Print this page
Saturday, 30 November 2019 12:51

ራስ ራሱን የሚሸተው ገጣሚ

Written by  ሻሎም ደሳለኝ
Rate this item
(1 Vote)

አዉርቶኝ አያውቅም ፈጣሪ ስለ ሰዉ
ሰዉ ስለፈጣሪ ብዙ ጊዜ አወራኝ
መጣፍ ይገልጥና ምዕራፍ ይጠቅስና
እግዜር ጠራህ ይላል እራሱ ሲጠራኝ

ርዕስ:- ወደ መንገድ ሰዎች
የገፅ ብዛት:- 88
የግጥም ብዛት:- 59
የመጀመሪያ ዕትም:- 2010 ዓ.ም
አንዳንዶች ስነግጥምን “ተናጋሪ ስዕል ነው” ይሉታል። ሌሎች ደሞ ስነግጥም “ሙዚቃዊ ሐሳብ ነው” ሲሉ ይደመጣል። በእኛም ሀገር ብዙ ገጣምያን የራሳቸውን ብያኔ ሲያሰፍሩ ይስተዋላል። ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን በ”እሳት ወይ አበባ” ፣ ሰሎሞን ደሬሳ በ”ዘበተ ዕልፊቱ” የግጥም መድብል ላይ የየግላቸውን ብያኔ አስቀምጠዋል፡፡
ዛሬ ለዳሰሳ በመረጥኩት “ወደ መንገድ ሰዎች” የግጥም መድበል መግቢያ ላይ ገጣሚ መዘክር ግርማ ስለ ግጥም ሲገልጽ፤ “የግጥም ሥላሴዎች ሀሳብ፣ ሙዚቃና ስሜት ሲሆኑ በስም ሦስት በመለኮት አንድ ናቸው። መለኮትም ቃል ነው የሚያዋስጣቸው።”  ብሏል፡፡
እንደ ቶማስ ካርሊሌ ከሆነ፤ “ሥነግጥም ሙዚቃዊ ሀሳብ ነው” ብሎ መበየን ይቻላል።
 ይሄን ሀሳብ ሰሎሞን ደሬሳ “ልጅነት” በተሰኘው መድበሉ መግቢያ ላይ ስለ ራሱ ግጥም ባቀረበው ሃሳብ እናጠናክረው።
“ግጥሞቼ እንደ አዝማሪ ግጥም ቢታዩልኝ የበለጠ ያኮራኛል። ድምፄ እንዳይሆን ባይሆን ኖሮ ፤ ከምፅፋቸው ይልቅ በያራዳው ከክራር ምት ጋር ባስማማቸው እመርጥ ነበር” ብሏል፡፡
ገጣሚ መዘክር ግርማ በበኩሉ፤ “ግጥም ሙዚቃ አይደለምን? “በማለት እራሱ ጠይቆ፣ እራሱ ሲመልስ፤ “ሙዚቃስ ከበሮ ብቻ ነውን ?” ይልና. . .  “ “ቤት ምቱ ነገር ግን በር አስከፍቱ። ቤት አትምቱ፤ ነገር ግን ከዘፈናችሁ አትውጡ” ሲል ምክሩን ይለግሳል፡፡
መምህርና ገጣሚ መስፍን ወንድወሰንን “ወደ መንገድ ሰዎች”  ስለተሰኘው  መድበል ጠይቄው ሲመልስልኝ. . .
