Saturday, 07 December 2019 12:13

የኢህአፓ ታጋዩ ቆይታ - ከአዲስ አድማስ ጋር

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

   - ‹‹የአሲምባ ታሪክ የትግሉ ሰማዕታት ሃውልት ነው››
             - “የአሲምባ ፍቅር” የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዛሬ ማታ ይካሄዳል

     በትግራይ ክልል አጋሜ አውራጃ ተወልደው፣ በኢህአፓ የትጥቅ ትግል ወቅት (በ1970ዎቹ)  አሲምባ ላይ ትግሉን በመቀላቀል ከሶስት ዓመታት የሞት ሽረት ትግል በኋላ በሱዳን በኩል ወደ አሜሪካ አቅንተው ኑሮአቸውን በአሜሪካ ኮሎራዶ አድርገዋል - “የሲምባ ፍቅር” መጽሐፍ ደራሲ ካህሣይ አብርሃ ወይም በትግል ስማቸው አማኑኤል ማንጁስ፡፡  መጽሐፉ የኢህአፓን የትግል ታሪክ ከአሲምባ ተራራ እስከ ተከዜ በረሃ፣ ከዋግሕምራ እስከ ራያ፣ ከወልዲያ እስከ በጌምድር ድረስ የሚተርክ ሲሆን፣ በርካታ ፀሐፍት ሸፋፍነው የሚያልፉትን የትግሉን ወቅት የፍቅር ታሪኮችንም ያስቃኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት “የአሲምባ ፍቅር” የተሰኘውን መጽሐፍ ወደ ፊልም ለመቀየር እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን የመጽሐፉ ደራሲም ለዚሁ ዓላማ ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ጥቂት ሳምንታት አስቆጥረዋል፡፡ ከመጽሐፉ ደራሲና ከቀድሞው የኢህአፓ ታጋይ ካህሣይ አብርሃ ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሣዬ አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች፡፡

