የያዘች ቀዳሚዋ ሴት መሆኗን ገልጧል፡፡
ተሰናባቹን የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቲ ሬኒን ተክታ አገሪቱን እንድትመራ በሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የተመረጠችውና የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆና ስታገለግል የቆየቺው ሳና ማሪን፣ ከሰሞኑ አምስት ፓርቲዎችን ያካተተ ጥምር መንግስት እንደምትመሰርት የጠቆመው ዘገባው፤ የአምስቱም ፓርቲዎች መሪዎች ሴቶች መሆናቸውንና ከአንዷ በስተቀር ሁሉም ከ35 አመት ዕድሜ በታች የሚገኙ መሆናቸው የአለምን ትኩረት መሳቡን አመልክቷል፡፡
የ34 አመቷ ሳና ማሪን ላለፉት አራት አመታት የፊንላንድ ፓርላማ አባል ሆና መዝለቋን ያስታወሰው ዘገባው፤ በፓርቲዎች አመኔታን በማጣታቸው ሳቢያ ባለፈው ሳምንት ስልጣናቸውን የለቀቁትን ጠቅላይ ሚኒስትር አንቲ ሬኒን ተክታ አገሪቱን እንደምትመራና በአገሪቱ ታሪክ ሶስተኛዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ትሆናለች ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁሟል፡፡
ሳራ ማሪን ወደ ፖለቲካው አለም የገባቺው የ27 አመት ወጣት እያለች እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ በወቅቱ የትውልድ ከተማዋ ታምፔሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ እንደነበረችና በቀጣይ አመታትም በፖለቲካው ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ ማድረጓን እንደቀጠለችና በፓርቲው ውስጥ ቁልፍ የአመራር ቦታን መያዟንም አክሎ ገልጧል፡፡
በአሁኑ ጊዜ አገራትን በመምራት ላይ ከሚገኙ የአለማችን ጠቅላይ ሚኒስትሮች መካከል ዝቅተኛ ዕድሜ አላቸው ተብለው በዘገባው የተጠቀሱት ደግሞ የ39 አመቷ የኒውዝላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደን እና የ35 አመቱ የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሌኪሲ ሆንቻሩክ እንደሚገኙበትም አስታውሷል፡፡

Read 3255 times