Saturday, 07 December 2019 12:00

ታዋቂው ድምጻዊ ኤኮን በሴኔጋል የራሱን ከተማ እየገነባ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ብራድ ፒት ላለፉት 20 አመታት አልቅሶ እንደማያውቅ ተናገረ

           ታዋቂው ድምጻዊ ኤኮን በትውልድ አገሩ ሴኔጋል በስሙ የምትሰየም የራሱን አዲስ ከተማ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ፣ ዝነኛው የሆሊውድ ተዋናይ ብራድ ፒት ደግሞ ላለፉት 20 አመታት ገደማ አንድም ጊዜ አልቅሶ እንደማያውቅ መናገሩን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ከአስር ያህል አመታት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ትጠናቀቃለች ተብላ የምትጠበቀዋ የአዲሷ የኤኮን ከተማ ግንባታ ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሩን ድምጻዊው ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ ግንባታው የሚከናወነው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለድምጻዊው በስጦታ ባበረከቱለትና ከመዲናዋ ዳካር አቅራቢያ በሚገኘው 2 ሺህ ካሬ መሬት ላይ መሆኑንም አመልክቷል፡፡ አዲሷ ከተማ ሙሉ ለሙሉ ከጸሃይ ብርሃን የሚመነጭ ሃይል የምትጠቀመውና በቴክኖሎጂ የተራቀቀች እንደምትሆን የተነገረላት አዲሷ የኤኮን ከተማ፤ ዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያን ጨምሮ አንድ ከተማ ሊኖራት የሚገባው መሰረተ ልማት እንደሚሟላላትም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ኤኮን ላይቲንግ አፍሪካ በሚል ፕሮጀክት 600 ሚሊዮን ያህል አፍሪካውያንን የታዳሽ ሃይል አቅርቦት ለማሟላት አቅዶ እየሰራ የሚገኘው ድምጻዊው፤ ከዚህ ቀደም ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደር በይፋ መናገሩን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ብራድ ፒት፣ ባለፉት 20 ያህል አመታት ጊዜ ውስጥ አንድም ቀን አልቅሶ እንደማያውቅ ከሰሞኑ ከአንድ መጽሄት ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ መናገሩን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ከቀድሞ ባለቤቱ አንጀሊና ጆሊ ጋር በማደጎ 6 ልጆች ያሉት የ55 አመቱ የሆሊውድ የፊልም ተዋናይ ብራድ ፒት፤ ባለፉት 20 ያህል አመታት ብዙ አሳዛኝና ልብ የሚሰብሩ ነገሮች ቢገጥሙትም፣ ስሜቱን ከመቆጣጠር ባለፈ አልቅሶ እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡
ብራድ ፒት በተለይም ከአንጀሊና ጆሊ ጋር ለሁለት አመታት የዘለቀውን ትዳር አፍርሶ፣ ከሶስት አመታት በፊት በፍቺ መለያየታቸውን ተከትሎ፣ በብቸኝነትና በሃዘን እየተቆራመደና መጠጥ በማብዛት ህይወቱን እየገፋ እንደሚገኝ ሚዲያዎች ቢዘግቡበትም፣ እሱ ግን የመጣውን በጸጋ በመቀበል ራሱን አረጋግቶ እንደሚኖር ገልጧል፡፡

Read 1416 times