Saturday, 07 December 2019 00:00

ሞገደኝነት፣ ፌዘኝነት እና አድር - ባይነት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የለውጥ ሐሳብን የምንቀበልበት መንገድ ከሦስት አንዱን ሳንካዎች የያዘ ነው፡፡ የመጀመሪያው “ሞገደኝነት” ሲሆን ይህም ሁሉንም የለውጥ ሐሳብ ላለመቀበል ሰበብ መደርደርና ለመዋጥ መቸገር ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ “ፌዘኝነት” ሲሆን፤ ይኸም ትላልቅ የለውጥ ሐሳቦችን ሁሉ ለቀልድና ለቧልት እያዋሉ ከቁም ነገራቸው ይልቅ ቀልዳቸው እንዲበዛ ማድረግ ነው፡፡ ነገሮችን በነጠረ ዐይን አይቶ ከማሰላሰል ይልቅ ነገሩን ዋዛና ፈዛዛ አድርጐ ማለፍ ነው፡፡ ፌዘኝነት በብዙ መልኩ ከሞገደኝነት ጋር የተያያዘ ወይም የሞገደኝነት ውጤት ነው:: ሦስተኛው ደግሞ “አድር ባይነት” ሲሆን ከለውጥ ሐሳቡ ይልቅ ለግለሰቡ በማበር ሳይገባን ለመቀበልና ለማስረዳት መሯሯጥና በዚህም የባሰ ጥፋት ማድረስ ነው፡፡ በለውጥና ስኬት ውስጥ ሀገርና ሕዝብ እንዲጠቀሙ ሳይሆን ከለውጡ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበውን ፍርፋሪ ለመልቀም ማቶስቶስን፣ እያወደሱ፣ እያንቆለጳጳሱና የተለወጡ እየመለሱ የግል ጥቅምን ማሳደድን ይመለከታል፡፡
“ሞገደኝነት”የምንለው አዲስ ነገርን ለመቀበል የምናሳየውን ልግመትና እምቢታ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መሪዎች ከሌሎች ሀገራት የተማሩትን ጠቃሚ ነገር ወደ ሀገራችን ለማስገባት እጅግ ይቸገራሉ፡፡ ይኸም ብቻ ሳይሆን መሪዎቹ ራሳቸው አዲስ ነገር ለመቀበል ልግመኝነት ሲያሳዩም ይስተዋላል፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አዘምናለሁ ብለው ሲነሱ የገጠማቸው አንዱ ፈተናም ይኼ ነው፡፡ ከአዲሱ ሐሳብ ጋር ተገናዝቦ ለውጣቸውን ከማፋጠንና ጉድለቱን ሞልቶ የተሻለ እንዲሆን ከማገዝ ይልቅ ብዙዎች ዳር ቆመው እንደ እብድ ያዩዋቸው ነበር፡፡
አዲስ ነገርን ለመቀበል በምናሳየው “ሞገደኝነት” ምክንያት የመሪዎች ሕልም ወደ ሕዝቡ ዘልቆ ለመግባት ዕንቅፋት ይበዛበታል:: በዚህም ምክንያት አዲስ ሐሳብ ይዘው የሚመጡ መሪዎች ከሕዝባቸው ሞገደኝነት ጋር መጋጨታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ይኼኔ ሕልማቸውን ለማስፈፀም ሲሉ ከሞገደኞች ጋር ግብግብ ይገጥማሉ፡፡
ብዙ ጊዜ መሪዎችን ገዢ የሚያደርጋቸው ዋና ምክንያት የሕልማቸው ከፋት ሳይሆን ሕልማቸውን ለማስፈፀም ከጥበብና ከብልሃት ይልቅ ጉልበት መጠቀማቸው ነው፡፡
ጉልበትን መጠቀም ቀላሉና አእምሮን የማይጠይቀው ዘዴ ነው፡፡ ሕዝብን አሳምኖና በጐ ተጽእኖ ፈጥሮ መምራት ግን እጅግ ፈታኝና ጥበብን የሚጠይቅ መንገድ ነው፡፡
መሪዎች ቀላሉን መንገድ በመምረጥ ሕልማቸውን ለማስፈፀም በሚያደርጉት መውተርተር ውስጥ ሕልማቸውን ማስፈፀም ቀርቶ የነበረንን እንኳን እንድናጣ እየሆንን ጉዟችን ወደኋላ ሆኗል፡፡
“ፌዘኝነት” በሌላ በኩል ቁም ነገሮችን ሁሉ ወደ ቧልት በመቀየር ሐሳቦቹ ተገቢውን ዋጋ እንዳያገኙ ማድረግ ነው፡፡ እንደ ማኅበረሰብ ካሉብን ችግሮች አንዱ ሊያንገበግበን፣ ሊያስቆጨንና ሊያብሰለስለን በሚገባው ሁሉ ላይ ፌዝና ቧልት እየተረክን እንደማሽላው እያረርን መሳቃችን ነው፡፡ በሂደት የጉዳዩ አሳሳቢነት ቀርቶ ስለጉዳዩ እንቶኔ የቀለደው ቀልድ እየገነነ፤ ከችግራችን መፍትሔ ሳይሆን ቀልድ እንፈጥራለን፡፡