“አንዲት ልብ የምትሰውር ሙዚቃ ሳደምጥ፣ ግጥሙ ከዜማው ሲዋሃድልኝ ፤ እውን ይሄን ሥራ ሰው ሰርቶት ነው ወይስ ከሰማይ ወርዶ? ብዬ አስባለሁ። ወደ መንገድ ሰዎችን ሳነብ የሚሰማኝ ልክ እንደዚሁ ነው” ብሎኛል፡፡
ደራሲና ሀያሲ ደረጀ በላይነህ በበኩሉ፤ “ወደ መንገድ ሰዎች” በተሰኘው መድበል ላይ በዚሁ ጋዜጣ ላይ  ባቀረበው ዳሰሳ፤
“ገጣሚው ስለ ፍቅር በተለይ ስለ ማራኪነት የፃፋት አንዲት ግጥም ፤ ሙዚቃው ሳይቀር ነፍስ ያስደስታል። አድናቆቱ እንደ ፊልም አንዲቷን ቀዘብ - ውልብ ያደርጋል” ይለናል። በዚህ ብቻም አያበቃም፤ “ግጥምን ከሙዚቃ ነጥለን ሀሳብ ብቻ ነው ማለት ሞኝነት ነው” ሲልም ይተቻል።
በዚሁ የተሳካ ሙዚቃዊ ውበት ከሚታይባቸው የገጣሚው ስራዎች አንዱን ልምዘዝ. . .
ደማምዬ ልጅ ናት
ከዘፈን ገላ’ና ፣ ከለምለም እወዳ
ቀምሞ የሰራት ፣ እሪኩም ዘመዳ
ደማምዬ ልጅ ናት … በደማምነቷ
የተከለከለ ቤተስኪያን መግባቷ።
መድረኩን ቢነሷት፣
ማህሌት ቢገፏት ባይሰጧት ዲቁና
ከንፈሯ ለሃሌ አይኗ ለትወና…
የፃፈችም እንደሁ፣ ጥርሷን አስመስላ
ያወራችም እንደሁ፣ ልብ ጨርቅ አስጥላ
የሳቀችም እንደሁ፣ ክራር ተኮልኩላ
የተቆጣች እንደሁ፣ እርግፍ እንደ ሾላ!
እርግፍ እንደ ሾላ፣ ቁጣዋን ሰምቼ
እሆዷ እንድገባ፣ በጇ ተነስቼ።
እነኚህ ስንኞች ለምላሳችን ቀላል፣ ለስሜታችን ቅርብ ሆነው፣ ሙዚቃዊ ለዛቸው ሲወርሰንና ሲዋሃደን ይታወቀናል። ነገር ግን ሙዚቃ ብቻ ደሞ አይደለም። ሀሳብ ሲተላለፍበትም እናየዋለን። የግጥሙ ገፀሰብ ተባዕት ቢሆንም፣ በሦስተኛ መደብ የምትተረከው ግን አንስታይ ናት። ይህቺ እንስት የተቀመመችው ከዘፈን ገላ’ና ከለምለም እወዳ ነው ። የዘፈን ገላ እንዴት ያለ ነው? ረቂቅ ነውና አናውቀውም። ነገር ግን የሲናን በረሀ ባስናቀ ሀሩር ምድር ላይ ፤ እንደ ጥጥ የሚለሰልስ ቀዝቃዛ ነፋስ ጅስማችንን ዳሶ ሲሄድ የሚሰጠንን ስሜት ያጋባብናል። ለስላሳነቱ ውልብ ይልብናል። ውበቷን ይጠራብናል። እንዲያም ሆኖ ግን እንዲህ ያለችውን ውብ ሴት፣ ቤተ ክርስቲያን መግባቷ የተከለከለ መሆኑን ይተርክልናል። “ለምን?” ለሚለው ጥያቄ ምላሹ፤ “በደማምነቷ” የሚል ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ዘፈኖቻችን መሀል ውበትን ለመግለፅ “ደማምዬ” የሚል ቃል መስማት የተለመደ ነው። በዚህ ግጥም ውስጥ ግን የተገለፀበት እማሬአዊና ፍካሬአዊ ፍቺው ለየቅል ነው። እውነት ነው፤ ከላይ ስለ ውበቷ እየነገረን ስለመጣ ቤተ ክርስቲያን መግባት የተከለከለችው በውበቷ ምክንያት ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን በውበቷ ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ መግባት የተከለከለች እንስት አጋጥሞን አያውቅምና “ጅል ግጥም” ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን ይህቺ እንስት “ደማምዬ ልጅ ናት” የተባለችበት ፍቺ “ውበቷን” ሳይሆን “የወር ግዴታዋን” መሆኑን ላጤነ አንባቢ፤ የገጣሚውን በቃላት የመጫወት ብቃትና ተዝናኖት ይገነዘባል:: ሌላው የገጣሚው ድንቅ ብቃት ግጥሙን የሚያስተላልፍበት ዘዴ ነው። “ገጣሚ አይሰብክም፤ ገጣሚ አያስተምርም፤ የነፍሱን ዘንግ በሚያወዛውዘው ወጀብ ውስጥ ሆኖ ቀለሙን ይረጫል እንጂ” እንዲል ደረጀ በላይነህ።
ለምሳሌ ያህል ቀጣዩን ግጥም እንመልከት. . .
