Saturday, 14 December 2019 12:23

ኦቦ ለማ መገርሳ - እኛንም አይርሱን!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(10 votes)

  ሰ….ፊ ነው ኢትዮጵያዊነት፣ ፍቅር ነው የስፋት ልኩ፤
ከፍቅር ባነሰ መዳፍ ለመቁረስ ጫፉን አትንኩ፡፡
አለው ስም፣ ግብር - ትንሳዔ በገፍ ያደለው፤
ዐፈር አራግፎ ይነሳል-“ተቀብሯል”፤ ሞቷል ስትለው::
ከሰሞኑ የተሰማው ወሬ ነፍስን ያናውጣል ቢባል የተጋነነ አይመስለኝም፡፡ የፖለቲካ ሰዎች ሳይታሰብ ሃሳብ ሲቀይሩ፣ በወደዱት ሊሥማሙ፣ ባልወደዱት ደግሞ ላይሥማሙ መቻላቸው ብርቅ አይደለም፡፡ የክርስቶስ ጉባዔ ምዕምን ቢከዳ፣ እንደ ይሁዳ ብር ቢመርጥ ግድ አይባልም፡፡ ሃዋርያው ዮሐንስ፣ የእስክ መስቀሉ የልብ ወዳጅ ቢሆን ግን ፀሐይ ነጠላ የምታዘቀዝቅ ይመስለኛል፡፡ ራሱ ክርስቶስን ሰብኮ የሰበሰበውን ጉባዔ መልሶ “ነገሩ እኔም አልገባኝም!” ቢል ድንጋጤው የመብረቅ ያህል ነው፡፡
ለእኔ ለወዳጃቸውና ለመሰሎቼ፣ የለማ መገርሣ ነገር ይህንን ያህል ግራ የሚያጋባ ነው:: አንገታችንን ደፍተን፣ እንባችንን ልባችን ላይ አንጠልጥለን ስናለቅስ፣ “አታልቅሱ፣ ማህተሙን የሚፈታ ተገኝቷል!” ብለው የሀገር አንድነትን የምሥራች የሰበኩን ኦቦ ለማ መገርሣ ናቸው፡፡ በሚጣፍጥ አንደበት፣ እንደ ግጥም በተመረጡ ቃላት፣ የታሪክ ሰበዝ እየመዘዙ፣ ህልምና እውኑን ቀይጠው በደስታ ያሰከሩን እርሳቸው ናቸው፡፡
እኔ በበኩሌ፤ በህይወት ዘመኔ አስቤው የማላውቀውን፣ ለሀገሬ ፖለቲከኛ ነፍስ የመስጠት ቃል ኪዳን የገባሁት ለአቶ ለማ መገርሣ ነው፡፡ ስለዚህም ገና ዝሆኖቹ ጠመንጃቸው ሳይነጠቅ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሃሳባቸውን በመደገፍ መጣጥፌን ሳቀርብ አንዳችም አልፈራሁም ነበር፡፡ ከሞትኩም ከኒህ የሀገሬ አንበሳ ጋር እሞታለሁ ብዬ ተፈጠምኩ:: ከዚያ በፊት በሀገሬ ፖለቲከኞች እምብዛም እምነት አልነበረኝም፡፡
አቶ ለማን ግን አመንኩ፡፡ ያኔ እስር፣ ወከባ ምናልባትም ሞት ሊያስከትሉ የሚችሉ ጽሑፎችን በተከታታይ መፃፍ ቀጠልኩ፡፡ ይህ ስሜት ደግሞ የኔ ብቻ አልነበረም፡፡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በስልክና በአካል ለአቶ ለማ ያቀረብኩትን ድጋፍ አስመልክተው አመሰገኑኝ፤ አቀፉኝ፣ ሳሙኝ፡፡
