Saturday, 30 November 2019 12:11

አውራ ዶሮ ራሱ ሳይነቃ ሌላውን አይቀሰቅስም

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  አንዳንድ ዕውነቶች ሲያረጁ ተረት ይመስላሉ፡፡ ትምህርትነታቸው ግን ዘመን - ተሻጋሪ ነው፡፡
ባለፈው ዘመን አንድ ሰው ጐረቤቱን በፖለቲካ ሰውነት (በመንግሥት ወጋኝነት) ይጠረጥረዋል:: በጣም ስለሚፈራውም  ግራ ቀኙን እያጣራ ነው መንገድ የሚሄደው፡፡ ሲወጣ ሲገባ ባየው ቁጥር እየተሸማቀቀ ነው የሚያልፈው፡፡ ጐረቤትዬው ኮስታራ ነው፡፡ ግን ሰው ቀና ብሎ ያይም:: ልጆቹ ከልጆቹ ጋር ሊጫወቱ ሲመጡ፤ “እናንተ ልጆች አርፋችሁ ቤታችሁ ተቀመጡ፡፡
ኋላ ጣጣ ታመጡብኛላችሁ!” እያለ ይቆጣቸዋል፡፡
የልጆቹ ኳስ ጐረቤትየው ግቢ ከገባ፤ ጭንቅ ነው።
“ይሄዋ እንደፈራሁት መዘዝ ልትጐትቱብኝ ነው!” ብሎ ያፈጥባቸዋል፡፡
ሚስት ትሄድና ኳሱን ታመጣለች፡፡ ጐረቤታሞቹ ሚስቶች ቡና ይጠራራሉ፡፡
ይሄኛው ባል፤
“ኋላ ነግሬሻለሁ፡፡ አፍሽን ሰብስበሽ ተቀመጪ፤ ምን ፍለጋ ቡና እንደሚጠሩሽ አይታወቅም” እያለ ያስጠነቅቃታል፡፡
 “ኧረ እኛ ምንም የፖለቲካ ነገር አናወራም፡፡ ሞኝ አደረከን እንዴ” ትለዋለች ሚስት፡፡
ባል፤ 
“አሄሄ አይምሰልሽ! ዛሬ ሣር - ቅጠሉ የሰው አፍ ጠባቂ ነው፡፡ ይቺ ሴትዮ እያዋዛች እንዳታወጣጣሽ!”
ሚስት፤
“ቆይ፤ መጀመሪያ ነገር፤ እኔ ምን አለኝና ነው እምታወጣጣኝ? ምን የደበቅኩት ፖለቲካ አለኝ?”
ባል፤
“እኔ አላውቅልሽም ወዳጄ! ብቻ ጠንቀቅ ነው!” ይላትና ይወጣል፡፡
አንድ ቀን እዚሁ ጐረቤት ጠበል ተጠሩ፡፡
ሚስት ለባሏ፤
“ጠበል ተጠርተናል ጐረቤት፡፡ እንሂድ?”
ባል፤ “አልሄድም” ይላል፡፡
ሚስት፤ “አክብረው ጠርተውሃል ምናለ ብትሄድ” ብላ ትሞግተዋለች፡፡
ባል፤ “አልሄድም ብያለሁ አልሄድም”
“እሺ፤ ለምን ቀረህ ቢሉኝ ምን እመልሳለሁ?”
“ትንሽ አሞት ተኝቷል በያቸው በቃ” አለ ቆጣ ብሎ፡፡
 ሚስት ሄደች፡፡ ባል ቀረ፡፡
አንድ ቀን ታዲያ አጋጣሚ ሆኖ ባል ወደ ሥራ ሊሄድ ውይይት ላይ ተሳፍሯል፡፡ ጫፍ በሩ ጋ ነው የተቀመጠው፡፡
ጐረቤትየው በዛው ታክሲ ሊሳፈር ይመጣል፡፡ ሳያስበው እግሩን ረግጦት ይገባል፡፡
ይሄኔ ባል ወደ ሰውዬው ዞር አለና፤
“ወንድሜ፤ የከፍተኛ ሊቀመንበር ነህ እንዴ?” ብሎ ይጠይቃል፡፡
“አይደለሁም” ይለዋል ጐረቤትዬው፡፡
“የቀበሌ ሊቀመንበር ነህ?”
“አይደለሁም”
“የአብዮት ጥበቃስ?”
“አይደለሁም”
“እሺ ካድሬ ነህ?”
“አይደለሁም”
“ታዲያ ምናባክ ያራግጥሃል? ና ውጣ ከፈለክ ይዋጣልን!”
“ኧረ ወዳጄ እኔ ምንም ጠብ ውስጥ የምገባ ሰው አይደለሁም፡፡ አሁን የጠየከኝን ሁሉ “አንተ ነህ” ብዬ ስንት ዘመን ስሰጋና ስፈራህ ኖርኩኮ!” አለው፡፡
*    *    *
ጥርጣሬ ቤቱን የሠራበት ማህበረሰብ ደስተኛና በተስፋ የተሞላ አይሆንም፡፡ መጠራጠርና መፈራራት ባለበት ቦታ ግልጽነት ድርሽ አይልም፡፡ አሜሪካዊው የንግድ ሰው ማክ ዳግላስ፤ “ጭምት ነብሶችን ትናንሽ ጥርጣሬዎች ለውድቀት ይዳርጓቸዋል፡፡ ጠባብ አመለካከት ያለው፤ ፍርሃት የወረረውና አመንቺ ህብረተሰብ ሽንፈቱን ያረጋገጠ ነው” ይለናል፡፡
