Saturday, 30 November 2019 13:58

አርቲስት ዳንኤል ጋጋኖ የስፔይን ፊልሙ በአውሮፓ ተወዶለታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  እስካሁን በ5 የስፔይን ፊልሞች ላይ ተውኗል

              በአንድ ወቅት በፑሽኪን የባህል ማዕከል በቀረበ ቴአትር ላይ የዶክተር ጋጋኖን ገፀ ባህሪ ወክሎ ከተወነ በኋላ ‹‹ዳኒ ጋጋኖ›› እየተባለ  ነው የሚጠራው፡፡ በበርካታ የአማርኛ ፊልሞችና ቴአትሮች ላይ የተወነው አርቲስት ዳንኤል ታደሰ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከስፔይን የፊልም ባለሙያዎች ጋር ፊልም እየሰራ ይገኛል፡፡ አምስተኛውና ‹‹Jesus shows you the way to the high way›› የተሰኘው  ፊልሙ በቅርቡ የተመረቀ ሲሆን በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ ይሁን እንጂ አርቲስቱ በገጠመው የጤና እክል በምርቃቱ ላይ አለመገኘቱን ይናገራል፡፡ ሰሞኑን በተመረቀው ፊልሙ፣ በጤና ሁኔታውና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በመኖሪያ ቤቱ ተገኝታ አነጋግራዋለች፡፡