ኦቦ ለማና ኢህአዴግ ረዥሙን የሞት ሽረት ስብሰባ ሲያደርጉ፣ ለአራት ቀናት ያህል እየባነንኩ፣ እንቅልፍ ማጣቴን አስታውሳለሁ፡፡ ያ መባነን ደግሞ እንደዚያ የወደድኩት መሪዬ፣ አንዳች ነገር እንዳይሆኑብኝ ከመስጋት ነበር፡፡ ለአቶ ለማ መገርሣ የሳሳሁትን ያህል ለማንም ሳስቼ አላውቅም፡፡ ለማ መገርሣ፤ በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይዞ እንደመጣ መሲህ፣ ህይወቱን ሊሠዋልኝ እንደተዘጋጀ አዳኝ የቆጠርኳቸው ሰው ናቸው፡፡ ቃላቸውን ቃሌ አድርጌ ድምፃቸው ሲጠፋ፣ አባቱ እንደናፈቀው ህፃን የቴሌቪዥን መስኮት እያየሁ ልቤ የመታላቸው መሪዬ ናቸው፡፡ እናም ክርስቶስ ነፍሱን የሰጣቸው ሃዋርያቱ፣ ነፍሳቸውን እንደሰጡት፣ ለእኒህ ሰው ነፍሴን ለመስጠት የተዘጋጀሁ ነበርኩ፡፡
እውነትም ለማ የሚናገሩት ንግግር መሬት ጠብ አይልም፣ አርትኦትም አያሻውም፡፡ የከበደ ሃሳብ፣ ዒላማው ላይ የሚያርፍ ትኩረትና ምርጫ የነበረው ነው፡፡ ስለዚህም ብዙዎቻችን የራሳችንን አካባቢና ምኞት ትተን፣ በፍቅር ተከትለናቸዋል፡፡
ይሁንና ሰሞኑን እኛ የጥያቄያችን ጠያቂ፣ የችግሮቻችን ፈቺ ያልናቸው የተከበሩ ሰው፤ “የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ” ብቻ ብለው ብቅ ሲሉ አዘንኩ፡፡ ምነው አቶ ለማ… እኛም’ኮ “የእኛ ጥያቄ መልስ ነዎት ብለን ተከትለንዎታል፡፡ ራስዎ የሰበኩንን ኢትዮጵያዊነት… ወደየት ጥለው፣ ኦሮሞን ብቻ ከኢትዮጵያ መዘዙ? እርግጥ ነው የኦዴፓ ምክትል ሊቀ መንበር ነዎት፤ ግን ደግሞ የለውጡ ፊታውራሪም ነበሩ፡፡” እያልኩ በልቤ ወቀስኳቸው፡፡
አንዳንድ ሰዎች ኦቦ ለማን እንደ አስመሳይ ወይም እንደ ይሁዳ የፈረጁበትን መንገድ ግን አልደግፍም፡፡ ለማ ይሁዳ አይደሉም፤ ይሁዳ ክርስቶስን የተከተለው በገንዘብ ያዢነቱ ገንዘብ ለመመንተፍ፣ በኋላም ጌታውን ለብር አሳልፎ ለመሸጥ ነው፡፡ ለማ ግን ሙሰኛም ሌባም አይደሉም፤ ምናልባት እንደ ጴጥሮስ የሆኑ ይመስለኛል፡፡ ወከባው በዛባቸው፣ ሠልፉ ጠነከረባቸው፣ ምድረበዳው አምታታቸው፡፡ አለዚያ ለማ ከህዝብ ኪስ ዘርፈው አያውቁም፤ በሥልጣናቸው ቀብጠው ህዝብን አላሳዘኑም፡፡ ስለዚህ ይሁዳ ሲባሉ ያምመኛል፤ አስመሳይም አይደሉም፤ ምክንያቱም አስመሳይ ነፍሱን አይሰጥም፡፡
አቶ ለማ በአምባገነኑ ወያኔ/ኢህአዴግ መንጋጋ ሥር ሆነው፣ የአንድነትን ባንዲራ ሲያውለበልቡ፣ የለውጡን ቀንዲል ሲለኩሱ፤ ሞት አፉን ከፍቶ እንደሚጠብቃቸው፣ መከራ በፉጨት ተጠራርቶ እንደሚከብባቸው ያውቃሉ፡፡ ይሁንና በዚያ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ለማ መገርሳ፤ ለእኔና ለሀገሬ ሰዎች ሌት ተቀን ነድደዋል፡፡ “እንተርፋለን” ብለው ሳይሆን “ሌሎችን እናተርፋለን” ብለው ወደሚነድደው እሣት ገብተዋል፡፡
