Saturday, 07 December 2019 11:57

የኢትዮጵያ መዳረሻ በ2032

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(8 votes)

  ባለፈው ዓርብ ከአንድ የሥጋ ዘመዴ የስልክ ጥሪ ደረሰኝ፡፡ ከዚህ ዘመዴ ጋር ለበዓል “እንኳን አደረሰህ” ለመባባል ወይም የተለየ አጋጣሚ ካልተፈጠረ በስተቀር የስልክ ግንኙነት ስለማናደርግ  በቤተሰብ አካባቢ አንዳች ነገር ተፈጥሮ ሊሆን እንደሚችል እያሰብኩ የስልክ ጥሪውን አነሳሁ፡፡ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ፤ 50 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ለስድስት ወራት ያህል በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሲወያዩና ሲመክሩ ቆይተው አራት “ቢሆኑዎች”ን (Scenarios) አንጥረው ማውጣታቸውንና እነዚህንም “ቢሆኑዎች” ለህዝብ ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀ ስነ-ስርዓት ላይ እንድገኝ ጥሪ አቀረበልኝ፡፡ እኔም ግብዣውን ተቀብዬ ማክሰኞ ህዳር 23 ቀን 2012 ዓ.ም በስካይ ላይን ሆቴል ተገኘሁ፡፡ ሂደቱንም ተከታተልኩ፡፡ ያየሁትንና የሰማሁትን በዚህ ማስታወሻ አማካይነት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ አንባብያን ለማካፈል በማሰብ ይቺን ጦማር ከተብኩ፡፡
በቅድሚያ ይህንን ስራ ለውጤት ስላበቃው ተቋም ማንነት ላስተዋውቃችሁ፡፡ ይህንን ስራ ከጅማሮ እስከ ፍጻሜ ያቀደው፣ ያቀናጀውና ያስተባበረው “ደስቲኒ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭ” የተባለ አገራችን ለምትገኝበት የፖለቲካ አጣብቂኝ መፍትሄ ለማቅረብ የተጠነሰሰ አገር በቀል እንቅስቃሴ ነው፡፡ ኢንሼቲቩ “ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን” ከተባለ መቀመጫውን ካናዳ ካደረገ ዓለም አቀፍ ተቋም ጋር በመተባበር እንደሰራም በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የኢንሼቲቭ ቡድኑ ጠንሳሽ አባላት ዘጠኝ ናቸው፡፡ ዋነኛው ጠንሳሽ ግን አቶ ንጉሱ አክሊሉ የተባለ በውጭ ሀገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ምሁር ነው፡፡ አቶ ንጉሱ የሀገሩ ጉዳይ የሚያሳስበው ዜጋ ነው፡፡ ሃሳቡን የጸነሰው ከዘጠኝ ዓመት በፊት (2004 ዓ.ም) መሆኑንም ተናግሯል:: በተመሳሳይ ሁኔታ የፖለቲካ አጣብቂኝ የገጠማቸው ደቡብ አፍሪካ፣ ኮሎምቢያና ሌሎች ሀገራት ችግራቸውን እንዴት እንደፈቱ አቶ ንጉሱ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ከተወያየ በኋላ የሌሎችን ተሞክሮ ወደ ሀገራችን ለማምጣት ጥረቱን ቀጠለ፡፡ በሌሎች ሀገራት ተመሳሳይ ስራ ያከናወነ “ሬዮ ፓርትነርስ” የተባለ ተቋም ጋር በ2009 ዓ.ም ተነጋገረ፡፡ እቅድ አውጥቶ ስራውን በመቀጠል የአስተባባሪ ቡድን መረጣ አካሄደ፡፡ ፕሮጄክት ተቀረጸ፣ ውል ተፈረመ፡፡ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት (በተለይም የሰላም ሚኒስቴር) እንዲያውቁት ተደረገ፡፡ ሁለት ዲያስፖራዎችን ጨምሮ 50 የሴናሪዮ ቡድን አባላት ተመለመሉ፡፡ ወደ ስራ ተገባ፡፡