            “የአሲምባ ፍቅር” እንዴት ተፃፈ? መጽሐፉንስ ለመፃፍ ምን አነሳሳዎት?
በህይወቴ ውስጥ ያለፉ በትጥቅ ትግሉ ውስጥ አብረውኝ የነበሩ ጓዶቼን ሁልጊዜም አስታውሳቸዋለሁ፡፡ መስዋዕትነትን ከፍለው ለነፃነት ሲታገሉ የኖሩና ያለፉ ጓዶቼን በህሊናዬ ሳላስታውሳቸው ውዬ አድሬ አላውቅም:: የነዚህ ጓዶቼ ታሪክ ግን የሚበቃውን ያህል እየተነገረ አለመሆኑ ይቆጨኛል፡፡ እነሱ አልፈዋል፡፡ እኔ በህይወት ያለሁት ግን ይህንን ታሪክ ጽፎ ለትውልድ ለማቆየት መስራት የለብኝም ወይ እያልኩ አስብ ነበር፡፡ ስለዚህም ራሴ በታሪኩ ውስጥ ያለፍኩ ሰው እንደመሆኔ፣ ከቤቴ ወጥቼ አሲምባ እስከደረስኩበት ጊዜ ድረስ ያሳለፍኩትን ውጣ ውረድ፣ በእጄ የጨበጥኩትን በእግሬ የረገጥኩትን እውነተኛ ታሪክ ብቻ ጽፌ ለትግል ጓዶቼ መታሰቢያ ለማድረግ ነው የፃፍኩት፡፡
የመጽሐፉን ርዕስ “የአሲምባ ፍቅር” ለምን አልከው?
ለኢህአፓ የትጥቅ ትግል መሰረቱ አሲምባ ነው፡፡ አሲምባ ለኢህአፓ ታጋዮች “ውስጣችን” ነው፡፡ በምንም ሁኔታና ከህሊናችን የማይወጣ ትልቅ ታሪካችን ነው፡፡ ስለዚህም “የአሲምባ ፍቅር” እኔም ለትግሉ፣ ለኢህአፓ ጓዶቼና ለአገሬ ያለኝን ፍቅር የገለጽኩበት መጽሐፌ በመሆኑ ነው ይህን ርዕስ የመረጥኩት፡፡
በመጽሃፍዎ ላይ ትግሉ የተነሳችሁለትን ዓላማ ስቶ እንደነበር የገለፁበት ሁኔታ አለ፡፡ ምን ማለትዎ ነው?
እንደ እኔ አይነቱ አፍላ ወጣት፣ ወደ ትግሉ ስንቀላቀል ይዘን የገባነው ወኔ ብቻ ነበር፡፡ ሞትን ፈጽሞ አንፈራም ነበር፡፡ ለመስዋዕትነት ዝግጁ ነበርን፡፡ ግን ሁኔታዎች ባሰብነው መንገድ አልሄዱልንም፡፡ የሃሳብ ልዩነቱ ከላይ ጀመረና እስከ ታች ደረሰ፡፡ ድርጅቱም ለሦስት ተከፈለ:: በዚህ አጋጣሚ መግለጽ የምፈልገው ሁለቱም ቡድኖች ሊታመኑ የሚችሉ፣ ለመስዋዕትነት ዝግጁ የነበሩ ሞት የማይፈሩ ነበሩ፡፡ እንደ ኢህአፓ ለመስዋዕትነት ቆራጥ የሆኑ ወጣቶችን ያሳባሰበ ድርጅት አልነበረም፡፡ ግን የሃሳብ ልዩነቶች በመፈጠራቸውና አንድ ሆነው ሊያታግሉን ባለመቻላቸው ተበታተንን፡፡
“በትግሉ ወቅት ያልተማሩ የኢህአፓ አባላት ይናቁ” ነበር ብለዋል?
በሠራዊቱ ውስጥ የነበረው አብዛኛው አባል የተማረ ወገን ነው፡፡ ገበሬውን በብዛት አላሳተፍንም ነበር፡፡
አንዱ ስህተታችንም ይኸው ነው፡፡ ገበሬው ሊሳተፍ እየፈለገም አላስገባነውም፡፡ ድርጅቱ በብዛት የሚንቀሳቀሰው በከተማ አካባቢ ስለነበር፣ በርካታ ወጣቶች ወደ አሲምባ መጥተው ነበር፡፡ ያን ጊዜም እዛ በቆየውና ከዚህ በሄደው የድርጅቱ አባላት መካከል ትንሽ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ እኔ ከ11ኛ ክፍል ነበር ትምህርቴን አቋርጬ ወደ ትግሉ የተቀላቀልኩት፤ እናም በግሌም የደረሰብኝን ነገር ነበር፡፡ ከዚያ በመነሳት ነው በመጽሐፉ ውስጥ ይህንን እውነት የፃፍኩት፡፡
ከትግል ጓዶችዎ ጋር በህይወት የመገናኘት ዕድሉን አግኝተው ያውቃሉ?
አዎ፡፡ አብረውኝ ከነበሩ ጓዶች ጋር አሁን በህይወት ለመገናኘት የቻልን ጓዶች አሉኝ:: በወቅቱ ስለበረው ነገር… ስለ ታሪካችን እናወራለን፣ እንወያያለን፤ የሃሳብ ልዩነቶች ቢኖሩብንም  ኢህአፓ የነበረ ሰው ልቡ አንድ ነው፡፡ ፍቅሩ እንዳለ ነው፡፡ አንዱን አሳልፎ አይሰጥም፡፡ መስዋዕትነትን አይፈራም፡፡ አሁንም ድረስ ልቡ ያው ነው፡፡
በትግሉ ወቅት “ይሄ ነገር ባይከሰት ኖሮ” ብለው የሚፀፀቱበት ጉዳይ አለ?
አዎ፡፡ አመራሩ ባይከፋፈል ኖሮ፡፡ የሃሳብ ልዩነቶች ባይፈጠሩ ኖሮ፣ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ ፈተው ሁሉም በአንድ መስመር ገብተው ቢያታግሉን ኖሮ… እንዲህ አንበታተንም ነበር፡፡ ትግሉ ይቀጥል ነበር፡፡ እኔም በህይወት አልቆይም ነበር፡፡ የትግላችን ዓላማ ግን ከግቡ ይደርስ ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡
“የአሲምባ ፍቅር” ከትግል ታሪክ በዘለለ የፍቅር ታሪክም አለው…
አዎ መጽሐፉ የተወደደበት ዋንኛው ምክንያትም ይኸው ይመስለኛል፡፡ ምንም የደበቅኩት ነገር የለም፡፡ ሁሉም ነገር በግልጽ በመጽሐፉ ላይ ሰፍሯል፡፡ ፍቅር በድርጅቱ ህግ ያስቀጣ ነበር፡፡ ፍቅር የራሱ ሂደት ስላለው ጊዜና ሁኔታን ይፈልጋል፡፡ የነበርንበት ሁኔታ ደግሞ ለዚህ አመቺ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ፍቅር በህግ የተከለከለ ነበር፡፡ ግን ደግሞ ተፈጥሮ ነውና፤ ሰዎች ነንና እንደዚህ አይነት ነገር አንዳንድ ጊዜ ሊፈጠር ይችላል:: ብዙ ፀሐፊዎች ግን ይህንን ታሪክ ሊጽፉት አይፈልጉም:: ይዘሉታል፤ ይደብቁታል፡፡ እኔ ግን መፃፍ አለበት ብዬ ስላመንኩኝ ፃፍኩት፡፡ እኔ በትግሉ ላይ ያገኘኋትን ድል ላይን፣ አገኛታለሁ ብዬ አልነበረም ወደ ትግል የገባሁት፡፡ እሷም እንደዚያው፤ ግን ታሪክ አገናኘን፡፡