ዛሬም ሆነ ትናንት፤ በጨለማው/በክፉው ጊዜ፣ ጥጋቸውን ይዘው፤ የራሳቸውን ቤት ዜማ ብቻ የሚያዜሙ፣ ሲላቸውም ከዘመኑ ሰዎች ጋር ተለጥፈው ሆዳቸውን ሲሞሉ የከረሙ ሰዎች፤ ሲዘልፏቸው መስማት ለኔና ለመሰሎቼ ህመም ነው፡፡ የቱንም ያህል ዛሬ ተሳሳቱ ብንል… ለማ ነፃ አውጪያችን ናቸው፡፡ ለማ የጨለማ ቀን ጧፍ ሆነው የነደዱልን ብርሃናችን ናቸው፡፡ ዛሬ እንደሚያገሳ አንበሣ ጥርሳቸው ተነቅሎ ድዳቸውን የሚነክሱብን ጨካኞች እንዳይውጡን፣ ጉሮሮዋቸውን መዝጋታቸውን አንረሣውም፡፡
እኔ ዛሬም በአቶ ለማ ተስፋ አልቆርጥም:: “ትንታጐቹ” የሚለውን መጽሐፌን ጽፌ ሳሳትምም፤ ዶክተር ዐቢይን በወቅቱ ከነበረው እሣት ለመቀነስ ብቻ ሳይሆን፣ አቶ ለማ መገርሣንም ታሪክ እንዲያስታውስ በማለት ነበር፡፡ የመጽሐፌ መግቢያ፤ ለማ መገርሣ መሆናቸውም፣ በጊዜ ውስጥ የከፈሉልን ውለታ እንዳይደበዝዝ በሚል ቅንዐት /Zeal/ ነበር፡፡
ከመጽሐፍ ባለፈ ብዙም ፍላጐቱ በሌለኝ ማህበራዊ ሚዲያ ሽንጤን ገትሬ ለመሟገት የገባሁት፣ ከእነ ኦቦ ለማ ጐን ለመቆም ነበር፡፡ ይህንንም ማድረጌ ለሌላ ሳይሆን የሚወዷትን ሀገሬን ስለምወድድ ነው፡፡ ሀገሬ ኢትዮጵያን ስወድድ ደግሞ፤ ዛሬ ጽንፈኞች ከእኛ ነጥለው የሚያዩትን የኦሮሞን ህዝብ ጭምር ነው፡፡ አሁን ከነጋ በኋላ ዋነኛ ሆነው “እኛ ብቻ ነን” የሚሉት የሥልጣን ጥመኞች፤ በአውሮፓና በአሜሪካ በርገር እየገመጡ፣ የኦሮሞ ወጣት ሲገደል ‹‹እኛንም ይግደሉን›› ብለን ጽፈናል፡፡ እኛ  ወንድሞቻቸው፡፡ ጽንፈኞቹ ለቁማራቸው ሊነጣጥሉን ቢመኙም፣ አማራና ኦሮሞ ወይም ትግራይና ሌላው ኢትዮጵያዊ የተዘነቅንና የተቀላቀልን፣ ክፉና ደግ አብረን ያሳለፍን ነንና… ወደፊትም አብሮነታችን መቀጠሉ አይቀሬ ነው:: ለዚህ ደግሞ የገጣሚ አበረ አያሌው ጥቂት ስንኞች ብዙ የሚናገሩ ይመስለኛል፡፡
ሰ….ፊ ነው ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው የስፋት ልኩ፤
ከፍቅር ባነሰ መዳፍ ለመቁረስ ጫፉን አትንኩ፡፡
አለው ስም፣ ግብር - ትንሳዔ በገፍ ያደለው፤
ዐፈር አራግፎ ይነሳል - “ተቀብሯል”፤ ሞቷል ስትለው::
ኢትዮጵያዊነትን የሚጠሉ ነሁላላዎች የሚያወሩትን ያህል፣ በሸረሪት ድር የታሠረ ሙትቻ ችቦ አይደለም - ኢትዮጵያዊነት! በጀግኖች አባቶቻችን ደምና አጥንት ተሠርቶ የፀና ሃይል እንጂ! ለዚህ ደግሞ በአድዋ፣ በማይጨውና በቅርቡ በነበሩ የጦር ግንባሮች የተከፈሉ መስዋዕትነቶች ምስክር ናቸው፡፡
