Print this page
Monday, 09 December 2019 00:00

የወባ በሽታ ባለፈው አመት 405 ሺህ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  በ2018 በመላው አለም 228 ሚሊዮን ሰዎች በወባ ተጠቅተዋል

          ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ በመላው አለም 228 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውንና ከእነዚህም መካከል 405 ሺህ የሚሆኑት ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
በአመቱ በአለማቀፍ ደረጃ በወባ ከተጠቁት ሰዎች መካከል ከ93 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወይም 213 ሚሊዮን ያህሉ አፍሪካውያን መሆናቸውንና በመላው አለም በበሽታው ከተጠቁት ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአምስት የአፍሪካ አገራት ማለትም፡- የናይጀሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኡጋንዳ፣ ኮትዲቯር፣ ሞዛምቢክና ኒጀር ዜጎች መሆናቸውንም ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የወባ በሽታ ክስተት ባለፉት አስር አመታት በአለማቀፍ ደረጃ መቀነሱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአመቱ በበሽታው ሳቢያ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥርም ከአንድ አመት በፊት ከነበረው 416 ሺህ ወደ 405 ሺህ ዝቅ ማለቱንም አስረድቷል፡፡ በአመቱ በከፍተኛ ሁኔታ በበሽታው ከተጠቁት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከአምስት አመት ዕድሜ በታች የሚገኙ ህጻናት ቀዳሚነቱን እንደሚይዙ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ለሞት ከተዳረጉት መካከልም 67 በመቶው ወይም 272 ሺህ ያህሉ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናት መሆናቸውን ገልጧል፡፡
በአመቱ ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በወባ በሽታ የተጠቁባት አገር ናይጀሪያ መሆኗንና በአለማችን በበሽታው ምክንያት ከሞቱ ሰዎች መካከል ሩብ ያህሉ ናይጀሪያውያን እንዲሁም 11 በመቶው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ 5 በመቶው የታንዛኒያ ዜጎች መሆናቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ በአለማቀፍ ደረጃ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመንግስታትና በአለማቀፍ ለጋሾች 2.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያህል ገንዘብ ወጪ መደረጉን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ባለፉት ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ 578 ያህል በኬሚካል የተነከሩ አጎበሮች ለተለያዩ አገራት መሰራጨታቸውንም አስታውሷል፡፡


Read 7941 times
Administrator

Latest from Administrator