አንድ አዲስ ሐሳብ ያነሣ ሰው ሐሳቡን ከፌዝና ከቧልት መጠበቅ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ለቁም ነገር የተባለው ሐሳብ ለቀልድ ውሎ ባክኖ ይቀራል፡፡ ቀልድ ጭቆናን ለመቋቋም የሚያገለግል ነገር ነው፡፡ ብዙ በጭቆና ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች የጭቆናቸውን ሕመም የሚቋቋሙትና ኑሯቸውን የሚያስቀጥሉት ራሳቸውን በቀልድ እየደለሉ ነው፡፡ ነገር ግን ቀልድ ሰዎች ጭቆናን በሥርዓት ታግለው እንዳያሸንፉ ጊዜያዊ መደለያ ስለሚሆናቸው በሽታውን ከማዳን ይልቅ ሕመሙን የማስታገሻ መንገድ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ጭቆናን የማስቀጠል ሚና ይኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንም ለረጅም ዘመን በጭቆና ውስጥ በመኖራችን ምክንያት የጭቆናን ሕመም የምንደልልበት የቀልድ ልማድ አዳብረናል:: በርግጥ ቀልድ ጭቆናን ከመደለል ባሻገር ለገዢዎች መራራውን እውነት አዋዝቶ ለማቅረብ ይጠቅማል፡፡ ነገር ግን በቀልድ የቀረበን ነገር ከቁም ነገር ቆጥረው መፍትሔ የሚሰጡ ገዢዎች ከስንት አንድ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ቀልድ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ መግባት ሲጀምርና ከቁም ነገር ጋር የሚለያቸውን ድንበር አልፎ ሲሄድ ጭቆናንም ሆነ ማንኛውንም ስህተት ለማረም ዕድል ይነፍጋል:: ትልልቅ ሐሳቦችን ያጫጫል፡፡
የፌዘኝነት ልማድ የሰዎችን ሐሳብ ዕድገት ሲገድል ነው የኖረው፡፡ በተለየ መንገድ ለማሰብ የሞከሩ የሀገራችን ሰዎች ቀልደኞች ተደርገው ሲቆጠሩ ኖረዋል፡፡
ሰዎች ሞክሮ መሳሳትንና አዲስ ነገር መጀመርን ይፈሩታል፡፡ ይሳቅብናል፤ መሳቂያ መሳለቂያ እንሆናለን፤ እናፍራለን፤ የሀገር መተረቻ እንሆናለን ብለው ይፈራሉ፡፡ በቁም ነገር ወስዶ ከማበረታታትና ከማረም ይልቅ በነገሩ ላይ ማፌዝ ስለሚመረጥ ከመናገር ዝምታ፣ ከመሥራት እጅ ማጣጠፍ፣ ከመሞከር መቆጠብ፣ ከመጀመር መከተል እንዲመረጥ አድርጐታል፡፡
ሦስተኛው ሳንካ “አድር ባይነት” ለውጥን የሚፈትነው ሌላኛው የአስተሳሰብ ጽንፍ ነው:: አድር ባይነት የመሪዎችን ሕልም ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ ሳያላምጡ የመዋጥ ችግር ነው፡፡ አድር ባዮች ሕልሙን ሳያላምጡ ስለሚውጡት የሕልሙን ጣዕም አያውቁትም፡፡ የተነገራቸውን ሁሉ “እሽ” ብለው የሚቀበሉና “አቤት ወዴት” የሚሉ በመሆናቸው በገዢዎች ዘንድ ተወዳጅና ተመራጭ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን አድርባ ባይነት ሕልምን ለማሳካት የሚጫወተው ሚና በአመዛኙ አሉታዊ ነው፡፡ መሪዎች ሕልማቸውን ከልቡ ተጋርቶ ያንን እውን ለማድረግ የሚደመርና ሕልሙ ላይ ችግር ሲኖርም ያንን ችግር ለመናገር፣ ከመሪዎችም ጋር ለመወያየትና ለመከራከር ወደኋላ የማይል ተከታይ ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡ በሀገራችን ይህ የአድር ባይነት አስተሳሰብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት የሕዝብን ድጋፍና ተቃውሞ መለየት እስኪሳነን ድረስ ደርሶ ነበር፡፡ አድር ባይነት የጋራ ግብን አስቀምጦ ለመንቀሳቀስ ትልቅ ዕንቅፋት የሆነብን ችግር ነው፡፡