ጣቷን ተከትዬ
ዐይን ዐይኗን እያየሁ ፣ ሰማዩን ታያለች
   ያመሻሹን ጀምበር ፣ አቅርራት እንደ’ንባ
ከጉም - ከብርሃን ፣ በስውር እጆቹ
   እግዜር ኅብረ - ቀለም ፣ ሰማዩን ሲቀባ
ወዲያው ሠምሮ ወዲያው ፣ የሚሰወረውን
   ያሣሣሉን ፈለግ ፣ እየተከተለች …
                           ተመልከት ትላለች።
“ተመልከት” ትላለች “ተመልከት እዚያ ጋ
ሰው አይታይህም - ወደማይደርስበት
                                   እጁን የዘረጋ? …
            ደሞ ከ’ርሱ በላይ
እያት ሳታመልጥህ ፣ ሳታመልጥህ እያት!
ከፀሐይ ግባት ስር ሌላ ፀሐይ ግባት
ሀምራዊ መስኳ ላይ ፣ ያልተጫነ ፈረስ
ቀለመ - ወርቅ ውሃ ፣ ከገነት የሚፈስ
ውሃው ዳር ገጣሚ ፣ እኒህን እያዬ
አየህ?! “ ትለኝና
እመለከትና ጣቷን ተከትዬ
ሄጄ ሄጄ እርሷው ጋር ፣ ይገታል ጉዞዬ
                   ይበዛል ስቃዬ …
አዬ!
ልነግራት ፈርቼ ፣ ያልነገርኳት ነገር
ካሳየችኝ ይልቅ ፣ ጣቷ ታምር ነበር!
በዚህ ግጥም ውስጥ አንዲት ሴት ሰማዩን እያየች፣አጠገቧ አብሯት ለተገኘ ወዳጇ እንዲህ ትለዋለች…
“ተመልከት” ትላለች “ተመልከት እዚያ ጋ
ሰው አይታይህም ወደ ማይደርስበት
                                       እጁን የዘረጋ? - እያለች ሰማዩ ላይ ስለምታየው የጉምና የብርሃን ተዋህዶ (ሃርሞናይዜሽን) የፈጠረውን ውበት ታወሳለታለች። እኒህን ሁለት መስመር ስንኞች ብቻ ተመርኩዞ፣ አንድ ሰው ብዙ ገፅ ትንታኔ ሊሰጥበት የሚያስችል ድንቅ መልዕክት አለው።  ከዚህ ስንኝ በላይ ለእምቅነት ማሳያ የሚሆን ስንኝ ከወዴት ይመጣል? ጉምና ብርሃን አይጨበጤ፣ አይዳሰሴ ናቸው። ሴቲቱ ሰማዩ ላይ የምታየው ምስል፤ አንድ ሰው ወደ ማይደርስበት እጁን ሲዘረጋ ነው። እሷም እጇን ትጠቁማለች፤ ወደ ማትደርስበት። ብትደርስበት እንኳ የማትጨብጠው የማትዳስሰው ወደሆነ የጉምና የብርሃን ምስል። ብዙ ሰው እንዲህ ነው። መዳረሻውን ሳያውቅ ይንጠራራል፤ ያለውን ሳያውቅ ለሸመታ ይወጣል፣ ትችትና አድናቆቱን ከእከሌ እንጂ ከራስ አይጀምርም።
የግጥሙ መቋጫ ላይ “እያት” እያለች ሰማዩን ስታሳየው የነበረው አብሯት የቆመው ሰው  እንዲህ ይላል፤ ከገዛ ልቡ ጋር ሲያወጋ. . .
