Saturday, 14 December 2019 12:07

“ዓለም አገሬን ሲያከብራት አይቼ በመመለሴ ደስ ብሎኛል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

  ኢትዮጵያ ከሰሞኑ የኦስሎ የኖቤል ሽልማት በኋላ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ የሚኖራት ቦታና ገጽታ በእጅጉ እንደሚቀየር አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡
በጠ/ሚሩ የኖቤል ሽልማቱ በውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተለያየ አግባብ ደስታቸውን የገለፁ ሲሆን ጠ/ሚሩ ይህን አስመልክቶ በማህበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በመላው አለም ተበትነው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዜግነት ክብራቸውን ከፍ የሚያደርግ ስራ በታሪክ ውስጥ ሲመዘገብ አዩ፣ ልጆቻቸውም በባዕድ አገር በታሪካቸው ኮሩ›› ብለዋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ አስደማሚ የተዋጣለት የኖቤል ሽልማት ንግግራቸውን ለመላው የዓለም ህዝብ አቅርበው የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማታቸውን የተቀበሉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤
በማህበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ማስታወሻ፤ ኦስሎ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እስክትመስል ድረስ በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማና በኢትዮጵያ ባነሮች ተውባ መሰንበቷን፣ ሚዲያዎች ሁሉ በኩራት ስለ ኢትዮጵያ  መመስከራቸውን፣ በድህነት በጦርነትና ረሃብ የሚያውቋት አገራችንን በሌላ አዲስ ታሪክ ለማወቅ እንደቻሉ በመግለጽ የአለም አይኖች ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ተተክለው እንደሰነበቱ ጽፈዋል፡፡
የሽልማቱ ስነ ሥርዓት የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭትም ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የአለም ሕዝብ እንደተከታተለው፤ ይህም ለኢትዮጵያ መልካም ገጽታ ግንባታ የማይተካ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
‹‹በመላው አለም ተበትነው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዜግነት ክብራቸውን ከፍ የሚያደርግ ስራ በታሪክ ውስጥ ሲመዘገብ አዩ:: ልጆቻቸው በባዕድ አገር በታሪካቸው ኮሩ:: አገራቸው በምሳሌነትና በአርአያነት ስትነሳ በአይናቸው ብሌን ተመለከቱ፤ ሰሙ፡፡  በአረብ አገር የሚኖሩ ዜጎቻችን አሰሪዎቻቸው ወደታች ሳይሆን ወደ ላይ እንዲያዩዋቸው የሚያደርግ ታሪክ በአለም አደባባይ ሲከወን እንባ በተሞሉ አይኖቻቸው አደነቁ›› ሲሉ ተርከዋል፡፡
‹‹በኦስሎ ያገኘነው ክብር የአገራችን ጉዞ ከትናንት የዛሬው፣ ከዛሬውም የነገው እጅግ የተሻለ መሆኑን አመላክቶናል፤ ይህ ለኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይሆንም፡፡ በሰላም በሳይንስ በሥነ ጽሑፍ ገና ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ኖቤል አገር ኖርዌይ ይመጣሉ›› ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ‹‹ዛሬ ያገኘነውን አክብረን፣ አያሌ ኢትዮጵያውያን በአለም አቀፍ መድረኮች አገራቸውን እንዲያስጠሩ እንሰራለን ለዚህ ደግሞ ሁላችንም አገር የሚያስጠራ ጥረት እናድርግ›› ሲሉ ጥሪያቸውንም አቅርበዋል፡፡
