Print this page
Saturday, 07 December 2019 12:55

የህልሜ መስተዋት

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(9 votes)

   መነሻ - ታሪክ
(የሳሙኤል ኮልሪጅ “በህልምህ የቀጠፍከውን አበባ፣ጠዋት እጅህ ላይ ብታገኘውስ--” የሚለው ግጥም)
ጠዋት ላይ ይመስለኛል - ከቁርስ በፊት:: ሥራ የለኝም፤ የእረፍት ቀን ነው፡፡ ቅዳሜ ወይም እሁድ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከተገዛች ብዙ ዓመታት ያስቆጠረች የእንጨት አልጋዬ ላይ ቁጭ ብያለሁ፤ እያሰብኩ፡፡ እኔ መስተዋቱ ፊት ልቀመጥ ወይም መስተዋቱ እኔ ፊት ይቀመጥ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በአንድ ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ያንን ዓይነት ትልቅ የፊት መስተዋት አይቼ አላውቅም፡፡ ፊቴን ብቻ ሳይሆን ልቤንም ጭምር እያሳየኝ ይመስለኛል፡፡ የልብ መስተዋት አይታችሁ ታውቃላችሁ?
በመስታወቱ ጭብጥ የምታህለው ልቤ፤ ንጥር ንጥር ስትል፣ በመስታወቱ አየኋትና፣ ነገረ ስራዋ አሳቀኝ፡፡ እኔ ብስቅባትም፤ እሷ ግን ከመጤፍ የቆጠረችኝ  አትመስልም፡፡ ዝም ብላ ትዘላለች፡፡ የተፈጥሮ ሥራዋን አክብራ እየሰራች ነው፡፡ እሷ ጋ መዝናናት የለም፡፡ አትልም እንጂ፣ ልዝናና ያለች ቀን፤ እኔ ቀጥ እላለሁ፡፡
ድንገት መስተዋቱ ላይ ባየሁት ነገር ክፉኛ ደነገጥኩኝ፡፡ ፊቴም ልቤም የሉም:: በምትካቸው የፍቅረኛዬ ፊት ጉብ ብሏል - በሌለችበት፡፡ የምወድላት ክብ ፊቷ፤ ፊት ለፊቴ  ይታየኛል - በመስተዋቱ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ የት ነው ያለሁት? ቀስ ብዬ ዙሪያ - ገባውን  ቃኘሁ፡፡ እዚያችው የተከራየኋት ጠባቧ ክፍሌ ውስጥ ነኝ፡፡ ሁሉም ነገር እንዳለ ነው - ግድግዳው ላይ የተሰቀለውን የፍቅረኛዬን ፎቶግራፍ ጨምሮ፡፡ ዓይኔን ወደ መስተዋቱ መለስኩ፡፡ አሁን ደግሞ የፍቅረኛዬ ክብ ፊት የለም፡፡ በቦታው የእኔ ቅርጽ የለሽ ፊት ተተክቷል፡፡
“ዘባራቂ መስተዋት?!” አልኩና ወደተለመደው  ሃሳቤን የማመንዠክ ሥራ ገባሁ:: አሮጊቷ እናቴ፣ ፍቅረኛዬን ካየቻት ጀምሮ አንድ ክፉ አመል አምጥታለች፡፡ “ውለዱ እንጂ!”፣ “አታስረግዛትም እንዴ?” ትለኛለች - በወጣሁ በገባሁ ቁጥር፡፡
ውትወታዋ ሲበዛብኝ እኔው ራሴ አርግዤላት ቁጭ አልኩኝ - ልጅ ሳይሆን ሃሳብ፡፡ የአብራኬን ሳይሆን የጭንቀቴን ክፋይ አረገዝኩላት፡፡ ደስታ ራቀኝ፡፡ በጭንቀት ሰለልኩ፡፡ ወልደው የማይገላገሉት ሃሳብ ጤናዬን  ቀማኝ፡፡ ሁለመናዬ በጥፋተኝነት ስሜት ተሞላ፡፡ ተስፋና ደስታ ራቀኝ፡፡