ይህንን ሃቅ ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል ለማጥፋትና ለማጠልሸት ሺህ ጊዜ ሸፍጥ ቢሰራም፣ ይህንን ሸፍጥ ሰብረው ብቅ ለማለት ለማ መገርሳን የቀደመ አልነበረም፡፡ “ትንታጐቹ” በተሰኘው መጽሐፌ መግቢያ ላይ ያልኩትም ይህንኑ ነው፡፡ ለአብነት፡-
“ሀገር እንባ ለብሳ፣ ደም አሸርጣ የቆመች ያህል ቀፍፎን፣ ሙሾ ተጠግቶን ሳለ ነው - አቶ ለማ መገርሳ ከአጋሮቻቸው ጋር በሰማይ አድማስ እንደ ብርሃን ዘንግ ተወርውረው፤ ተስፋ የዘሩብን፡፡ ‹ኢትዮጵያ፣ አንድነት› የሚሉት ቃላት ለሃያ ሰባት ዐመታት ከተጣሉበት ተነስተው እንደገና አደባባይ ላይ ዘንባባ ተነስንሶ፣ በመዝሙር ቅኝት ሰማይ የነካ ክብር ያገኙት ያኔ ነው፡፡ የእኔም ልብ በደስታ ሲኮራ፣ ጉንጮቼን የፌሽታ እንባ የላሳቸው፤ “የጣና ጉዳይ ያገባናል” በሚል የኦሮሚያ ወጣቶች ከመሪዎቻቸው ጋር ባህርዳር የሄዱ ቀን ነበር፡፡ ከዚህ በላይ የምሥራች አልነበረም፡፡››
እንግዲህ አቶ ለማ መገርሳ፤ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ዘንድ ያላቸው ከበሬታና ፍቅር ይህን ያህል ነው፡፡ ምናልባትም እኔ መግለጽ ከምችለው በላይ የሚወደዱ፣ የሚከበሩና የሚታመኑ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሚዲያ የጠፉ ሰሞን ሰው ሁሉ “ለማ የት ጠፋ? ምን ሆነ? አመመው ይሆን?” እያለ የሚሳሳላቸው የሀገር ባንዲራ ናቸው፡፡ ታዲያ እንዴት ሆነው አቶ ለማ “የእናንተ ነገር አይመለከተኝም፤” አሉ? ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡
እኔ አንዳንዶች እንደሚሉት፤ የፓርቲዎቹ መዋሃድ ቦታ ያሳጣኛል ብለው ሰግተው አይመስለኝም፡፡ በኔ እምነት በይበልጥ ደግሞ ስለ ዶክተር ዐቢይ ፕሮፋይል ለመሥራት ያነጋገርኳቸው የቅርብና የሩቅ የተለያየ ብሔርና ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች የነገሩኝን ከሰማሁ በኋላ፣ በምንም ተዓምር ከልጅነት ጀምሮ የተሰራ በጐ ማንነትና ቅንነት፣ ድንገት ሊፈርስ ይችላል ብዬ አልጠረጥርም፡፡ በዚህም የተነሳ ለወንበር ይጋፋሉ ብዬም አላስብም፡፡
