Print this page
Saturday, 07 December 2019 11:44

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 9ኛው ዙር “ይቆጥቡ ይሸለሙ” ታህሳስ 22 ይጀመራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

    - ባንኩ ብርን በኤቲኤም ማሽን የማስገባት አዲስ አሰራር አስተዋውቋል
               - አጠቃላይ የባንኩ ሀብት 712 ቢሊዮን ብር ደርሷል
                    
            የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2004 ዓ.ም የጀመረውና ለማህበረሰቡ ቁጠባን ለማበረታት እያካሄደ ያለው 9ኛው ዙር “ይቆጥቡ ይሸለሙ” መርሃ ግብር ታህሳስ 22 እንደሚጀመር ባንኩ ትላንት  በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ፡፡ 9ኛውን ዙር ካለፉት 8 ዙሮች የሚለየው ሁለት የመኖሪያ አፓርታማዎችን ጨምሮ በርካታ አጓጊ ሽልማቶችን ማካተቱ እንደሆነ የባንኩ ሃላፊዎች በመግለጫው ላይ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ባንኩ ሰዎች ቁጠባን በመለማመድ በእርጅናቸው፣ በጤናቸው፣ በድንገተኛ አደጋ፣ በተለያዩ ችግሮችና ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚያጥሟቸውን ተግዳሮቶች ያለ ችግር እንዲወጡ እንደሚረዳቸው፣ ከቁጠባ ተነስተው ወደ ትልልቅ ኢንቨስትመንት መሸጋገር እንዲችሉና ባንኩም ለግሉ ዘርፍ ፋይናንስ የማቅረቡን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዲችል በማቀድ ላለፉት 8 ዓመታት ያካሄደው “ይቆጥቡ ይሸለሙ” መርሃ ግብር ያመጣውን አዎንታዊ ለውጥ አስታውሶ፣ ሰዎችን ለማበረታታትና ይበልጥ እንዲቆጥቡ ለማድረግ የሽልማቶቹን አይነትና ብዛት እየጨመረና እያሳደገ በመምጣቱ ሰዎች የመቆጠብ ባህላቸውንና ልምዳቸውን ማሳደግ መቻሉም ተመልክቷል፡፡
እስከ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ መርሃ ግብር የእጣው ተወዳዳሪ ለመሆን የቆጠቡትን ገንዘብ እስከ ዕጣው ማውጫ አለማንቀሳቀስ፣ ቢያንስ አነስተኛውን ተጨማሪ ገንዘብ መቆጠብ እንደ መስፈርት የተቀመጡ ሲሆን፤ አዲስ ደንበኞች ከ500 ብር ጀምሮ መቆጠብ ሲችሉ፣ ነባር ደንበኞች እንደ ቀደመ የቁጠባቸው ገንዘብ መጠን ከ500-700 ብር መቆጠብ እንደሚችሉና የሚቀበሉት የኩፖን መጠን ጣሪያ 10 እንደሆነ በመግለጫው ተብራርቷል::
በነዚህ መስፈርቶች መሰረትም ብቁ ለሆኑ ተወዳዳሪዎች ለ1ኛ ዕጣ፡- ሁለት የመኖሪያ አፓርታማዎች፣ ለ2ኛ ዕጣ፡- ሦስት መለስተኛ የጭነት መኪናዎች፣ ለ3ኛ ዕጣ፡- 15 የቤት አውቶሞቢሎች እና ለ4ኛ ዕጣ፡- በተለይ በገጠሩ አካባቢ ለሚኖሩ ቆጣቢዎች አገልግሎት የሚውሉ 6 ሰዎችን ማስቀመጥና ዕቃም መጫን የሚችሉ 30 የሚደርሱ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ለሽልማት መዘጋጀታቸውን የባንኩ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ የአብስራ ከበደ ተናግረዋል፡፡
ባንኩ በአሁኑ ወቅት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንም ለህዝብ እያስተዋወቀ ሲሆን፤ ሰሞኑን ራስ ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው ፊንፊኔ ቅርንጫፉ በሙከራ ደረጃ የጀመረው ብርን በኤቲኤም ማሽን ወደ ሂሳብ ቁጥር የማስገባት አሰራር አንዱ ነው፡፡ በዚህ ማሽን ብር ለወዳጅ ዘመድ መላክ፣ የተለያዩ የብር ኖቶችን ቀላቅሎ ማስገባትና በቼክ ገንዘብ ዲፖዚት ማድረግ የሚያስችል ሲሆን፣ ማሽኑ ሃሰተኛ የብር ኖቶችን መለየት፣ የውጭ ምንዛሬን መስጠትና የተቀላቀሉ የብር ኖቶችን መለየት፣ ኖቶቹን እንደየአይነታቸው ለይቶ መመዝገብና ደረሰኝ መስጠት እንደሚችል የገለፁት አቶ የአብስራ ይህ አሰራር የባንኩን የስራ ጫና ከመቀነሱም ባሻገር ደንበኞች ሰዓታቸውን ለመቆጠብም ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡
ባንኩ በአሁኑ ሰዓት 1510 ቅርንጫፎች፣ ከ22 ሚ. በላይ ደንበኞች፣ ከ40ሺህ በላይ ሰራተኞች፣ ከ2 ሚ. በላይ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች፣ ከ5 ሚ. በላይ የኤቲኤም ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን፣ የተቀማጭ ገንዘቡ መጠን 542 ቢሊዮን ብር መድረሱንና አጠቃላይ ሀብቱ 712 ቢሊዮን ብር መድረሱንም አቶ የአብስራ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

Read 12485 times