 “ደስታ ለምን ከእኔ ራቀ?!” ስል ጮህኩኝ - ወደ  ትልቁ መስተዋት እያየሁ፡፡ የእኔ ያረጀ ፊት መስተዋቱ ውስጥ ጉብ ብሏል፡፡  ተጠራጥሬ ትክ ብዬ አየሁት፡፡ የእኔን  ይመስላል እንጂ የእኔ ፊት አይደለም፡፡ እኔ የ35 ዓመት ጐልማሳ! መስተዋቱ ውስጥ ያለው የ75 ዓመት  አዛውንት፡፡ “ቅዠት ነው?” አልኩኝ በሆዴ፡፡ “እውነት ነው!” አለኝ ፊት ለፊቴ የሚታየኝ አዛውንት ፊት፡፡ ደንግጬ ሳፈጥበት፣ ደንግጦ አቀረቀረ - በመስተዋቱ የሚታየው ሽማግሌ ፊት፡፡
“ምንድነህ? ከየት መጣህ?” አልኩኝ አፍጥጬ - ወደ መስተዋቱ እያየሁ፡፡
“የወደፊት ትዝታ አትፈልግም?” አለኝ፡፡
 አሁን ገባኝ፡፡ ሳረጅ ምን እንደምመስል እያሳየኝ ነው - የእኔን ፊት የሚመስለው ሽማግሌ ፊት፡፡ እኔ ግን ለጊዜው፣ የወደፊት ትዝታዬ አላስጨነቀኝም፡፡ እኔን ያስጨነቀኝ፣ አሁን ደስታዬን መነጠቄ ነው፡፡ እኔን ያስጨነቀኝ፣ አሁን ያረገዝኩት ሃሳብ ነው፡፡
“ደስታዬን ለምን ተቀማሁ?” አልኩኝ፤ ለሽማግሌው ሳይሆን ለራሴ፡፡ ቀና ብዬ መስተዋቱን ስመለከት ባዶ ነው፤ ምንም  የለም::  ባዶ ነው፡፡ ከተፈጠርኩ ባዶ መስተዋት አይቼ አላውቅም፡፡ የት ገባ የሰውየው ፊት?  ሽማግሌው የት ተሰወረ? ለአፍታ በሃሳብ ተዋጥኩኝ፡፡
“ይቅርታ ለውሃ ሽንት ሄጄ ነው” ድምፁን የሰማሁት ከመስተዋቱ ውስጥ ነው፡፡ ቀና ስል ሽማግሌውን ፊት አየሁት፡፡ የወደፊት ትዝታዬን::
“ሰምቼሃለሁ” አለኝ መስተዋቱ ውስጥ ጉብ ያለው ፊት፤ “ደስታህን ማንም አልቀማህም”
“ጅል ሽማግሌ!” አልኩ በልቤ፡፡ የሰማኝ አልመሰለኝም፡፡
“ታስሮ እኮ ነው -  ደስታህን አስረኸዋል!”  አለኝ ሽማግሌው ፊት፡፡ የሚያሾፍብኝ መስሎኝ ነበር፡፡ ግን ፊቱ ላይ ሹፈት አይታይም፡፡
“የት ነው ያሰርኩት?” ከጥያቄ ይልቅ ግራ መጋባቴን የሚያስተጋባ ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡
“ልብህ ጓሮ!” መለሰልኝ ሽማግሌው፡፡ ዝም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡
“ተረጋግተህ አስብ…ወደ ውስጥህ ተመልከት” አከለ ሽማግሌው
ለእንዲህ ዓይነቱ እልህ አስጨራሽ ምክር፣ ቅንጣት ትዕግስት እንደሌለኝ ልነግረው ፈለግሁ::
“የእኔ ወንድም  ቅኔ አልፈልግም …በግልጽ ተናገር” አልኩት
“አትማረር! ገና ልጅ እኮ ነህ”
“የሚያጽናናኝም አልፈልግም” በቁጣ መለስኩ
“ማረጋጋቴ እንጂ ማጽናናቴ አይደለም” አለ ተረጋግቶ፡፡
“ሙግትም አልሻም፤ መልሱን ብቻ”
“ኧረ ሽማግሌ አይሟገትም” አለኝ በሚያሳዝን ቅላፄ፡፡
በመሃላችን ለአፍታ ዝምታ ነገሰ፡፡ ቀና ብዬ መስተዋቱን ተመለከትኩ፡፡ ሰውየው ለመናገር አፉን ሲያሞጠሙጥ አየሁት፡፡
“ልብህ ሁለት ቦታ ደም ቋጥሯል”
ይሄ ሽማግሌ ምናባቱ ነው የሚዘባርቀው ስል - አሰብኩ፡፡
“አልዘባረቅኩም፤ ከልቤ ነው”
