Saturday, 07 December 2019 11:58

ፓርቲዎች የህወሐትን ግብዣ ተቃወሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

   ‹‹ህወኃት ለፈፀማቸው በደሎች ይቅርታ ሳይጠይቅ ለውይይት አንቀመጥም››

           ህወኃት የብልጽግና ፓርቲን ውህደት ‹‹የፌደራል ስርአቱን ማዳን›› በሚል ሰሞኑን ለሁለተኛ ጊዜ በመቀሌ ባደረገው ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል መኢአድ፣ ኦብነግ፣ ኦነግ እና አብን ስብሰባውን በጽኑ ተቃውመውታል፡፡
ህወኃት ባለፉት ዘመናት ለፈፀማቸው ወንጀሎች ይቅርታ ሳይጠይቅ ከድርጅቱ ጋር የሚደረግ ውይይት አይኖርም ብለዋል- ፓርቲዎቹ፡፡
“ህወኃት ህገመንግስት እና ህብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ስርአት” በሚል በመቐሌ ከተማ ባለፈው ማክሰኞ ህዳር 23 ተጀምሮ ለሁለት ቀናት በተደረገው ውይይት ላይ አምስት አመራሮቹ ተገኝተው እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦለት የነበረው መኢአድ፤ በደብዳቤ በሰጠው ምላሽ ‹‹ህወኃት/ትህነግ/ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለፈፀመው ግፍና መከራ በግልጽ ይቅርታ ሳይጠይቅ አብሮ ውይይት ለማካሄድ እንደሚቸገር  አስታውቋል፡፡
ከህወኃት/ትህነግ/ የቀረበለትን ጥያቄ በስራ አስፈፃሚ ደረጃ ተሰብስቦ እንደተወያየበት የጠቆመው መኢአድ፤ ‹‹ህወኃት/ትህነግ/ ባለፉት 27 አመታት ለፈፀማቸው ግፍና ሰቆቃ በይፋ የኢትዮጵያን ህዝብ ሳይጠይቅ በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ መወያየት እንደማይቻል›› አቋም መያዙን ገልጿል፡፡
አብን በበኩሉ፤ ‹‹ህወኃት ወንጀለኛ ድርጅት ነው እንዲያውም በሽብርተኝነት መፈረጅ ያለበት ነው›› ሲል ድርጅቱን ወንጅሏል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት ከህወኃት ጋር በአንድነት እየመከሩ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎችም የህወኀትን ወንጀል እየተጋሩና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በደል እየፈፀሙ መሆኑ መታወቅ አለበት›› ብሏል - አብን በሰጠው መግለጫ፡፡
ህወኃት የፌደራላዊ ስርአቱን ማዳን ብሎ የጀመረው ውይይትም ስላቅ ነው ያለው አብን ‹‹ባለፉት 27 አመታት የፌደራላዊ ስርአት በኢትዮጵያ እንዳይኖር ያደረገ አካል፣ አሁን የፌደራሊዝም ተቆርቋሪ መሆን የሚችልበት የሞራል ልዕልና የለውም›› ብሏል - ድርጅቱ፡፡
‹‹ህወኃት የፌደራላዊ ስርአት ተቆርቋሪ መሆን አይችልም፤ ባለፉት 27 አመታት ሲፈፀም የነበረው ለአሃዳዊነት የቀረበ ድርጊት ነው›› ብሏል፡፡ የፌደራሊስት ሃይሎች ስብሰባን መቀሌ ላይ በንግግር የከፈቱት የህወኃት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤል፤ አገሪቱ እጅግ አስፈሪና አደገኛ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝና የፌደራል ስርአቱ የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠበት ገልጸዋል፡፡
ሰሞኑን ህወሐት ባዘጋጀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጠቅላይነት አስተሳሰብ የተጫናቸው ተግባራት በሀገሪቱ እየተፈፀሙ ነው ያሉት ዶ/ር ደብረፂዮን፤ ይሄን መቀልበስ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በመድረክ የተገኙ ፓርቲዎች በዋናነነት የብልጽግና ፓርቲ መቋቋምን ሲኮንኑ እንደነበር ለአዲስ አድማስ የገለፁ ተሳታፊዎች ፓርቲው ጨፍላቂ መሆኑን በስፋት መነሳቱን ጠቁመዋል::
ተሰብሳቢዎቹ በመጨረሻ ባወጡት የአቋም መግለጫም፤ በቀጣይ ከህወኃት ጋር በመሆን የፌደራል ስርአቱንና ህገመንግስቱን ለመታደግ እንደሚታገሉ አስታውቀዋል፡፡ የጋራ ፎረም ማቋቋማቸውንም ገልጸዋል - ፓርቲዎቹ፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ከእያንዳንዱ ፓርቲ 5 ሰው ተወክሎ መገኘቱንና ከ50 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች መሳተፋቸውን የገለፀው የመድረኩ አዘጋጅ ኮሚቴ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ 7መቶ ያህል ተሳታፊዎች እንደተገኙም አስታውቋል፡፡
በመድረኩ የቀድሞዎቹ የህወኃትና የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩ የተሳተፉ ሲሆን፤ ከእነዚህም የትምህርት ሚኒስቴር የነበሩት ገነት ዘውዴ፣ የከተማ ልማት ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ካሡ ኢላላ ተጠቃሽ ናቸው፡፡   

Read 12922 times