‹‹ፍቅርና ክብር የገባውን ሕዝብ ማገልገል ኩራትም ዕድልም ነው›› ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ አዲስ አበባ ሲደርሱ በተደረገላቸው አቀባበልም በእጅጉ መደሰታቸውን በመግለጽ ለህዝቡ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ‹‹አለም አገሬን ሲያከብራት አይቼ ወደ አገሬ በመመለሴ ደስ ብሎኛል›› ብለዋል - የኖቤል ተሸላሚው ጠ/ሚኒስትር፡፡
ከትናንት በስቲያ ማለዳ 12፡30 ቦሌ አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ ለሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ ሽልማቱ ለኢትዮጵያ፣ ለኤርትራና ለምስራቅ አፍሪካ ያለው ትርጉም ከፍተኛ ነው ብለዋል። ሽልማቱም የብዙ እናቶች ለቅሶና ፀሎት ውጤት መሆኑንም አልሸሸጉም፡፡ “ሽልማቱ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት እንደ መነሻ የምንገለገልበት ነው” ሲሉም የኖቤል ሽልማታቸው የወደፊት ቀጣይ ጥቅምም እንዳለው ተናግረዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ትውልድ የሚበላ ሾተላይ አለ፤ ይሄን ሾተላይ ማከም ያስፈልጋል›› ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ወደ መሰላል የሚወስድ ሥራ  ላይ ልጆቻችን ካሉ ጎትቶ ማውረድ ሳይሆን ገፍተን ጫፍ እንዲደርሱ ማድረግ ከሁላችን ይጠበቃል” ሲሉ መክረዋል፡። “ኢትዮጵያም የብዙ ጀግኖች አገር እንደ መሆኗ፣ ጀግኖቻችን ደግፈን ወደ መሰላሉ እናውጣ” ብለዋል በመልዕክታቸው።
በኖቤል ሽልማቱ ሥነ ሥርአት ላይ ባደረጉት ንግግር ደግሞ፤ ኢትዮጵያውያን የሰብዓዊነትን የመተባበር፣ የመደጋገፍ፣ የሰላም እሴት እንዳላቸው በመጥቀስ፤ አገሪቱን በመደመር እሳቤ ወደ ፊት ለማሻገር እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኖሪዌጂያን ኖቤል ኮሚቴ ሊቀ መንበር ቤሪት ራያሲስ አንደርሰን በሥነስርዓቱ ላይ ባቀረቡት ዘለግ ያለ ንግግር፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር ምንጭ ናት፤ የመጀመሪያው ሆሞ ሳፒያን ከዚያ ተነስቶ ነው አለምን የሞላው፡፡ ከዚህ አንጻር እኛ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ አገራችሁ ኢትዮጵያም በፍፁም በምዕራባውያን ቅኝ ያልተገዛች ነች፤ ከአፍሪካ የተለየ የራሷ ታሪክ አላት፤ በዚህ የተነሳ ነው የአፍሪካ ሕብረት መዲና የሆነችው›› ሲሉ ኢትዮጵያን የክብርና የኩራት ማማ ላይ ሰቅለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ሽልማቱን በተቀበሉባት ኖርዌይ ኦስሎ ከተማ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአደባባይ ደስታቸውን ሲገልፁ የሰነበቱ ሲሆን፤ በተለያዩ አለማት የሚገኙም በማህበራዊ ገፆቻቸውና በመገናኛ ብዙሃኃን ደስታቸውንና የኩራትና የክብር ስሜታቸውን አጋርተዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ ወደ ሀገር ውስጥ ከተመለሱበት ሰአት ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ ሐረር፣ ጅማ፣ ወላይታ ሶዶና በሌሎችም አካባቢዎች የደስታ መግለጫ ሠላማዊ ሠልፎች መካሄዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ታዋቂ ኢትዮጰያውያንና አንጋፋ ምሁራንም በሽልማቱ የተሰማቸውን ስሜት አጋርተዋል፡፡