አዬ!
ልነግራት ፈርቼ ያልነገርኳት ነገር
ካሳዬቺኝ ይልቅ ጣቷ ያምር ነበር!
ገጣሚው አካባቢውን ይወዳል፣ ልጅነቱን ይወዳል፣ ተፈጥሮን ይወዳል። ይሄንን የሚነግረን ግን በእጅ አዙርና በስውር እንጂ በጉልበቱ ተመክቶ በጠብ መንገድ ጉዳዩን እንደሚያስፈፅም ጎረምሳ አይደለም። ይልቁንም እንደ አሰላሳይ ባለ አዕምሮ ሰው እንጂ። ይሄ ነው ትልቁ የገጣሚ ብቃት።
ገጣሚው “ጥቢ በር” ብሎ በሰየመው የመድበሉ መግቢያ ላይ ያነሳው ሌላኛው ነገር ልጅነትን ነው። እንዲህ ይላል. . .
“ግጥምን ከምወድባቸው ዋነኛ ሃጃዎች አንደኛው፣ ልጅነትን ከነለዛ ቅጠሉ ስለሚያስታውሰን ነው። ስለሆነም ይሁነኝ ብዬ ባመጣኋቸው ጥቂት ግጥሞች አብረን እንቅበጥ” ብሎ አንባቢያንን ጭምር ይጋብዛል። በኔ እምነት እስካሁን ካየኋቸው የግጥም ሽብስቦች እንደ “ወደ መንገድ ሰዎች” ልጅነትን ከቁብ ቆጥሮ፤ በልጅነት ለዛ ስንኝ ሸምኖ ግጥምን ያለበሰን መድበል ያለ አይመስለኝም። ይሄን በማስረጃ ላቀርብ እችላለሁ. . .
ታላቁ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ፤ “የብርሃን ፍቅር” በተሰኘ መድብሉ ውስጥ “ልጅነት” የምትል ግጥም  እናገኛለን።
በዚህ የግጥም ሥራ ውስጥ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ “ልጅነት”ን በምልሰት ሊያስተዋውቀን ይሞክራል እንጂ በልጅነት ጫማ ቆሞ ፣ ልጅ ሆኖ ፣ እንደ ልጅ ታሞ፣ እንደ ልጅ ቦርቆ አይተርክልንም። ከጊዜ አንፃር ሙሉ ግጥሙን ባላሰፍረውም በስንኞቹ መሐል ግን ይሄን እናገኛለን… …
:
:
መች ጠፋችሁ
       ጓደኞቼ
       ካባ አልባሾቼ
እንደ ገዛኝ የልጅነት ሥልጣናችሁ?
የሕፃንነት ሞኝነት
የአዋቂ ብልጠት
ዙሪያ ቀለበት
የሕይወት ጉዘት።
:
:
በዛን የልጅነት መክሊት
ዛሬም እንነግድበት … …
በዚህ ስንኝ ውስጥ የምናገኘው “በዛን” እና “ዛሬን” የተሰኙት ቃላት የሚጠቁሙት ገፀ ሰቡ የልጅነት ጊዜው ካለፈ በኋላ በምልሰት የሚተርክልን፤ የልጅነት ዕድሜው ቆይታን መሆኑን ነው። ይሄ ብቻም አይደል። “እቴቴ” በተሰኘውም ሌላው ግጥሙ፣ ልጅነትን ያወሳል እንጂ ገፀ ሰቡ ግን ልጅ ሆኖ የተቀረፀ አይደለም። ገጣሚ መዘክር ግርማ በበኩሉ፤ በስራዎቹ ውስጥ ልጅነትን መስሎም፣ ሆኖም ሲያወጋን እናያለን። ይኸው ማሳያ. . .