ከድል ላይ ጋር ከትግል በኋላ ተገናኛችሁ?
አልተገናኘንም፡፡ ድል ላይ እዚያው ትግል ላይ ተሰውታለች፡፡ ታዲያ ያንን ታሪክ እንዴት ሳልጽፍ ልዝለለው፡፡ በትግልና በፍቅር መሃል ሆነሽ ልታስተናግጂው የማትችይው ፍቅር ገጥሞሽ፣ ይህንን በዓይነህሊና ውስጥ ተቀርፆ የሚቀር ታላቅ ትዝታ፣ በፍፁም ልዋሸውም ላስቀረውም ባለመቻሌ በመጽሐፌ ውስጥ አካትቼዋለሁ፡፡
መጽሐፉ ምን ያህል ተቀባይነትን አግኝቷል?
መጽሐፉ በብዛት ተነቧል፡፡ ሦስት ጊዜ ነው ያሳተምነው፡፡ ግን እኛ በማናውቀው መንገድም ታትሞ ብዙ ተሸጧል፡፡ በፒዲኤፍም ተሰራጭቷል፡፡ በመጽሐፉ ላይ ከአምስት ሺ በላይ “አርቲክል” ተጽፎበታል፡፡ 17 ሚሊዮን ሰው ተነጋግሮበታል፡፡ ይህ በጐግል ላይ በግልጽ የሚገኝ መረጃ ነው፡፡
አሁን መጽሐፉን ወደ ፊልም ለመቀየር እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ሃሳቡ እንዴት መጣ?
በርካታ አንባብያንና የስነጽሑፍ ባለሙያዎች መጽሐፉን ካነበቡ በኋላ የተለያዩ አስተያየቶችን ይሰጡኝ ነበር፡፡ ብዙ የስነጽሑፍ ባለሙያዎች “መጽሐፍህ በጣም አስተማሪ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ወጣቱ ከማንበብ ይልቅ ወደ ዲጂታል መረጃዎች መሄድን እያዘወተረ  በመሆኑ የመጽሐፉ ታሪክ ወደ ፊልም ቢቀየር፣ በርካታ ወጣቶች ፊልሙን በማየት ታሪካቸውን ማወቅና ከታሪካቸው መማር ይችላሉ” እያሉ አበረታቱኝ፤ እናም መጽሐፉ ወደ ፊልም ተቀይሮ እንዲሠራ ውሣኔ ላይ ደረስኩ፡፡
የፊልሙ በጀት ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ምን ያህል ነው? ገንዘቡስ ከየት ያገኛል?
አዎ፤ በጀቱ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ፊልሙ የሚሰራው እዚያው ታሪኩ በተፈፀመበት ቦታ ላይ በመሆኑ ነው፡፡ ከአሲምባ ተራራ ጀምሮ ላስታ፣ ጠለምት፣ ራስ ዳሽን፣ ወዲያ እግሬ በረገጠበት ቦታ ሁሉ ይሄዳል፡፡ ታሪኩ የድርጅቱ ሌጋሲ ስለሆነ ከተሰራ በደንብ መሰራት ይኖርበታል፡፡ በርካታ ተዋንያንም ይሳተፉበታል፡፡ ለፊልሙ ስራ የተያዘው በጀት 8 ሚሊዮን ብር ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሹ ወይም 4 ሚሊዮን የሚሆነው የሚሸፈነው በእኔ ነው፡፡ ቀሪውን በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች ለማግኘት ነው ዕቅዳችን፡፡ የዚሁ ፕሮግራም አካል የሆነው የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ፕሮግራም፣ ዛሬ በኤልያና ሆቴል ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል:: ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት የገቢ ማሰባሰቢያ ከሰራን በኋላ ወደ ቀረፃ እንገባለን፡፡
አራት ሚሊየን ብር ማሰባሰብ ትንሽ ከበድ አይልም?
እኔ ድሮ አሲምባ ላይ መሰዋት የነበረብኝ ሰው ነኝ፡፡ አሁን የምኖረው ሁለተኛ ህይወት ነው፡፡ ይህ ፊልም በትግሉ ወቅት የተሰዉት ጓዶቼ መታሰቢያ ሃውልት ነው፡፡ በህይወቴ ውስጥ ማድረግ የምመኘውም ይህ ነው፡፡
አማኑኤል ማንጁስ የተባሉበትን ታሪክ ይንገሩኝና በዚሁ እንሰነባበት…
ወደ ትግል ስገባ ስሜን መቀየር እንዳለብኝ አላውቅም ነበር፡፡ ወደ ስፍራው ስደርስ “ከአሁን በኋላ ካህሣይ የሚለው ስምህ አይሰራም፤ ሌላ ስም ምረጥና በእሱ እንጥራህ” አሉኝ፡፡ ከየት እንደመጣልኝ አላውቅም፤ ብቻ አማኑኤል አልኩኝ፡፡ በቃ ይኸው ስም ስሜ ሆኖ ቀረ፡፡ ማንሣስ ማለት ደግሞ በኤርትራ ቋንቋ ትንሽ ማለት ነው፡፡ እኔ በወቅቱ እዚያ ከነበሩት ትንሹ ስለነበርኩ ነው ማንጂስ ብለው ስም ያወጡልኝ:: በኋላ ግን እነዚያ ጓዶች ፍልስጥኤም ውስጥ ሲሰለጥኑ፣ አሰልጣኛቸው ስሙ አማኑኤል ይባል ስለነበር፣ ስሜን በጣም ይወዱት እንደነበር ነግረውኛል፡፡  

Read 1789 times