በፖለቲካውም ሆነ በሕዝብ አገልግሎት አመራር ሂደት ውስጥ አድር ባይነት ትልቅ በሽታችን ነው፡፡ በፖለቲካው መስክ አድር ባይነት በሕዝብ ዘንድ ሲሠርጽ በሕዝብና በመሪ መካከል የሐሳብ ግብይት አይኖርም፤ ቢኖርም ጤናማ አይሆንም፡፡ ይኸም ማለት በአንድ ሀገር ፖለቲካ ውስጥ መንግሥት የሕዝብን ድምጽና ትክክለኛ ፍላጐት ማወቅ የሚችልበት መንገድ አይኖርም ማለት ነው፡፡ በዚህም መንግሥት የሕዝብን ሐሳብ ሳይገዛ የራሱን ሕልም ለመሸጥ የሚሞክርበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ ያ ደግሞ ለፖለቲካ ቀውስ ይዳርጋል፡፡ መንግሥት የሕዝብን ፍላጐት ማወቅ የሚችለው ምክንያታዊ የሆነ የሐሳብ ልውውጥ በመሪና ተመሪ መካከል ሲካሄድ ነው፡፡ ድጋፉንም ሆነ ተቃውሞውን በግልጽ መመርመርና ለውጥ ማምጣት የሚቻለው አድር ባይነቱ ሲቀር ነው:: በሕዝብ አገልግሎት ሥራዎች ላይም መሪዎች በአድርባይ ሠራተኞች ስለሚከበቡና ከሞገደኞች ለመራቅ ሲሉ ከአድር ባዮች ጋር የጫጉላ ሽርሽር ውስጥ ይገባሉ፡፡
አድርባ ባዮቹ ለተቋማት ስኬትና ለሕዝብ ጥቅም ከመጣር ይልቅ መሪዎቻቸውን በማስደሰት ጥቅም ለማግኘት ይጥራሉ:: በተቋማት ውስጥም ለሕዝብ ከመቆምና ለተቋሙ ራዕይ ስኬት ከመረባረብ ይልቅ አለቃን ለማስደሰት ሲባል የመኩነስነስ ባሕርይ ይሰፍናል፡፡
ሞገደኞች፤ ፌዘኞች እና አድርባዮች ወደ ምክንያታዊ ተከታይነት እስካልተለወጡ ድረስ ማንኛውም በጐ ሕልም በእነዚህ አስተሳሰቦች ምክንያት በቶሎ ይመክናል፡፡ ይህ ሲባል ግን ሞገደኝነትም ሆነ አድር ባይነት የሕዝብ ወይም የተመሪ ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ በመሪዎችም ላይ የሚስተዋሉ ጉዳዮች መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
መሪዎች ከሕዝብ የሚነሳን ወይም ከተመሪዎቻቸው የሚሰነዘርን ተቃውሞና ሐሳብ እንደ አስፈላጊነቱ የሚቀበሉ ካልሆኑ ራሳቸው ሞገደኛ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይኸም መሪነት የሚያስፈልገውን የጋራ ሕልምን ትቶ የራሱን የመሪውን ሕልም ብቻ ይዞ ስለሚጓዝ መሪውን ከመሪነት ወደ ገዥነት ይቀይረዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝብን ሐሳብና ፍላጐት እያነጠሩ ከመውሰድ ይልቅ ሳያላምጡ የሚውጡ ከሆነ “ሕዝበኝነት” ያጠቃቸዋል:: ሕዝበኝነት የመሪዎች አድር ባይነት ነው፡፡ መሪዎች የሕዝብን ስሜታዊ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ የሕልም እንጀራ የሚጋግሩበት መንገድ ነው፡፡ አመክንዮአዊ በሆነ መንገድ እንደማይሳካ፣ ትክክልም እንዳልሆነ እያወቁ የሕዝብን ስሜታዊ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ግን የማይሆነውን ይሆናል ይላሉ፡፡ ከዘላቂ ዓላማ ይልቅ ጊዜያዊ ነጠብጣቦችን ይመርጣሉ፡፡
የምክንያታዊነት ጉድለታችን ሕይወት የሰጣቸው የሞገደኝነት፤ የፌዘኝነትና የአድር ባይነት ችግሮች ምክንያታዊነት እየጐለበተ ሲሄድ እንደሚቀረፉ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያታዊነት ሲጐለብት ተነጋግሮ ለመግባባት የሚያስችል ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና ይኖራል:: ይህ ሲሆንም በብቸኝነትን ጉድለት ውስጥ እየበሰበሱ ከመምጣት ወጥቶ ወደ ከሱትነት ለማምራት ይቻላል፡፡
(“መደመር” ከዶ/ር ዐቢይ አህመድ
መፅሐፍ የተወሰደ)

Read 2045 times