“እዬ ንዬ ንዬ”
(የሕፃን ልጅ ግጥም) በሚለው ስራው ውስጥ የተቀረፀው ገፀ ሰብ ልጅነትን የተላበሰ ነው። ይሄን የሚያስረዳልን ሁለት ነጥቦችን ከጊዜ አንፃር አጠር አድርጌ ላንሳ።
፩) ሙሉ ግጥሙ በልጅ አፍ የሚነበብ መሆኑ ነው።
እርግጥ ይሄ ሀሳብ ብቻውን ላያሳምን ይችላል። አያቶች፣ ወይ አባቶች፣ ወይ ከፍ ያሉ ሰዎች፣ ከሕፃናት ጋር ወግ ሲገጥሙ፣ ጫወታ ሲያደምቁ በልጅነት አፍ ማውራታቸው የተለመደ ነውና ነው። ይሄን ለማሳመን እሩቅ መሄድ ሳይጠበቅብን፣  “አባትነት እኮ” ከሚለው ግጥሙ ላይ እነዚህን ስንኞች ለማሳያነት መጠቀም ይቻላል።
አባትነት እኮ ፣ አባትነት ማለት
ተኮሳትሮ መሮ ፣ ለመድሃኒትነት
በልብ ማፍሰስ ነው ፣ የ’ሹሩሩ ጅረት (ብሎ አፉን በፈታ ሰው አንደበት የአባትነትን ተግባር ከነገረን በኋላ)
እሹሉሉ ልጄ እምንድነው እሹ
እሹሉሉ ልጄ ትንሹ ቅዱሹ
ኸለ ኸነ ገታ ፣ ኸለ ኸነ ሽኮ
መኮለታተፍ ነው አባትነትኮ (ሲል ይተርክልናል።)
ከዚህም የምንረዳው፣ በዚህ ግጥም ውስጥ ያለውን ገፀ ሰብ ወክሎ፣ በልጅ አፍ ማውራትና እንደ ልጅ መተወን የሚችል ሁሉ፣ እራሱን ተክቶ ግጥሚቱን ማንበቡ በተገባ ነበር። ነገር ግን እውነትም ገጣሚው ለልጅነት ጊዜው ያለውን ከፍተኛ ስሜት ሊያጋባብን ስለሻተ፣ “እዬ ንዬ ንዬ” የሚለውን ግጥም ፤ በቅንፍ ውስጥ (የሕፃን ልጅ ግጥም) ብሎ ሀሳባችንን ሲያጥረው ፤ አድማሳችንን ሲገታው እናስተውላለን።
፪) ልጅነታዊ ሰላላ አመክንዮ
በዚህ ግጥም ውስጥ እንዲህ የሚል ስንኝ ሰፍሮ ይገኛል. . .
“ደሞ አሻንጉሊትሽ ፣ አንገቷን ሙቋታል
ልብስ ባመጣላት ፣ በጣ…ም ይበርዳታል”
በአዋቂዎች ዐይን ሲታይ የልጆች እሳቤ እንደ አካላቸው ትንሽ፣ እንደ ጅስማቸው ሰላላ ሆኖ መታየቱ አያጠራጥርም። በየትኛው ሀገር ነው “አሻንጉሊቷ ይሞቃታል” ብሎ አዋቂ ሰው ሀሳብ ላይ የሚወድቀው? በዚህም ብቻ አያበቃም። “አንሻንጉሊትሽ እንዳይሞቃት ልብስ ላምጣላት፤ ልብስ ባመጣላት በጣም ይበርዳታል” ይለናል። የዚህ አይነት የችግርና የመፍትሄ መጣረስ የሕፃንነት መገለጫ ነው።
ከሽፋን ስዕሉ ጀምሮ እስከ መድበሉ ፍፃሜ ድረስ በየስፍራው፤ ልጅነት በገጣሚው ብዕር ዘንድ አፅንኦት ተሰጥቶት ተደጋግሞ ተወስቷል። አንዲት ማጠናከሪያ የማጠቃለያ ስንኝ ላንሳ. . .
የገጣሚው ግጥምና የገጣሚው የልጅነት ዘመን፤ አካልና መንፈስ መሆናቸውን የሚያሳይ ግጥም፣ “ልጆች እንደነበርን” በሚል ርዕስ ሰፍሯል. . .