“ጠርጥር” የሚል ዘፈን በሚያስደስተው ህብረተሰብ ውስጥ እርግጠኝነትን ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። ይሄ ሥር ከሰደደ ደግሞ መድሐኒት አይገኝለትም፡፡ “በሽታው ሥር-የሰደደ ከሆነ ሞቱንም መዳኑንም መተንበይ አስተማማኝ አይደለም” ይለናል የግሪኩ የህክምና አባት፤ ሒፖክራተስ፡፡
ጥርጣሬ የበዛበት ማህበረሰብ አገር ለመገንባት አስተማማኝ ኃይል አይሆንም፡፡ መልካም አስተዳደርን ለማበልፀግ ይከብደዋል፡፡ ከእያንዳንዱ ድርጊት ጀርባ አንድ ጥርጣሬ እየኖረን ወደፊት መራመድ አይቻልም:: ግልፅነት ከሌለ ዴሞክራሲ ደብዛው ይጠፋል፡፡ ኢ-ፍትሐዊነት ይነግሣል፡፡ ሙስና ያጥጣል። ሚስጥራዊነት ያይላል፡፡ በመጨረሻም፤ “በልቼ ልሙት!” መፈክር ይሆናል!! በሀገራችን ታሪክን እንኳ በጥርጣሬ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የተዘመረላቸው አሉ፡፡ ያልተዘመረላቸው አሉ፡፡ እየተዘመረላቸው የማይታወቁ አሉ፡፡ ለምሳሌ የሰላሌው ጀግና አቢቹ፡፡ አዶልፍ ፓርለሳክ እንደፃፈው፤ “ይቺ አንድ ፍሬ ደጃዝማች! ከኛ በላይ ጀብዱ እየሰራች መሆኑን እንሰማለን!” አሉ አሉ ጃንሆይ፤ ስለ አቢቹ ሲናገሩ፡፡
“አቢቹ ነጋ ነጋ …. ቆሬን ሲወራኒኒ ለቺቱ ነጋ ነጋ …… አምቱን ሲላሊኒ”
(“አቢቹ ሰላም ሰላም አቢቹ እሾህ አይውጋህ አቢቹ ክፉ አይይህ አቢቹ ዐይን አያይህ” እንደማለት ነው፡፡)
ይህ የተዘፈነው ለአቢቹ ነው፡፡ ዛሬም ይዘፈናል፡፡ ግን አቢቹን ሰው አያውቀውም “ዛሬ አዝማሪው ሳይቀር ስለ ራሶች ጀግንነትና ስለ ንጉሠ ነገሥቱ ታላቅነት፤ ማንጎራጎሩን እርግፍ አድርጎ ትቶታል…” ይለናል፤ ያው ፀሐፊ፡፡ ልብ ያለው ግን የለም፡፡ ምናልባት የነገሥታቱ
ጀግኖች እንዳይወደሱ ሆን ተብሎም ታሪክ ተጋርዶ ይሆናል፡፡ ይሄም ያው ጥርጣሬ ነው፡፡
ስለ መሪዎች ትተን ስለ ህዝብ ወይም ስለ ህዝባዊ ጀግኖች እንዘምር ነው ነገሩ፡፡ ያልነቃ ህብረተረሰብ ተጠራጣሪነቱ ያይላል፡፡ በዕውቀትና በትምህርት ያልዳበረ ማህበረሰብ ተጠራጣሪነቱ ያይላል። የማይተማመኑ ፖለቲከኞች ያሉትና የሚመሩት ማህበረሰብ ተጠራጣሪነቱ ያይላል፡፡ በዚህ ላይ ከፖለቲካው ሥርዓት ጋር አለመግባባት ከተጨመረበት ጨርሶ ማበድ ነው፡፡ “ማሰብም ሊገታ ይችላል” እንዳለው ነው፤ቲዮዶር አዶርኖ-የጀርመኑ ፈላስፋ፡፡ “አንበሳና የበግ ግልገል አብረው ሊተኙ ይችላሉ፡፡ ችግሩ የበግ ግልገሏ እንቅልፍ አይኖራትም” ይላሉ ፀሐፍት፡፡ እንደተጠራጠረች መንጋቱ ነው ማለታቸው ነው፡፡
ከጥርጣሬ የምንወጣው ዕውነቱን በማወቅ ነው፡፡ መረጃዎች በቀጥታ ሲደርሱ ነው፡፡ መረጃ ሲጠራ ዕውነት ማየት ይጀመራል፡፡ ካልጠራ ጎሾ ያጎሸናል፡፡ የተማሩ ያስተምሩ፡፡ የነቁ ያንቁ፡፡ ያወቁ ያሳውቁ፡፡ “አውራ ዶሮ ራሱ ሳይነቃ ሌላውን አይቀሰቅስም” የሚባለውን ልብ እንበል፡፡

Read 12886 times