ምናልባት የቴሌቪዥን ጣቢያ ሳይቀር ከፍተው፣ ከተለያየ አቅጣጫ የተሰለፉ ጽንፈኞች፣ ወዳጅ መስለው የገቡ ሠርሣሪዎች፣ በሁለቱ መሪዎቻችን መካከል ጠብ ሊዘሩ እንደሞከሩ መጠርጠር አይከብደኝም፡፡ በቀጥታ ለውጡን ከሚያጣምሙ አክቲቪስቶች ያለፈ፣ በሃይማኖት ጭንብል፣ የዘር ፖለቲካ የሚያራምዱና የኢትዮጵያ አንድነት ደስታ የማይሰጣቸው ሰዎች እንዳሉ በሚሠሩት ሥራ እያየን ነው፡፡ ለአቅመ ጋዜጠኝነት ያልደረሱና ንባብ ያላያቸው ሳይቀሩ፣ ከጀርባቸው ሌላ ድምጽ እየቀዱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማቃለል ሲሞክሩ ስናይ አንዳች ደባ እንዳለ እንገምታለን፡፡
እንደ ማህተመ ጋንዲ፣ ከፍቅር በቀር ዱላና ጥይት የማይመኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩን፤ አበሳቸውን ያበዛውም እነዚህና መሰል ነገሮች ተደራርበው ይመስለኛል፡፡ የአማራ ጽንፈኞች - “ኦነግ” ሲሏቸው፣ የኦሮሞ ጽንፈኞች - እንደ ባንዳ እያዩዋቸው፤ እንባቸውን ውጠው በፅናት መቀጠላቸው ከእግዚአብሔር እርዳታ በስተቀር ምንም ሊሆን አይችልም፡፡
እንደ መጽሐፍ ቅዱሶቹ ዮናታንና ዳዊት ነፍሳቸው በፍቅር የታሠረችው ለማ መገርሳና ዐቢይ አህመድ፤ በቀላሉ ይፈታሉ ብለን ባናምንም፣ ዛሬም መለስ ብለው የሠፈሩን ወሬ ሳይሆን የሩቁን ታሪክ እንዲያጤኑ እንመኛለን፡፡  
በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት፣ የተገንጣዩ ወገን ቀንድና መሪ ሆኖ ለስድስት መቶ ሺህ ሰዎች ማለቅና ለአሜሪካ ኢኮኖሚ መድቀቅ ምክንያት የሆነው ጀኔራል ሮበርት፤ “የአሜሪካን አንድነት እየወደደ ነገር ግን በቨርጂኒያ ሰዎች ጠባብነት እንደተጠለፈው፤ የምወዳቸውና የማከብራቸው፣ እንደ ሀገሬም ባንዲራ የምቆጥራቸው ጀግናዬ ለማ መገርሳ እንዳይጠለፉና እንደ ጀኔራሉ ከእልቂትና ጥፋት በኋላ እንዳይፀፀቱ ምኞቴና ፀሎቴ ነው፡፡ ኦቦ ለማ መገርሣ፤ የምንወድዎትንና ልንሞትልዎት የተሠለፍነውን ሰዎችም አይርሱን!
ስለ አቶ ለማ መገርሳ ሳስብ ትዝ ያለኝ “ፍርድ እና እርድ” የግጥም መድበል ውስጥ ያለው ግጥም ነው፡፡ ምክንያቱም እኔና መሠሎቼ፣ በለማ መገርሳ ተስፋ አንቆርጥምና!
በ“ሆሳዕና” ዜማ ሰግደው የዘመሩ
“ስቀሉት” ይሉኛል ፈጣሪን ሳይፈሩ!
ፈጣሪስ ተነሳ - ገድለውት መች ቀረ
የጁን ፍጡር ግብር - በሞቱ ተማረ
ተሰቅሎ በሞተ - ተነስቶ በረረ፡፡
የኔም እምነት እንደዚያ ነው፡፡ ለማ መገርሳ ስተው ከሆነ እንደ ጴጥሮስ ይፀፀታሉ፡፡ የተሟገትንላቸውን ኢትዮጵያውያን ሀቅም አፈር አያስግጡም፡፡ የሃሳብ ልዩነታቸውን እናከብራለን፡፡ ግን የሚጠቅመንን ይመርጣሉ ብለን እንጠብቃለን! እንዲህም ሆኖ ለማ መገርሣ፤ የነፃነት ቀንዲላችን መሆናቸውን ፈጽሞ አንረሳም፡፡ መቼም!!



Read 4074 times