ልጅነታችንን ፣ “የሕይወት ታሪኬ” እያልኩ አላነሳም
የታሪካችንን ሕይወት ከቶ አልረሳም!…
ሌላኛው የመድበሉ ውበት አፈንጋጭነቱ ነው። በግጥም ውስጥ አፈንጋጭነት መልኩ ብዙ ቢሆንም፣ ለጊዜው በዳሰሳዬ ላነሳው የወደድኩት ግን ገፀ ጽሁፋዊ ማፈንገጥን ነው። አንድ ሁለቱን ብቻ ልጥቀስ፡፡ በመድብሉ ገፅ 65 እና 70 ላይ “አዉ…ሰዉ…መጣ…እ?!” እና “ደስ ይለኛል” የሚሉ ግጥሞች  ይገኛሉ። በሌላው ዓለምም ገፀ ፅሁፋዊ አፈንግጦት በስነግጥም ውስጥ በጉልህ ሲተገበር ይስተዋላል። በእኛ አገር የሥነግጥም ስራዎች ላይ የሉም ባይባልም መጠናቸው ትንሽ መሆኑን  በድፍረት መናገር እችላለሁ።
የሆነው ሆነና፣ ማንኛውም የሥነ-ግጥም አንባቢ፣ ገፅ 65 ላይ ያለውን ግጥም፣ አንዴ ተመልክቶ ይረዳዋል ማለት ይከብድ ይመስለኛል። ሥነግጥምን ለመረዳት ከሚያስችሉ ቁልፍ ነገሮች አንዱ፣ ለግጥሙ የተሰጠውን ርዕስ መመርመርና መረዳት መቻል ነው። በዚህም የተነሳ “አዉ…ሰዉ…መጣ…እ?!” የሚለውን በx ምልክት የሰፈረውን ግጥም፣ ከርዕሱ መፍቻ ቁልፍ እየተነሳን ግጥሙን መረዳት እንችላለን።
   አዉ … ሰዉ … መጣ … እ?!
አውርቶኝ                               አወራኝ
      አያቅም                    ብዙ ጊዜ
          ፈጣሪ               ስለፈጣሪ
               ስለ           ሰዉ
                     ሰዉ
              መጣፍ          እግዜር
   ይገልጥና                 ጠራህ ይላል
ምዕራፍ                               እራሱ
ይጠቅስና                             ሲጠራኝ
ይሄን ግጥም ልብ ላለው ሰው፤ የግጥሙ ሀሳብና ገፀ ጽሁፋዊ አፈንግጦቱ የሚጣረሱ አይደሉም። ይልቁንም የግጥሙን ሀሳብ የሚያጎላው እንጂ።
አዉርቶኝ አያውቅም ፈጣሪ ስለ ሰዉ
ሰዉ ስለፈጣሪ ብዙ ጊዜ አወራኝ
መጣፍ ይገልጥና ምዕራፍ ይጠቅስና
እግዜር ጠራህ ይላል እራሱ ሲጠራኝ
ይሄ ግጥም በX ምልክት የተቀመጠ ነው። ግማሹን የX አካል ብንሸፍነው፣ የV ወይም የራይት ምልክት ይሰጠናል። አንድ X የሁለት ራይቶች ጥምር ውጤት ነው። ያንዱ ሰው እውነት ለሌላው ሰው ሀሰት ሊሆን ይችላል። የሌላው ሰው እውነት ለአንዱ ደሞ ውሸት ሊሆን ይችላል።
