Saturday, 07 December 2019 12:22

‹‹ከህወሐት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለንም››

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

     - ዓላማችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ነው
           - ኦነግ የሚታገለው ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ነው
           - ውህደቱ አሃዳዊነትን ያመጣል የሚለውን አንቀበለውም

             በቅርቡ በምርጫ ቦርድ በአገራዊ ፓርቲነት መመዝገቡን ያስታወቀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፤ ከህወሐት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለኝም ይላል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ከሰሞኑ በኢሕአዴግ ውህደትና በመደመር እሳቤ ላይ ባነሱት ተቃውሞና በኦሮሞ ፖለቲካ ላይ ስላለው አንደምታ፣ ህወኃት ከሰሞኑ ከ‹‹ፌደራሊስት ሃይሎች›› ጋር ስላደረገው ጉባኤ እንዲሁም በወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የኦነግ ከፍተኛ አመራር አቶ ቶሌራ አዳባ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

              በቅርቡ ኦነግ፤ ‹‹አብረን እንስራ›› የሚል ጥሪ በአገሪቱ ለሚገኙ የፖለቲካ ሃይሎች አቅርቧል፡፡ ድርጅታችሁ ይህን የትብብር ጥሪ በዚህ ወቅት ያቀረበበትን ምክንያት ሊነግሩን ይችላሉ?  
በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና ውጥረቶች እያየሉ መምጣታቸው በእጅጉ አሳስቦናል፡፡ እነዚህ ውጥረቶች ሊረግቡ የሚችሉት ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ተቀራርበው ሲሰሩና ሲወያዩ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ ድርጅቶች ተቀራርበው መስራታቸው በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ ችግር እንዲጠብ ይረዳል፤ የዴሞክራሲ ግንባታ እንዲፋጠንና የበለጠ ግልጽ እንዲሆን ያደርጋል:: የፓርቲዎች ተቀራርቦ መስራት በሕዝቡ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያስችላል… በሚል አላማ ነው ጥሪውን ያቀረብነው፡፡
ጥሪያችሁ ምላሽ እያገኘ ነው?
እስካሁን ወደኛ የመጣ የለም፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ አሁንም አሳሳቢ በሆነው የአገሪቱ ጉዳይ ላይ ተቀራርበው እንዲሰሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ይሄ ለኛ አዲስ አቋም አይደለም፡፡ ከሌሎች ጋር ያሉንን ግንኙነቶች የበለጠ ለማዳበር በማሰብ ነው ጥሪ ያቀረብነው::
ኦነግ፤ አገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ መመዝገቡን ይፋ አድርጓል። ለቀጣዩ ምርጫ ዝግጅት ጀምራችኋል?
እኛ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት፣ ምርጫ ወሳኝ መሆኑን በማመን ሰፊ እንቅስቃሴ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ የእውቅና ወረቀት ከማግኘታችን በፊትም ጥሩ ተወዳዳሪ ለመሆን በማሰብ፣ በየቦታው ባሉ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ዝግጅት ስናደርግ ነው የቆየነው:: ወረቀቱን ካገኘን ወዲህ ደግሞ በተሻለ ሁኔታ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ጽ/ቤቶችም የከፈትንባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡
ክልላዊ የነበረው ኦነግ እንዴት አገር አቀፍ ፓርቲ ሊሆን ቻለ?
እኛ ግንባር ቀደም አላማችን፣ ‹‹አገሩ በኛ ስር ይተዳደር›› የሚል ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ነው፡፡ ለዚህም ፓርቲያችን በአገሪቱ የትኛውም አካባቢ የመንቀሳቀስ መብት አለው፡፡ አንድ ድርጅት ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ መንቀሳቀስ የሚችለው፣ ከተቋቋመበት ክልል ውጭ ባሉ አካባቢዎች የድጋፍ ፊርማ ሲያሰባስብ ነው፡፡ እኛም በዚህ መንገድ ከኦሮሚያ ውጪ ድጋፍ ያገኘንባቸው አካባቢዎች  አሉ ማለት ነው፡፡
ከኦሮሚያ ውጭ የምትንቀሳቀሱባቸውን አካባቢዎች ሊጠቅሱልን ይችላሉ?