የሴናሪዮ ቡድኑ የኢትዮጵያን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚመሩ ወካይ አባላት ስብስብ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ አባላቱ በየዘርፋቸውና በየክፍላቸው የተከበሩና ተቀባይነት ያላቸው መሪዎች ሲሆኑ እንደ ቡድን ደግሞ በመፈጠር ላይ ያለውን ስርዓት በጋራ ለመገንዘብ የሚያስችል የተለያየ ግለ ታሪክና አመለካከት ያላቸው መሆናቸው ተነግሯል፡፡ የዚህ ቡድን አባላት የሲቪል ማህበራትን፣ የመንግስትን፣ የንግድ ሥራን፣ የትምህርት ተቋማትን፣ ወጣቶችን፣ ምሁራንን፣ ፖለቲከኞችን፣ ጦማሪያንንና ሌሎችንም የሚያጠቃልል መሆኑን በስነ-ስርዓቱ ላይ ከተበተኑ ሰነዶች ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ከእነዚህ 50 ሰዎች ውስጥ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ (ከአረና)፣ አቶ ዳውድ ኢብሣ (ከኦነግ)፣ አርቲስት አስቴር በዳኔ፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ዶ/ር ደሣለኝ ጫኔ (ከአብን)፣ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ (ከሸገር)፣ መምህርት መስከረም አበራ፣… የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከ50ዎቹ ውስጥ በግሌ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ቢያንስ በስም አውቃቸዋለሁ፡፡ ከአንዳንዶቹ ጋር የቅርብ ትውውቅም አለኝ፡፡
እነዚህ 50 የሴናሪዮ ቡድን አባላት ከብዙ ክርክርና ውይይት በኋላ በ2032 ዓ.ም ኢትዮጵያ ምን ዓይነት መልክ ሊኖራት እንደሚችል የሚያመላክቱ፣ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚወክሉ አራት አማራጭ “ቢሆኑዎችን” (Scenatios) በስምምነት ቀርጸዋል፡፡ እያንዳንዱ “ሴናሪዮ” እንደ ሀገር ምን ዓይነት ጉዞ ብንከተል ወደ የት ልናመራ እንደምንችል ያመላክታል፤ የእያንዳንዱ የጉዞ መስመር መጨረሻ ምን እንደሆነ ያሳያል ተብሏል፡፡ አራቱ “ቢሆኑዎች” የሚከተሉት ናቸው፡፡
1ኛ) “ሰባራ ወንበር”፡- የመጀመሪያው ሴናሪዮ “ሰባራ ወንበር” (Broken Chair) የሚል ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ ይህም ሲተነተን፤ ጠንካራ በሚመስል ነገር ግን ገና ሲነኩት እንደሚሽመደመድ ወንበር ቀላል ክብደትን እንኳ የማይሸከም መሆኑን የሚያመላክት ነው:: የወንበሩ አቅም ማጣት በማህበረሰቡ ለሚነሱ የልማት ፍላጎቶች የተግባር እርምጃ ለመውሰድ እንደማያስችልም በተምሳሌት የተገለጸበት ነው፡፡ መነሻው ላይ ብሩህ ተስፋን ቢያሳይም ለህዝብ ፍላጎት ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት አለመቻል በስርዓቱ ላይ የሚፈጠርን ጫና ያሳያል፡፡ ተግዳሮቶቹ ቢታወቁም ወቅቱን የጠበቀ ምላሽ ለመስጠት አለመቻል ባለንበት ቦታ ተቸንክረን እንደምንቀር ምክንያት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡
2ኛ) “አፄ በጉልበቱ”፡- ሁለተኛውን ሴናሪዮ “አፄ በጉልበቱ” (Hegemony) የሚል ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ በዚህ የማን አለብኝነት ሴናሪዮ የችግሮቻችን ምላሽ ይሆናል ብለው ያመላከቱት ስርዓት፤ ፈላጭ ቆራጭ የሆነና ጥብቅ ቁጥጥርን የሚያማክል እንደሚሆን ነው፡፡ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የኢኮኖሚውን አካሄድ፣ የአካባቢ መራቆትና የህዝብ እድገት ጫናዎችን ምላሽ ለመስጠት ቁጥጥር ተኮር ስርዓት መከተል አስፈላጊ አድርጎ ይወስዳል፡፡ በጊዜ ሂደት ተስፋ በመቁረጥ አመጽ ይቀሰቅሳል ብለው ማመናቸውን ገልጸዋል፡፡
3ኛ) “የፉክክር ቤት”፡- ሦስተኛው ሴናሪዮ “የፉክክር ቤት” (Divided House) የሚል ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ እንደሚያድረው ሁሉ የተለያዩ ቡድኖችና ክልሎች ያገኙትን አዲስ ነፃነት ባሻቸው መልኩ እንደሚጠቀሙበት የሚያመላክት ሲሆን፤ ከመንግስት ጀምሮ እስከ ቤተሰብ ድረስ በየደረጃው የሚፈጠሩ ክፍተቶችንና መከፋፈሎችን ለማመላከት የተጠቀሙበት ስያሜ ነው፡፡ ዘርፈ ብዙ ቀውሶች ፌዴራል መንግስቱን ሊፈረካክሱት እንደሚችሉና አንዳንድ ክልሎች የራሳቸውን ነፃነት ለማወጅ የሚያስችል ጡንቻ ማፈርጠማቸውን ያመላክታል ይላሉ፡፡
4ኛ) “ንጋት”፡- አራተኛው ሴናሪዮ “ንጋት” (Dawn) የሚል ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ በዚህ ሴናሪዮ የኢትዮጵያ እድገት ደረጃ በደረጃ እውን እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡ ፀሐይዋ ሙሉ ለሙሉ አልወጣችም፡፡ ግን የአዲሱ ቀን ወገግታ ጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያውያን መጠነ ሰፊ ማሻሻያዎችንና የእርቅ ሂደቶችን አጠናክረው በመተግበር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን ያስቀጥላሉ፡፡ ስር የሰደዱ ማህበረሰባዊ ቅራኔዎች በውይይት እልባት ማግኘት ጀምረዋል:: የይቅርታና የእርቅ ተቀባይነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ኢኮኖሚውና የዴሞክራሲ ተቋማት ደረጃ በደረጃ እየተገነቡ በጋራ ራዕይ ላይ የተመሰረተ አንድነት በመፍጠር ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡
ስለ ወደፊት ሁኔታ በእርግጠኛነት መተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የተወሰኑ ጉዳዮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ መተንበይ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፡- በመጪዎቹ ዓመታት የህዝብ ቀጥር እንደሚጨምር፣ ከተሞች እንደሚስፋፉ፣ የወጣቶች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ፣… ወዘተ. መተንበይ ነብይነትን የሚጠይቅ ጉዳይ እንዳልሆነ ኢንሼቲቩ በበተነው ሰነድ ላይ ተገልጿል፡፡ በእርግጠኛነት ሊተነበዩ ከሚያስቸግሩ ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ፤ የሀገሪቱ የዴሞክራሲ ባህሪ ምን ሊሆን ይችላል፣ የኢኮኖሚ እድገትና ሁሉን ተጠቃሚ የማድረጉ ሁኔታ፣ የግጭትና የብጥብጥ አዝማሚያ፣ የምግብ ዋስትና ሁኔታ፣ እንደ ሀገር የመቀጠላችንን ሁኔታ መገመት አስቸጋሪ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በዚህ ሂደት የተሳተፉ ወገኖች እነዚህን አራት ሴናሪዮዎች ከለዩ በኋላ ለሀገሪቱ የተሻለ ነው ያሉትን ሴናሪዮ መርጠዋል፡፡ የእነርሱ ምርጫ “ንጋት” (Dawn) የተሰኘው መሆን እንደሚገባው መተማመን ላይ መድረሳቸውን በስነ-ስርዓቱ ላይ ገልጸዋል:: እነዚህን ሴናሪዮዎች 50ዎቹ የቡድኑ አባላት ለሚወክሉት ማህበረሰብ ለማድረስ በጋራ ስልት መነደፉ ከተሰራጩ ሰነዶች ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም ሂደት የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ይጠበቃል፡፡ ከሌሎች ሀገሮች ከተገኘው ተሞክሮ በመነሳት የሴናሪዮ ቀረጻው ሂደት የተሳታፊዎችን አስተሳሰብ በመቅረጽና እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር መተማመን ለመፍጠር እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡ በዚህ ሂደት በተፈጠረው ግንኙነት የአብን ሊቀ መንበር ዶ/ር ደሣለኝ ጫኔ፣ ከአንድ የፖለቲካ መሪ ጋር በመግባባታቸው በቅርቡ በተካሄደ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውን ጭምር ተሞክሯቸውን አጋርተዋል፡፡
እነዚህ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ 50 ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት ተገናኝተው በሀገራቸው እጣ ፋንታ ላይ ሲመክሩ ቆይተዋል፡፡ በውይይቶቹ መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ጊዜያት ሊገጥሟት የሚችሉትን አራት “ቢሆኑዎች” ለይተው ለህዝብ ይፋ አድርገዋል፡፡ በእለቱ በነበረው ስነ ስርዓት ላይ እንዴት ለቡድኑ አባልነት እንደተመለመሉ፣ የቡድኑ አባላት በተገናኙበት በመጀመሪያው እለት የነበራቸውን ስሜት፣ በሂደቱ ያጋጠማቸውን ሁኔታ በተሞክሮ መልክ ለተሰብሳቢውና በቴሌቪዥን ለተከታተሉ ታዳሚዎች አካፍለዋል፡፡ ከአራቱ “ቢሆኑዎች” የቡድኑ አባላት መሆን ይገባዋል ብለው የመረጡትን ካሳወቁ በኋላ የመረጡት ሴናሪዮ እውን እንዲሆን እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የእኔን አስተያየት ልጨምርና ጽሁፌን ልቋጭ:: አራቱ ሴናሪዮዎች ለህዝብ ይፋ በተደረጉበት ስነ-ስርዓት ላይ ከነበሩ ተጋባዦችና በቴሌቪዥን ከተከታተሉ ሰዎች የሰማኋቸውን አስተያየቶች ላስቀድም፡፡ ከሰማኋቸው አስተያየቶች ውስጥ “እነዚህ 50 ሰዎች በምን መስፈርት ተመረጡ? ከአንድ ፓርቲ ሁለት ሦስት ሰው ከሚመረጥ ለሌሎች እድል ቢሰጥ አይሻልም ነበር ወይ? በእነዚህ 50 ሰዎች አማካይነት ብቻ ይህንን ትልቅ ተግባር ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ይቻላል ወይ? ከዓመታት በፊት እነ ዶ/ር ብርሃኑና ፕሮፌሰር መስፍን “ኢትዮጵያ በ2020” ብለው ጀምረውት ከነበረው ጋር ግንኙነት አለው?