Saturday, 30 November 2019 13:14

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   --እስክንድርና ታምራት ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሠራተኞች የሥራ መጀመሪያ ሰዓት አንስተው ነበር ቪዲዮ መመልከት የጀመሩት:: በስቱዲዮ ፊልም ማቀናበሪያ ማሽን እየታገዙ በሐምሌና ነሐሴ 1983 የተላለፉ ፕሮግራሞች ለሦስት ሰዓታት አዩ፡፡ አራት ዐይኖች ለረዥም ሰዓት በስክሪን ላይ ፈጠው ሊያብጡ ደረሱ፡፡
ይህ የገረመው የቲቪ ማሽን ሠራተኛ፤ “የሻይ ሰዓት ስለሆነ ዕረፍት መውሰድ ትችላላችሁ” በማለት ከተመሰጡበት ስሜት ቀሰቀሳቸው:: አክሎም፤ “ወጥታችሁ ትጠጣላችሁ? ወይስ እዚህ ላምጣላችሁ?” አለ፡፡ ሁለቱም መልሳቸው አንድ ነበር፤ ያውም በፍጥነት፡፡
“ከተቻለ እዚህ ብታመጣልን እንወዳለን” የሚል ነበር፡፡
“ደህና ...ሻይ ….ቡና …..ለስላሳ……ምርጫችሁን ብትነግሩኝ?”
“ቡና በወተት….ካላስቸገርንህ ላይተር ሲጋራም ብታስልክልን…ከይቅርታ ጋር” ታምራት በትህትና የተናገረው ነው፡፡
“ዶንት ወሪይ (Don’t worry) ….ምንም ችግር የለውም ….ምን ዓይነት ሲጋራ?”
“ዊኒስተን አንድ ፓኬት…” አለ እስክንድር፤ የሃምሳ ብር ኖት እየሰጠው፡፡
እነ ፕሮፌሰር በዚህ የቪዲዮ ሶስት ሰዓት ምልከታቸው፤ በመላው አዲስ አበባ የቀይ ሽብር ተዋንያኖች ሲጋለጡ የተላለፈውን ፕሮግራም አገባደው ነበር፡፡ በመሐል ፒያሳ እነ እርገጤ መድባቸውና ኤልያስ ኑር የጨፈጨፉት…በጉለሌ ዙሪያ ከፍተኛ ሰባትና ስምንት ፍቃዱ የገደላቸው የኢህአፓ ወጣቶች …በጉራጌ ዞን ደግሞ ገስግስ የተባለው ያደረሰውን እልቂት ወዳጅ ዘመድ እየተነሳ ሲያጋልጥ ተመለከቱ:: በተለይ አንድ አዛውንት እናት፤ ቅዱስ የሆኑ ባላቸውና ልጆቻቸው እንደተገደሉባቸው እያነቡ አጋለጡ፡፡ ገስግስ ከክልል ውጪ አዲስ አበባ መጥቶ የአብሬት ሼክ የሆኑት አዛውንት፤ ያለ አንዳች ወንጀል ከእነ መኖሪያ ቤታቸው እንደወሰዳቸው …እስከ አሁን የት እንደደረሱ እንደማያውቁ ጐልማሳ ልጆቻቸው እያነቡ አጋለጡ፡፡
እነዚህ ልጆቻቸው በማከልም “…እስከ አሁን በአባታቸው የአብሬት ሼህ በሕይወት አለመገኘትና ተሰውሮ መጥፋት ሳቢያ…እናታቸው በሐዘን ተቆራምተው…ቤተሰቦቻቸው በሰቀቀን ሲጠበሱ እንዲኖሩ …የበለጠ ደግሞ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ጨምሮ …በእስልምና ሃይማኖት ቅድስናቸው …እኝኸ የአብሬት ሼህ ያፈሯቸው የሰባት ቤት ጉራጌ ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኙ ተከታዮቻቸው…ምንጊዜም ሀዘናቸው አብሮዋቸው ይኖራል…” አሉ፡፡
ይህ የቪዲዮ ትዕይንት እንዳበቃ የከፍተኛ ሰባቱ ፍቃዱ ሲጋለጥ የሚያሳየው ምስል ቀጠለ:: ጋዜጠኛው ሰለሞን አስመላሽ፣ ሁለት ሴቶችን ከዳርና ከዳር አስቀምጦ ከመሃል ፍቃዱን መጠየቅ ጀምሯል፡፡
“እነዚህን ሴቶች ታውቃቸዋለህ?”
“አላስታውሳቸውም…”
“እናንተስ እሱን ታስታውሱታለችሁ?”....ጋዜጠኛው ነበር፡፡
“በደንብ ነዋ! ...አንድ ሰፈር አብረን ኖረናል…በደንብ እንተዋወቃለን…”
በስተግራ የተቀመጠችው በሲቃ ተናገረች፡፡
“እሺ የተፈፀመባችሁን በደል ግለጹ!...”
“በ1969 ዓ.ም ወር አንድ እለት፣ እኩለ ሌሊት ካለፈ በኋላ በራችን ተንኳኳ፤እናቴ ስትከፍት ፍቃዱ አጥራችንን ዘለው ከገቡ ግብረ አበሮቹ ጋር መሣሪያ እንደታጠቁ ዘው አሉ፡፡ …ወንድ ልጇን ውለጂ አሏት…ካየችው እንደሰነበተ ብትገልጽም፤ ከጥፊና ርግጫ አልዳነችም፡፡…በመጨረሻ ሁላችንንም አፍሰው ቀበሌ አሰሩን፡፡
“የበደላቸው በደል ከእስር ቤት እየጠሩ ማታ ጠጥተው እየመጡ ይዳሩን ጀመር በተለይ ፍቃዱ መጀመሪያ እናታችንን …አስገድዶ ከተገናኘ በኋላ …ቀጥሎ እኔና ታናሽ እህቴን ተራ አስገባን…” በማለት እንባ እየተናነቃት ተናገረች፡፡
ጋዜጠኛው የከፍተኛ ሰባቱን ጨፍጫፊ ፍቃዱን እየተመለከተው “…እህሳ! ...ለዚህ ምን መልስ አለህ? አለ፡፡ አረመኔው ፍቃዱ የሐሰትን ሸማ እንደተከናነበ የውርደት ማቁን ተከሽኖ መዘባረቅ ጀመረ፡፡ ጊዜ የገለጠው ጉድ፣ ወቅት ያሳጣው ግፍ በዚህ መልክ ለአደባባይ በቃ፡፡
እነ ፕሮፌሰር ቡና እንደመጣላቸው፣ ቪዲዮውን አጥፍተው ዕረፍት ወሰዱ፡፡ ለትንሽ አፍታ ዝም ብለው በራሳቸው ሐሳብ ተዋጡ፡፡ ሲጋራ እየለኮሰ ዝምታውን የገረሰሰው ታምራት ነበር…ቀድሞ፡፡    
ምንጭ፡- (ከዘውዴ አርጋው “የአሲንባ ናሙና መርካቶ” የተሰኘ  አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ፤2012 ዓ.ም)

Read 3514 times