የአማራ ክልል፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ሃረሪ፣ ድሬደዋና ፊንፊኔን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች እንንቀሳቀሳለን፡፡ ደቡብ አካባቢም ከሕዝብ ጋር እየተገናኘን ውይይት እያደረግን ነው። ከሌሎች የክልል ድርጅቶች ጋርም ተቀራርቦ ለመስራት በውይይት ላይ ነው ያለነው፡፡
ከሰሞኑ የኦዴፓ ም/ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ ‹‹መደመርና የብልጽግና ፓርቲን አላምንበትም›› ብለዋል፡፡ ይሄ አቋማቸው በኦሮሞ ፖለቲካ ላይ ምን አንደምታ ይኖረዋል?
አቶ ለማ መገርሳ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው የለውጥ ሁኔታ እንዲፈጠር ከታገሉ ሃይሎች ወይም የኢሕአዴግ አመራሮች መካከል ዋነኛው ናቸው፡፡ እሳቸው ብቻም ሳይሆኑ በስማቸው  ‹‹ቲም ለማ›› እየተባሉ ሲጠሩ የነበሩ አሉ፡፡ እሳቸው እንደ ግንባር ቀደም መሪ የሚታዩ ሰው ናቸው። በአሮሞ  ሕዝብ ዘንድም ትልቅ ቦታ ያላቸው ናቸው፡፡
ሁኔታው አስቸጋሪ በነበረ ወቅት ወደፊት ወጥተው፣ የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ መስማትና መመለስ አለብን ያሉ መሪ እንደሆኑ ይታወቃል:: በዚህም እሳቸውን የሚደግፉ ሃይሎች አሉ፡፡ ይሄ በኦዴፓ አመራሮች መካከል የሚፈጥረው ጫና ይኖራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ችግሩ ሳይሰፋ ከወዲሁ ተነጋግረው መፍትሄ ቢያበጁለት መልካም ነው፡፡ አሁን የበለጠ ተቀራርቦ መስራት የሚያስፈልግበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ተቀራርበው እንዲሰሩ እመክራቸዋለሁ፡፡
የአቶ ለማ የተለየ አቋም መያዝ በኦሮሞ ፖለቲካ ላይ የተለየ ሚና ይኖረው ይሆን?
እንደምንሰማው፤ በአቶ ለማና በሌሎች መካከል ያለው ልዩነት የውህደቱ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ የሰጠንን አደራ በቅድሚያ ልንመልሳቸው ይገባል›› ከሚል ነው:: ጉዳዩ በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለውና ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ያልተመለሱለት ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?
ይሄ ምንም ግራ የሚያጋባ ነገር የለውም፤ ጥያቄው ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲመጣ፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ እንዲሁም የህዝቦች መብት የሚጠበቅባት፤ ሁሉም በእኩልነትና በነፃነት የሚኖርባት ኢትዮጵያን መፍጠር የሚል ነው - ጥያቄው፡፡
ታዲያ እነዚህ ጥያቄዎች በተለየ መልኩ እንዴት የኦሮሞ ሕዝብ ይሆናሉ? ሁሉም ሕዝብ የሚፈልገው አይደለም እንዴ?
ብዙዎች ነገሩን አጣመው ነው የሚረዱት፡፡ እኛ ይሄን ስንል፣ ጥያቄው የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ነው እያልን አይደለም፡፡ ኦነግም የሚታገለው ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መብት ነው፡፡  ዲሞክራሲያዊት የሆነች ኢትዮጵያ ትገንባ ሲባል እኮ፣ ሁሉም ባለ መብት የሆነባት ኢትዮጵያ ትገንባ ማለት ነው፡፡
አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የለውጥ ሃይል ለጥያቄው ምላሽ እየሰጠ አይደለም ብላችሁ ታምናላችሁ?
አሁን ያለው መንግስት እኮ ገና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እገነባለሁ እያለ ያለ ነው እንጂ ‹‹ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ተገንብቷል፤ የሕዝቦች ጥያቄ ተመልሷል›› አላለም፡፡ ገና የወደፊቷን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንገነባለን ነው እየተባለ ያለው፡፡ በዚያ ሂደት ውስጥ ነው የኦሮሞም ሆነ የሌላው ሕዝብ ጥያቄ አልተመለሰም የሚል አቋም ያለን፡፡
ጥያቄው እንዴት ነው የሚመለሰው ትላላችሁ?
ዋነኛው ሕዝቡ የኔ ነው የሚለውን መንግሥት በምርጫ ማቋቋም ሲቻል ነው፡፡ የሁሉንም ሕዝብ ወኪሎች ያቀፈ መንግሥት በምርጫ ሲመሠረት ነው ጥያቄዎቹ መልስ ሊያገኙ የሚችለው እንጂ አሁን በተያዘው የጥገና አካሄድ ብቻ አይደለም፡፡
የኢህአዴግን ውህደት ኦነግ እንዴት ይመለከተዋል?  
እነዚህ ፓርቲዎች በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያስገኝልናል እስካሉ ድረስ መዋሀዳቸው የእነሱ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ ኦነግ ውህደቱን የሚያየው የራሳቸው ጉዳይ አድርጎ ነው፤ መብታቸው ነው፡፡