…” የሚሉት በተደጋጋሚ የሰማኋቸው ናቸው፡፡ “ምንም ግልጽ ነገር አይደለም፡፡ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስዶ በመገናኛ ብዙሃን ቢብራራ ጥሩ ነው” ያሉኝም አሉ፡፡
የራሴን ተሞክሮ ልንገራችሁ፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ በሀገራችን ተመሳሳይ የፖለቲካ አጣብቂኝ ተፈጥሮ እንደነበር የሚታወስ ነው:: በ1998 ፓርላማ ከገባን በኋላ መጀመሪያ አካባቢ ፓርላማው የመነታረኪያ መድረክ ሆኖ ነበር፡፡ መደማመጥም አልነበረም:: አንዳንዱ ሁኔታ በልምድ ማነስ የተፈጠረ ነበር:: ይህ ችግር ካልተፈታ ፓርላማው በመጪዎቹ 5 ዓመታት ሥራ መስራት እንደማይችል የገባቸው “ለጋሽ ሀገራት” አንድ ብልሃት አመጡ፡፡ መፍትሄው “ስምምነት መገንባት” የሚያስችል (consensus building) መድረክ በማዘጋጀት፣ ከተቃዋሚዎችና ከገዢው ፓርቲ ለተውጣጡ የተወሰኑ የምክር ቤት አባላት ስልጠና መስጠት ነበር፡፡ በዚህም መሰረት አፈ-ጉባዔውን ጨምሮ ወደ 50 የምንሆን የምክር ቤት አባላት ወደ አዳማ ከተማ እንድንሄድ ተደረግን፡፡ በሁለት ሆቴሎች አልጋ ተያዘልን፡፡ ከህንድ፣ ከካናዳና ከአሜሪካ የመጡ ባለሙያዎች ለአንድ ሳምንት ገደማ ስልጠና ሰጡን፡፡ የሌሎች ሀገሮችን የፓርላማ አሰራር አካፈሉን፡፡ በቡድን እንድንወያይ አደረጉን፡፡ አብረን እንድንበላና እንድንጠጣ አደረጉን፡፡ ምን ምን ብለው እንዳስተማሩን አሁን ባላስታውሰውም፣ በዚያች አጭር ጊዜ አብረን ያሳለፍን ሰዎች ጥላቻን ከልባችን ፋቅን፡፡ ልዩነቶቻችንን ይዘን አብረን መስራት እንደምንችል አምነን ተቀበልን፡፡ ልዩነቶቻችን ሳይሰረዙ የአንድ ፓርቲ አባል እስክንመስል ድረስ ተግባብተን ተመለስን፡፡ ወሬያችን ሁሉ “consensus building” የሚል ሆነ፡፡ አንዳንዶቻችን እስከ አሁን ድረስ እንጠያየቃለን:: በየበዓሉ መልካም ምኞታችንን እንላላካለን፡፡
በዚያ ስልጠና የቀሰምኩትና እስከ አሁን ድረስ በልቤ ውስጥ ያደረ ነገር ቢኖር የፈለገው ዓይነት የሰማይና የምድርን ያህል የሰፋ ልዩነት ቢኖር እንኳ ሰዎች ከተዋወቁ፣ ተቀራርበው ከተወያዩ፣ አብረው ከበሉና ከጠጡ፣ የተወሰኑ ሰዓታትን የሆድ የሆዳቸውን እያወሩ ካሳለፉ፣ ስጋትና እምነታቸውን ከተገላለጡ… በውስጣቸው ያለው ቂም፣ ቁርሾ፣ ጥላቻም ሆነ ቅራኔ ይለዝባል፡፡ ጥርጣሬ፣ ማግለልና መገፋፋት ይቀንሳል፡፡ መግባባትና መተሳሰብ ይፈጠራል:: ልዩነትን ጠብቆ አብሮ የመስራት አስተሳሰብ ይዳብራል፡፡
ስለሆነም፤ “ደስቲኒ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭ” ልዩ ልዩ መድረኮችን በመፍጠር በፖለቲካ ኃይሎች መካከል መቀራረብ እንዲፈጠር ጅማሮውን አጠናክሮ ቢቀጥል፣ በዚህ ወቅት የገጠመንን የፖለቲካ አጣብቂኝና ውጥረት ለማርገብ ያግዛል ብዬ አስባለሁ፡፡


Read 3005 times