Sunday, 08 December 2019 00:00

የአለም “የትያትር ኦሎምፒክ” በሩስያ ተጀምሯል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የአለም “የትያትር ኦሎምፒክ” እየተባለ የሚጠራውና በየአራት አመቱ በተመረጡ የአለማችን ከተሞች የሚካሄደው አለማቀፉ የትያትር ፌስቲቫል በሩስያዋ ከተማ ሴንት ፒተርስበርግ እየተከናወነ እንደሚገኝ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
ቻይና፣ ቤልጂየም፣ ፖላንድ፣ ጣሊያን፣ ህንድና ፈረንሳይን ጨምሮ 22 የተለያዩ የአለማችን አገራት በሚሳተፉበት የዘንድሮው የአለም “የትያትር ኦሎምፒክ”፤ በድምሩ 104 ትያትሮች ለእይታ የሚበቁ ሲሆን፣ ከእነዚህ ትያትሮች መካከል 78 የሚሆኑት በሩስያ የተዘጋጁ እንደሆኑም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ፌስቲቫሉ ምንም እንኳን የአለም “የትያትር ኦሎምፒክ”  የሚል ስያሜ ቢሰጠውም፣ በአገራት የሚዘጋጁ ትያትሮችን ለእይታ በማብቃት በኪነጥበብ አማካይነት ባህልን፣ ታሪክንና ማንነትን በማንጸባረቅ ትስስርን ከማጎልበትና በባለሙያዎች መካከል ልምድ ከመለዋወጥ ባለፈ በውድድር መልክ ሽልማት የሚሰጥበት አለመሆኑ ተነግሯል፡፡
ለ25ኛ ጊዜ በሩስያ በመከናወን ላይ የሚገኘውና የተለያዩ ዓለማቀፍ ታዋቂ የትያትር አዘጋጆችና ተዋንያን እየተሳተፉበት ያለው የ2019 የአለም “የትያትር ኦሎምፒክ”፤ በመጪው ሳምንት መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 የተጀመረው የአለም “የትያትር ኦሎምፒክ”፤ ከዚህ ቀደምም ቻይና፣ ግሪክ፣ ጃፓን፣ ቱርክና ደቡብ ኮርያን ጨምሮ በተለያዩ የአለማችን አገራት ከተሞች በስኬታማ ሁኔታ መከናወኑንም ዘገባው አስታውሷል፡፡  

Read 2219 times