ከሁሉም ተቀራራቢ የ X ፊደል ጫፎች ተነስቶ ወደ መሀል የሚሄድ መስመር ብንስል፣ የምናገኘው የቀስት ምስል መዳረሻው፣ የሁለቱ ራይቶች መጋጠሚያ ነጥብ ላይ ይሆናል። መጋጠሚያ ነጥቡ ጋ ያለው ቃል ደሞ “ሰዉ” የሚል ነው። ልክ እና እውነት። ስህተት እና ውድቀት፣ ከሰው ሰው ይለያያልና ነው፤ ማጠንጠኛውን “ሰው” ያደረገው ገጣሚው።
ሌላኛው ግጥም ገፅ 70 ላይ የሰፈረው “ደስ ይለኛል” የሚለው ስራ ነው። የግጥሙ ሀሳብ ውስጥ ገፀ ሰቡ ከጥቁር አሞራ ጋር እራሱን ሲያመሳስል ይስተዋላል። እያወሳ ያለው ስለ ጥቁር አሞራ ነውና “አሞራ ቀደደው ሰማይ አማረበት” የሚለውን ስንኝ፣ በደማቅ ጥቁር ቀለም ከሌሎቹ ስንኞች ለይቶ ከትቦት ይታያል። በደማቅ ጥቁር ቀለም መከተብ ብቻም ሳይሆን ክንፉን በዘረጋ የአሞራ ምስል ነው ስንኙን አስፍሮት የምናየው። በዚህ የተነሳ ምንም እንኳን የገፀ ጽሁፉ አፈንግጦት ከዚህ በተሻለ መልኩ መኳሸት የሚችል ቢሆንም፣ ገጣሚው ግን የማፈንገጥን እሳቤ በመድበሉ ውስጥ ማሳየት ችሏል እንድንል የሚያስደፍረን ይሆናል።
በዚህ መድበል ዙሪያ ብዙ ሰዎች የተሻለ ሀሳብ ሊሰጡበት እንደሚችሉ ይሰማኛል። እኔ ግን በወፍ በረር ከብዙ መዳፈር ጋር እንዲህ አየሁት። እናንተም አንብባችሁ የተሰማችሁን እንድትጋሩን በመጋበዝ በቀጣዩ ግጥም ልሰናበታችሁ።
እዬ ንዬ ንዬ
(የሕፃን ልጅ ግጥም)
እዝጋቤር ፀሐይን ፣ ጠዋት ሲጋግራት
ኋላ ስትበስል
እሳት ስትመስል
ፈረሴን ቼ ብዬ ፣ አመጣልሻለሁ።
ደሞ ሣር ቀለበት
መታረቂያ ጣትሽ - ላይ እንዳረግልሽ
አብረን እንጫወት ፣ ወንድም አይደለሁ?!
እሺ … እምቢ ነው? - ተይው
ትልቅዬ እቃቃ ፣ ከሰማይ ያከለ
አባባ ሲመጣ ፣ ያመጣልኝ የለ!
ደሞ ደሞ ደሞ …
ቢራቢሮ አለችኝ - አዘፍናታለሁ።
ኋላ ስትታለብ ፣ ወተት አላቀምስሽ!
ኋላ ስትታለብ ፣ ወተት እንድሰጥሽ
አብረን እንጫወት ፣ ወንድምሽ አይደለሁ?!
ደሞ አሻንጉሊትሽ አንገቷን ሙቋታል
ልብስ ባመጣላት ፣ በጣ…ም ይበርዳታል
እሺ ልብስ ላምጣ?
እሺ አመት በዓል ሆኖ ፣ እምቧዬ ላዋጣ
ተይው!
እኔኮ ትልቅ ነኝ ፣ አያት ዓመቴ ነው
አንቺኮ ትንሽ ነሽ ፣ አሸንፍሻለሁ።
ቤትሽን አይተሽ ነው - አይደል እምቢ ያልሽው?
ቆይ ትመጫታለሽ … … እሄድልሻለሁ!!
ደሞኮንዬዬ………እዬንዬንዬ
የናንተ ቤት ትንሽ ፣ የኛ ትልቅዬ
ዝናቡ አሳደገኝ ፣ ከሚመጣበት ላይ
ከዝጋቤር ቤት ጋራ ፣ ቤት አለን ከሰማይ።
ፈረሴን ቼ ብዬ ፣ በኋላ እንድወስድሽ
አብረን እንጫወት ፣ ተዪ ግን ስወድሽ
ተይ?!……

Read 2251 times Last modified on Saturday, 14 December 2019 15:44