              የጤና እክል እንደገጠመህ ሰምቻለሁ፡፡ ህመምህ ምንድን ነው?
ወደ ሕክምና ስሄድ የልብ ህመም ነው ብለውኝ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ልብህ ደህና ነው፤ የኦክሲጅን እጥረት ነው ተብያለሁ፡፡
አሁን በኦክስጅን እየታገዝክ ነው የምትተነፍሰው አይደል…?
እውነት ነው፤ በኦክስጅን እየታገዝኩ መተንፈስ ከጀመርኩ ከሰባት ወራት በላይ ሆኖኛል፡፡ የኦክስጅን እጥረት አለብኝ፡፡ እጥረቱ በምን ምክንያት እንደመጣ በግልጽ የነገሩኝ ነገር የለም፡፡
ለመሆኑ ህመሙ ምን ይሆን? አሁን እንዴት ነህ? ለውጥ አለህ?
እንደነገርኩሽ በህመሙ ምክንያት ብዙ እንቅስቃሴም ስራም ላይ አልነበርኩም፤ ነገር ግን አሁን እግዜር ይመስገን መንቀሳቀስም መስራትም እችላለሁ፡፡ በጣም ለውጥ አለኝ፡፡
ስለ መታመምህ ብዙ ያልተነገረው ለምንድን ነው?
እኔ ሰው ሰምቶ እንዲጨነቅ ስላልፈግሁ አልተሰማም፤ ቤተሰቤም ጓደኞቼም አጠገቤ ሆነው አይዞህ እያሉኝ ስለነበረና እንክብካቤያቸው ስላልተለየኝ ነው፡፡ ከነሱ አልፎ ሌላው ሰምቶ እንዲጨነቅ ባለመፈለጌ ነው እንጂ ህመሙ ቀላል ሆኖ አልነበረም አሁን ግን በጣም ደህና ነኝ፡፡
አንተ በመሪ ተዋናይነት የሰራህበት “Jesus shows you the way to the high way” የተሰኘው ፊልምህ ሰሞኑን በስፔን ተመርቋል፡፡ እስኪ ስለ ፊልሙ ንገረኝ?   
የፊልሙ ዘውግ ሳይንስ ፊክሽን ነው ደራሲና ዳይሬክተሩ ስፔናዊው ሚካኤል ሎዮንሰ ሲሆን የፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ከመሆኑም በተጨማሪ ኢስቶኒያ ውስጥ የፊልም መምህርም ነው፡፡ የፊልሙ ሀሳብ በስለላ ላይ የሚያጠነጥን ሆኖ ሳይንሳዊ ይዘትም አለው፡፡
ፊልሙ ስፔይን ውስጥ ከመመረቁ በፊት በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ታይቶ ተወዳጅነት ማትረፉን ሰምቻለሁ…
እውነት ነው ፊልሙ በአውሮፓ አገራት፣ በአሜሪካና በኢስቶኒያም ጭምር ታይቶ ከጠበቅነው በላይ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ቀረፃው ኢስቶኒያና ስፔይን ነው የተካሄደው:: እኔም ለቀረፃው እዚያ ነበርኩኝ፡፡ ደርሼ ነው የመጣሁት፡፡
ፊልሙ ሲመረቅ በቦታው አልተገኘህም፡፡ በህመምህ ምክንያት ነው ያልሄድከው?
አዎ የጤናዬ ሁኔታ በምረቃው ላይ እንዳልገኝ አድርጎኝ ነበር፡፡ አሁንም በስፔይን በስፋት መታየቱን ስለቀጠለ መሄዴ አይቀርም፡፡ ጤናዬ ጥሩ እየሆነ ነው፡፡
በምርቃቱ የተገኘው ተመልካች በአንተ ፊት የተሰራ ማስክ አጥልቆ ነው ወደ አዳራሹ የገባው ተብሏል፡፡ በዚህ ምን ተሰማህ?
ይሄ ከደስታ አልፎ ግራ ነው ያጋባኝ:: ምክንያቱም ከዚህ በፊት ተመልካች የመሪ ተዋናይ ፊት ማስክ ለብሶ ሲታደም አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ አስበሽዋል… አዳራሹ ሁሉ ዳኒ ጋጋኖ ሆኖ… በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ያው ምርቃቱ ላይ ‹‹ሰርፕራይዝ እናድርገው›› ብለው ለእኔ ክብር አስበው ነበር ያደረጉት:: እንግዲህ የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ አልተገኘሁም:: ነገር ግን ከምርቃቱም በኋላ የሚገቡት የፊልሙ ተመልካቾች፣ የፊቴን ማስክ ለብሰው ማየታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በአዳራሹ ውስጥ ከአንድ ሰዓት በላይ የፈጀውን ፊልም ለመመልከት የፊቴ ማክስ ይለበሳል ማለት ነው፡፡
ከዚሁ ፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ጋር የተለያዩ ፊልሞችን ሰርተሃል፡፡ አንድ ጊዜ ከአርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሸ አበራ ሞላ) ጋር… አንድ ጊዜ ደግሞ ከአርቲስት ሰላም ተስፋዬ ጋር የተወናችሁበት ይመስለኛል…?
እውነት ነው፡፡ ከጋሸ አበራ ሞላ ጋር ‹‹Where is my dog›› የተሰኘ አጭር ፊልም የሰራሁ ሲሆን ሰላም ተስፋዬ ያለችበት ደግሞ ‹‹ክራምፕስ›› ይሰኛል፡፡ ርዝመቱ ከአንድ ሰዓት በላይ ነው፡፡ ሌላው ‹‹ችግር አለ?›› የሚል ነው:: አንዱን ስሙን ረሳሁት፡፡ ብቻ የአሁኑ ‹‹Jesus Shows you the way to the high way›› አምስተኛ ሥራዬ ነው - ከስፔኖቹ ጋር ስሰራ፡፡
በዚህኛው ፊልም ክፍያው እንዴት ነው… ጥሩ ነበር?
በጣም አሪፍ ነው ለእኔ እንደውም እጅግ ጥሩ ነው፤ በዩሮ ነው የከፈሉኝ፡፡   
የክፍያውን መጠን ብትገልጽልኝ…
መጠኑን ባልገልፅ ደስ ይለኛል፣ በጥቅሉ ጥሩ ክፍያ ነው ካልኩሽ አይበቃም?
አሃ…ቁጥሩ ያስደነግጣል እንዴ?
ማስደንገጥ እንኳን አያስደነግጥም፤ ግን መግለፁ አስፈላጊ መስሎ ስላልታየኝ ነው፡፡
የእኛ አገር አርቲስቶች ከውጭው አለም አርቲስቶች ጋር ተገናኝተው የመስራት ብዙ ዕድል የላቸውም፡፡ አንተ እንዴት ነው ይህን ሁሉ ፊልም ከስፔይን ባለሙያዎች ጋር ለመስራት የቻልከው?
እኔ በዚህ አጋጣሚ አርቲስት ዮሐንስ ፈለቀን (ጆኒን) ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በእሱ ምክንያት ነው እነዚህን ሰዎች ያገኘኋቸው፡፡ ጋሸ አያልነህ ሙላቱ ከስፔይን የተረጎመው አንድ ቴአትር ብሄራዊ ቴአትር ይመረቅ ነበር፡፡ የስፔይኑ ዳይሬክተር የተተረጎመውን ቴአትር ሊመለከት እዚህ አገር በመጣበት አጋጣሚ አርቲስት ዮሐንስ አስተዋወቀኝና ‹‹ከዚህ ልጅ ጋር መስራት›› እፈልጋለሁ አለ፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ ግንኙነታችን ቀጥሎ እዚህ ደረስን፡፡ የግኙነታችን መነሻ ግን አርቲስት ዮሐንስ ፈለቀ ነው፡፡ ከጆኒ ጋር እንደምታወቂው ‹‹ሳምራዊው›› እና ሌሎች ስራዎችንም አብሬው ሰርቻለሁ፡፡ የቅርብ ወዳጄና ጓደኛዬ ነው፡፡ አሁን ኑሮውን አሜሪካ አድርጓል፡፡ መልካሙን ሁሉ እመኝለታለሁ፡፡
አሁን ምን ለመስራት አቅደሃል?
አሁን ከወዳጄ አርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ ጋር እየሰራሁ ነው፡፡ ቴአትርም ማስታወቂያም አሰርቶኛል፡፡ ለእኔ የሚጨነቅና የቅርቤ ሰው ነው፡፡ በጣም አመሰግኝልኝ፡፡ ከዚህ በኋላም አብሬያቸው እንድሰራ ጓደኞቼ ጥሪ እያደረጉ ነው፡፡ ለምሳሌ እነ የድል አክሊል፣ ሀብታሙ ማሞ፣ እነ ደረጀ ፍቅሩና እነ ግርማይ እየደወሉና አብረን እንስራ እያሉ እያበረታቱኝ ስለሆነ፤ ለስራው በዝግጅት ላይ ነኝ ጤናዬም እየተሻሻለ ነው፡፡
ፊልምህ ለዚህ ስኬት በመብቃቱ እንኳን ደስ አለህ… ጤናህ ሙሉ ለሙሉ ተስተካክሎ ወደ ስራህ እንድትመለስ እመኝልሃለሁ፡፡
እጅግ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከዚህም ቀደም ሰፊ ቦታ ሰጥቶ እንግዳ አድርጎኛል፡፡ አሁንም በውጭ የሰራሁት ፊልም ስኬት አስደስቶት፣ የጤናዬም ሁኔታ አሳስቦት ‹እንዴት ነህ› ለማለትና ለመጠየቅ ያሳየውን ተቆርቋሪነት አደንቃለሁ፡፡ የዝግጅት ክፍሉን አመሰግናለሁ፡፡

Read 1048 times