ቢቸግረኝ ማሰብ ተውኩ፡፡ እንደ ቅድሙ መስተዋት አዕምሮዬን ባዶ አደረኩት፡፡ ሃሳብ አልባ አዕምሮ፡፡
“የተቋጠረውን ደም ፍታው” አለኝ ሽማግሌው፤ የምክር ቃና ባዘለ ድምፅ፡፡
“እንዴት?” ሳላስበው ከአፌ ያፈተለከ ጥያቄ ነው፡፡
“በረከቶችህን ቁጠራቸው!” አለኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈገግ ብሎ፡፡
 የምን በረከት እንደሚያወራ አልገባኝም፡፡
አዕምሮዬን ከሃሳብ ነፃ ማውጣት ስለፈለኩኝ ዝም አልኩት፡፡ ዝም ሲባል አዕምሮ ባዶ ይሆናል የሚል ሳይንሳዊ ጥናት ባይኖርም፣ ለዛሬ ሰርቶልኛል፡፡ ሽማግሌው መዘባረቁን ቀጠለ፡፡
ያው እኔም ሳረጅ እንዲሁ ልዘባርቅ አይደል! የወደፊቱ እኔ እኮ ነኝ፣ መስተዋቱ ውስጥ የምታየው፡፡ የ75 ዓመቱ አዛውንት እኔ፡፡ ሰውን በምክር የማሰለቸው እኔ፣ ቅጂ ነው አሁን የሚያወራኝ፡፡
“ከራስህ ጋር አውራ! ከልብህ ጋር ተማከር … ያኔ የምናብህን አበባ ታገኛለህ”
የመጽሐፍ ጥቅስ የተናገረ ነው የመሰለኝ፡፡ አባባሉን በአዕምሮዬ እያብሰለሰልኩ ቆየሁና፣ ገርሞኝ ወደ መስተዋቱ ተመለከትኩ፡፡
መስተዋቱ በተለያዩ የጽጌረዳ አበቦች ተሞልቷል፡፡ ቀይ፣ ሮዝ፣ ነጭ፣ ሐምራዊ…ገና ያልፈነዱ፣ በከፊል የፈነዱ፣ ሙሉ በሙሉ የፈነዱ … ደሳስ የሚሉ የአበባ ቤተሰቦች፡፡
ለምን እንደሆነ እንጃ አበቦቹ ፍቅረኛዬን አስታወሱኝ፡፡ አንድ ንብ አበቦቹ ላይ እየተፈናጠረች ቆይታ --- ከመስተዋቱ ወጣችና ከንፈሬ ላይ አረፈች፡፡ በድንጋጤ እየተርበደበድኩ፣ ከከንፈሬ ላይ ላላቅቃት ሞከርኩ፡፡
“እንቅልፋም” አለችኝ - ንቧ ሳትሆን ከጐኔ የተጋደመችው ፍቅረኛዬ፡፡ ከእንቅልፌ ነቅቼ በደንብ አየኋት፡፡
በህልሜ መስተዋት እንዳየኋቸው ውብ አበቦች ፈክታለች፡፡ ደምቃለች፡፡
 “የምስራች ልንገርህ!?” አለችኝ፤ ልብ በሚሰረስር ጣፋጭ ድምጽ፡፡
“ደስ ይለኛል” አልኳት - በጉጉት፡፡
ከንፈሯን ለዓመል ያህል ከንፈሬ ላይ አሳረፈችና፤ “አርግዤአለሁ” አለችኝ፡፡
ያረገዝኩትን ሃሳብ የተገላገልኩ መሰለኝ፡፡
***
ውድ አንባብያን፡- ከላይ ያነበባችሁት ሸጋ ድርሰት፤ ባለፉት ዓመታት በአዲስ አድማስ ላይ ከታተሙ አጭር ልብወለዶች መካከል ተመርጦ በድጋሚ የወጣ ነው፡፡ በሚቀጥለው ታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ የምናከብረውን የጋዜጣውን 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ፣ ምርጥ ጽሁፎችን እየመረጥን ደግመን በማውጣት፣ ያለፉትን 20 ዓመታት በጨረፍታ ማስታወሳችንን እንቀጥላለን፡፡ ያለፉትን ዓመታት አብራችሁን ስለተጓዛችሁ፣ ወደፊትም አብራችሁን ስለምትጓዙ ልባዊ ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡


Read 3270 times