Print this page
Saturday, 07 December 2019 12:07

ልቀት የጥበባትና የቢዝነስ ኮሌጅ በድግሪ ፕሮግራሞች እውቅና አገኘ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

      ለ52 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሰራተኞችና ለበጎ ፈቃደኞች ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጥቷል

            በተመሰረተ በአንድ ዓመት ውስጥ ከፍተኛ እመርታ ያሳየው ‹‹ልቀት›› የኪነ ጥበባትና የቢዝነስ ኮሌጅ በአካውንቲንግና ፋይናንስ እንዲሁም በማኔጅመንት የትምህርት ዘርፎች በድግሪ ፕሮግራም ለማስተማር ከከፍተኛ ትምህርትና አግባብነት ኤጀንሲ እውቅና ማግኘቱን ኮሌጁ አስታወቀ፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ለመሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ ለሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት፣  ለአቢሲኒያ ሕጻናትና ሴቶች አካል ጉዳተኞች መረጃ፣ ለዘውዲቱ ሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ለመቄዶኒያ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ለእያንዳንዳቸው የሁለት ሁለት ሰው በድግሪ ፕሮግራም ነፃ የትምህርት እድል የሰጠ ሲሆን በከንቲባ ጽ/ቤት ይመራ ለነበረው የክረምት የበጎ ፈቃደኞች ቡድን ለ40ዎቹ ከደረጃ 1-4 ባሉና በኮሌጁ በሚሰጡ የትምህርት አይነቶች ለሁለቱ የድግሪ ፕሮግራም በአጠቃላይ ለ52 ሰዎች ነፃ የትምህርት እድል መስጠቱን አስታውቋል፡፡ የኮሌጁ ሀላፊዎች በኮሌጁ አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የ5ቱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሃላፊዎች ኮሌጁ ነፃ የትምህርት እድል መስጠቱን የሚገልጽ ሰነድ ከአርቲስት ዳንኤል ተገኝ እጅ ተቀብለው ለኮሌጁ ያላቸውን ምስጋናና አድናቆት ገልጸዋል፡፡ ኮሌጁ ባለፈው ዓመት ሲመሰረትና ስራ ሲጀምር 40 ለሚሆኑ ከፍለው መማር ለማይችሉ ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጥቶ የነበረ ሲሆን መስፈርቱን አሟልተውና ከቀበሌያቸው መክፈል እንደማይችሉ ደብዳቤ አጽፈው የመጡትን 20 ተማሪዎች ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት በአካውንቲንግ ፋይናንስና በማኔጅመንት በድግሪ በአካውንቲንግና በፊልም ሜኪንግ ከደረጃ 1-4 እያስተማረ ሲሆን በቪዲዮ ሜኪንግ፣ በቪዲዮ ካሜራ፣ በግራፊክስ ዲዛይንና አኒሜሽን እንዲሁም በቪዲዮ ኤዲቲንግ ዘርፍ አጫጭርና መካከለኛ ኮርሶችን በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡

Read 2038 times