ውህደቱ አሃዳዊነት የሚያመጣ ነው በሚል የሚቃወሙ ወገኖች አሉ፡፡ በናንተ በኩል ምን አስተያየት አላችሁ?
በኦነግ አቋም፤ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው ሥርዓትን የመሰለ አሃዳዊ ሥርዓት የለም፡፡  ለስም ፌደራላዊ ሥርዓት ተባለ እንጂ እውነተኛና ትክክለኛ የሆነ ፌደራላዊ ሥርዓት አልነበረም፤ የአሃዳዊነት መልክ የነበረው ነው:: ሥርዓቱ የአንድን ቡድን የበላይነት ያረጋገጠ፤ አሃዳዊ ሥርዓት ነበር፡፡ ሕዝቦች ይወክለኛል ብለው በመረጡት ሲመሩ ብቻ ነው ትክክለኛ ፌደራሊዝም ሊገነባ የሚችለው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ግን ካለውም የሕዝቦች ንቃተ ሁኔታ ከአሁን በኋላ የአንድን ቡድን ጥቅም የሚያስከብር ሌሎችን የሚጨቁን አንድ ቡድን ወይም ፓርቲ ለማስተናገድ አይፈቅድም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥነ ልቦናና የደረሰበት የንቃት ደረጃ፣ ለ27 ዓመት እንደነበረው፣ የአንድ ቡድን የበላይ የሆነበትን ሥርዓት ለማስተናገድ ዝግጁ አይደለም፡፡ ከእንግዲህ አሃዳዊነት የሚመጣበት እድል የለም፤ ቢመጣም ወዲያው ተሸናፊ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የኢሕአዴግ ውህደት አሃዳዊነትን ያመጣል የሚለውን እኛ አንቀበለውም፡፡
ምዕራብ ወለጋ አካባቢ ግጭትና ውጥረቱ አልረገበም…?
ኦነግ እንግዲህ በአካባቢው ታጥቆ ከሚንቀሳቀሰው ቡድን ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው በይፋ አስታውቋል፡፡ ሆኖም በዚያ አካባቢ ግጭቶች እየተከሰቱ፣ የሰው ሕይወት እየጠፋ ነው፡፡ ሁኔታው እንዲለወጥና እንዲረጋጋ ኦነግ፣ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመቀራረብ መፍትሄ በመሻት ላይ ይገኛል፡፡ ችግሩ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት መፍትሄ ያገኛል የሚል እምነት አለን፡፡ ግን የሃይል እርምጃ መፍትሄ እንደማይሆን፣ መንግስትም ያመነበት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ በመመርኮዝ፣ መፍትሄ ለመስጠት ተስፋ ሰጪ ሙከራዎች እያደረግን ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ቀጣዩን ምርጫ ማድረግ  ይቻላል ይላሉ?
አንዳንድ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ለምርጫ መቀስቀስ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይሄ ሊፈታ የሚችል ችግር ነው፡፡ ዋናው መንግሥት ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ቁርጠኛ አቋም መያዙ ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ደጋግሞ እየገለፀ ነው፡፡ ኦነግ ይሄን በማመን ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡ ከአቅም በላይ የሆኑ ሁኔታዎች እስካልተፈጠሩ ድረስ ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካለ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፤ መራዘም ሊኖርበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ነገሮችን የማስተካከል ሚና ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም፤ ሁሉም ድርጅቶችና ሕዝቡም ጭምር መሳተፍ አለበት:: ሕዝቡ አካባቢውን የተረጋጋ ለማድረግ መጣር አለበት፡፡
ሕወሐት ‹‹ሃገር ማዳን›› በሚል መርህ ሰሞኑን ‹‹የፌደራሊስት ሃይሎች›› ከሚላቸው ጋር በመቀሌ ጉባኤ አድርጓል፡፡ ኦነግ በዚህ ጉባኤ ላይ ተሳትፏል?
በፍጹም አልተሳተፍንም፡፡ ልንሳተፍም አንችልም፡፡
ለምን?
እኛ ባለፉት 27 አመታት፣ ህወኃትን ለመጣል ስንታገል  የነበረን ድርጅት ነን:: በዚያ 27 አመታት ውስጥ ብዙ የተገደሉ፣ የተሰቃዩ… ታፍነው የት እንደገቡ የማይታወቁ የኦሮሞ ታጋዮች  አሉ፡፡ ህወኃት ብዙ ጉዳቶችን በሕዝባችንና በድርጅታችን ላይ አድርሷል:: ይሄን ጉዳይ አንድ መቋጫ ላይ ሳናደርስ ወደ ፖለቲካ ውይይት አንገባም፡፡ ስለዚህ እኛ ከህወሐት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለንም:: ለወደፊትም በሕዝባችን ላይ የደረሱት በደሎች ፍትህ ሳያገኙ፣ ምንም ዓይነት ግንኙነት አይኖረንም፡፡  


Read 12378 times