Saturday, 07 December 2019 12:45

ሙሴቬኒ “ዕድሜዬን ሙሉ አንድም ነገር ሰርቄ አላውቅም” አሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ሙጋቤ በባንክ ያላቸውን 10 ሚ. ዶላር ጨምሮ ሃብታቸውን ሳይናዘዙ መሞታቸው ተነገረ

                      የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዮሪ ሙሴቬኒ፤ ዕድሜ ዘመናቸውን ሲኖሩ፣ ከማንም ሰው ምንም ነገር ሰርቀው እንደማያውቁ ሰሞኑን ለአገራቸው ህዝብ በአደባባይ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
ሙሴቬኒ ባለፈው እሁድ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኡጋንዳውያን ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት በመዲናዋ ካምፓላ በተከናወነ የጸረ-ሙስና የእግር ጉዞ ላይ ከተሳተፉ በኋላ ለህዝቡ ባደረጉት ንግግር፣ “በህይወት ዘመኔ ምንም ነገር ሰርቄ አላውቅም፤ ስላልሰረቅኩ ግን ድሃ አልሆንኩም!” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
“ሙሰኞች ጥገኛ ተዋህሲያን ናቸው፤ ምክንያቱም የራሳቸው ያልሆነ ሃብት ነው የሚያፈሩት፡፡ መንግስታችን ሙሰኞችን ለመዋጋት ቆርጦ ተነስቷልና ህዝባችን ከጎኑ እንዲቆም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ” ብለዋል ሙሴቬኒ፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ በቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ የግል የባንክ ሂሳብ ውስጥ 10 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ዚምባቡዌን ለ37 አመታት ያህል አንቀጥቅጠው የገዙትና ባለፈው መስከረም ወር በ95 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ሙጋቤ፤ በባንክ ያስቀመጡትን 10 ሚሊዮን ዶላር፣ አራት መኖሪያ ቤቶችን፣ አስር መኪኖችንና አንድ ግዙፍ እርሻ ጨምሮ ሃብታቸውን ለማንም ሳይናዘዙ ማለፋቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ ህግ መሰረት አንድ ሰው ሃብቱን ማን እንደሚወርሰው ሳይናዘዝ ከሞተ ለትዳር አጋሩና ልጆቹ እንደሚከፋፈል የጠቆመው ዘገባው፤ የሙጋቤን ሃብትም ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤና አራት ልጆቻቸው ይወርሱታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡


Read 2415 times