የስነጽሑፍና ቋንቋ ምሁሩ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ “ዛሬ እንደ ሩዋጮቻችን በመሪያችን ተከበርን፣ ቀና አልን፣ “የፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መለኪያዎች ነን” የሚሉት አውሮፓውያን፤ በአንድ ድምጽ “አንተ ወደ ሰላምና ዲሞክራሲ የሚወስደውን መንገድ ለሀገርህ መርጠሃል” አንተ ዲሞክራሲያዊና ሠላማዊ ማህበረሰብ ልትገነባ ጉዞ ጀምረሃል የሚሉት መሪ አገኘን” ሲሉ ደስታቸውን በፌስቡክ ገፃቸው ገልፀዋል፡፡
“የጠቅላይ ሚኒስትራችን የኖቤል ሽልማት ለኢትዮጵያውያን የማንቂያ ደውል ነው” ያሉት ዶ/ር በድሉ፤ “ይህ ደውል በአለም ላይ ያለንን ቦታ ያሳየ ነው፤ ይህ ደውል የሚገባንን የሚመጥነንን ፖለቲካዊ አስተዳደር ጅምር ያመላከተ ነው፤ ይህ ደውል ከእውነት ጋር እንድንታረቅ የሽምግልና ድምጽ ነው፤ ይህ ደውል የ1990ዎቹ ከፋፋይ የሴራ ፖለቲካ መሞትን የሚያበስር የመርዶ ድምጽ ነው፤ ይህ ደወል የጀመርነው የለውጥ መንገድ ብቸኛ አማራጫችን እንደሆነና ተጋግዘን ለግብ ማብቃት እንዳለብን የሚያስገነዝብ ድምጽ ነው” ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው በትዊተር ገፃቸው ባሠፈሩት ሃሳብ፤ “ኢትዮጵያችንን ከፍታ ላይ አስቀምጠውልናል፤ እኛ ዜጐቿ በጣም ኮርተናል፤ በእጅጉ እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “አገራችንን ያደረሱበት ደረጃ ላይ ለማቆየትና ይበልጥም እንድትራመድ ሁላችንም ድርሻ አለን ብዙ ስራ ይጠበቅብናል፡፡ ቆርጠን ተባብረን እንነሳለን” በማለትም ጥሪ አቅርበዋል” - ፕሬዚዳንቷ፡፡
ጠ/ሚሩ ስለ ሰላም የተሸለሙትን የኖቤል ሽልማት ሜዳሊያና ዲፕሎማ በብሔራዊ ሙዚየም እንዲቀመጥ መወሰናቸውን ተከትሎ በነገው እለት ለብሄራዊ ሙዚየም ያስረክባሉ የተባለ ሲሆን ከሰሞኑ ወደ ኤርትራ በማቅናትም ከኤርትራ ሕዝብና ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ስኬቱን እንደሚያከብሩም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሜዳሊያና ዲፕሎማውን ለብሄራዊ ሙዚየም የሚያስረክቡት በቅርስነት እንዲቀመጥ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አንጋፋው ምሁርና የዕድሜ ባለፀጋው ፕ/ር መስፍን ወልደ ማሪያም በፌስቡክ ገፃቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡- ‹‹አፄ ኃይለስላሴ ከእነግርማ ሞገሳቸው ከዙፋናቸው ከወረዱ በኋላ የኢትዮጵያ ስም እንዲህ በገናናነት ተሰምቶ አያውቅም፤ የኢትዮጵያውያን ልብ በኩራት አበጥ ብሎ አያውቅም፤ ኢትዮጵያዊነት ቀና ብሎ አያውቅም፤ አሁን ሳየው ትልቁ ቁም ነገር፣ ዐቢይ ሽልማቱን መቀበሉ አልነበረም፤ ሽልማቱ ትልቅ ነገር ነው፤ ከዐቢይ ስም ጋር ተቆራኝቶ እንደሚቀርም እርግጥ ነው፤ ለእኔ ዋናው ቁም ነገር ሆኖ ያገኘሁት ሽልማቱ ምክንያት የሆነለት የዐቢይ ንግግር ነው፤ የዐቢይ ንግግር በእንግሊዝኛ ከመሆኑ ሌላ ድንቅ፣ ልብን የሚነካና ኢትዮጵያዊ ሰውነትን ተላብሰው ‹‹እኛም ኢትዮጵያውያን ነን›› አሰኛቸው፤ የኢትዮጵያን ሰብዓዊነት የኢትዮጵያን የመንፈስ ልዕልና፣ የኢትዮጵያውያንን የማስተዋል ቅርስ፣ የኢትዮጵያውያን የአዕምሮም ሆነ የመንፈስ ችሎታና ብቃት በሚገባ ለአለም በሙሉ አሳይቷል፤ ንግግሩን ያላዳመጡት የዐቢይን ሰውነትና የአዕምሮ ችሎታ መገንዘብ ያቅታቸዋል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ እግዚአብሔር ይባርክህ! መንገድህን ያቅናልህ››

Read 12141 times