Saturday, 23 June 2012 07:50

የፖለቲካ “ቅሸባ” - ከዲሞክራሲ እስከ ምርጫ!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(0 votes)

ህገመንግስትም ይቀሸባል - በአምባገነን መሪዎች

የዛሬ ፖለቲካዊ ወጋችን በቅሸባ ዙሪያ ያጠነጥናል - ይመቻችሁዋል አይደል? (አይዞአችሁ ምቾታችሁን የመቀሸብ ዓላማ የለኝም!) ይሄውላችሁ … ባለፈው ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ስብሰባ ላይ፣ አገራችን ስለተዘፈቀችበት የሙስና ጉድ ሲያስረዱ፤ “የመንግስትና የግል ሌቦች” ያሉት ነገር በትክክል የገባኝ አሁን ነው - ወዳጄ ስለቅሸባ ካወጋኝ በኋላ፡፡ በነገራችሁ ላይ እሳቸው እንዳሉት ቅሸባም የመንግስትና የግል አለው (የመንግስትና የግል ቀሻቢዎች እንደማለት!)።

ሰሞኑን በኢቴቪ፣ የግል ኢንቨስተሩ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በቂ አቅም መገንባት ያልቻለበትን ምክንያት በተመለከተ የመንግስት ባለስልጣናትና የንግዱ ማህበረሰብ ውይይት ሲያደርጉ ነበር - ብቻቸውን ሳይሆን በኢቴቪ ጋዜጠኛ አወያይነት (አፋጣጭነት ቢባል ይሻላል)። እኔን ያስገረመኝ ታዲያ ምን መሰላችሁ? የጋዜጠኛው የጥያቄ አቀራረብ፡፡ (መርማሪ ፖሊስ የመሆን ተስፋ አለው)። “የግል ኢንቨስተሩ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በቂ አቅም ላለመገንባቱ ተጠያቂው ማነው? መንግስት ነው የግሉ ሴክተር?” በማለት አንዱን መርጣች ተጠያቂ ካላደረጋችሁት አለቃችሁም ብሎ ድርቅ አይል መሰላችሁ! እኔ የምለው… በአማን አገር ማፋጠጥን ምን አመጣው? (ወይስ ማስፈራራቱ ነው?) “ሃርድ ቶክ” ነገር እየተለማመደብብ ከሆነ ደግሞ በግልፅ ይንገረን (ለተጋበዙትም ያሳውቃቸው!)

ይኸውላችሁ ዛሬ ቅሸባን አጀንዳችን ያደረግሁት አዲስ ነገር ተፈጥሮ አይደለም፡፡ (አይዞአችሁ --- አገር አማን ነው! የባእድ ወራሪም አልመጣም)። የሚቀሸበውም የሚቀሽበውም የአበሻ ልጅ እኮ ነው!

በእርግጥ ዛሬ የማስቃኛችሁ እስከዛሬ በተለምዶ ከምናውቃቸው ለየት ያሉ ቅሸባዎችን ነው፡፡ ከየት አመጣኸው የሚለኝ ካለ … ያለስፖንሰር በግል ተነሳሽነት ካካሄድኩት መጠነኛ ጥናት እለዋለሁ፡፡

ወዳጆቼ፤ ቅሸባ መኪና ላይ በተጫነ ቡናና በቦቴ ነዳጅ ላይ ብቻ... ከመሰላችሁ በጧም ተሸውዳችኋል፡፡ በጥናቴ ውጤት መሰረት፤ በአሁኑ ጊዜ ቅሸባ የማይገባበት የህይወት ዘርፍ የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ፖለቲካውን እንኳን አልማረውም እኮ! ደግሞ ቀላል እንዳይመስላችሁ - የፖለቲካ ቅሸባ!

ለምሳሌ ከሚገባው የስልጣን ዘመን በላይ በፈጣጣ ከቤተመንግስት አልወጣም ያለ ወይም ደግሞ አስከሬኔ ነው ከፓላስ የሚወጣው ብሎ ግግም ያለ መሪ ካለ፤ እሱ ስልጣን ቀሻቢ ነው ማለት ነው፡፡ አጢናችሁ እንደሆነ... አንዳንድ የአፍሪካ አምባገነን መንግሥታት የሥልጣናቸውን ሳይጠግቡት ሊያልቅባቸው ሲል (ከሃያ ዓመት በኋላ ማለት ነው)፤ ህገ መንግሥት ደልዘው  የስልጣን እድሜያቸውን ያራዝማሉ - የስልጣን ቅሸባውን በህገወጥ መንገድ ህጋዊ በማድረግ፡፡ እኒህ አይነቶቹ ደግሞ የሥልጣን ብቻ ሳይሆን የህገ መንግሥትም ቀሻቢዎች ናቸው፡፡ ስንቱ የአፍሪካ መሪ ይሆን የአገሩን ህገመንግስት ስልጣኑን ለማራዘም ሲል የቀሸበው? የየአገሩ መከረኛ ህዝብ ይቁጠረው!  (ስፖንሰር ከተገኘ ግን እኔም ልቆጥረው እችላለሁ)

በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ዝነኛ የሆነ ሌላ የፖለቲካ ቅሸባ ደግሞ አለ - የምርጫ ቅሸባ ይሉታል - ኒዮሊበራል የፖለቲካ ተንታኞች፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ድምፅ ማጭበርበር በማለት ይጠሩታል፡፡ በዚህ ስልት ብዙዎቹ አምባገነን መሪዎች የሥልጣን ዕድሜያቸውን  አራዝመዋል - በተደጋጋሚ፡፡ ችግሩ ግን በአንድ ዓመት ብቻ ሶስት የአፍሪካ አምባገነኖችን ከስልጣን የገረሰሰው የ”ፌስ ቡክ አብዮት” ወይም ህዝባዊ አመፅ ሲከሰት ማምለጫ የላቸውም - ስልጣን ከመልቀቅ በቀር፡፡ ያኔ ከምርጫም፤ ከሥልጣንም ቅሸባ ይሰናበታሉ - እንደነሙባረክ!

ገዢው ፓርቲያችን (ያው ኢህአዴግን ማለቴ ነው) ግን በአብዛኛው ሲተች የምንሰማው በአዋጆችና በህጐች ቅሸባ ነው፡፡ ኢህአዴግ ህግ ባወጣ ቁጥር በዲሞክራሲ የዳበረ ልምድና ተመክሮ ካላቸው አገራት “ቃል በቃል የቀዳሁት ነው” ቢልም ተቀናቃኞቹ ግን ኢህአዴግ ሁሌም ከውጭ የሚቀዳው “ክፉ ክፉውን ነው” ሲሉ ክፉኛ ይተቹታል (ይሆን እንዴ?)

በዲሞክራሲ ቅሸባማ ማን ይችለዋል ይላሉ - ተቃዋሚዎች (ኢህአዴግን እኮ ነው!) እንዴት ብሎ ለጠየቃቸው ታዲያ ማብራራት አይሰለቻቸውም፡፡ አውራው ፓርቲ (ኢህአዴግ ይሄን ስሙን በፈቃዱ ትቶታል ልበል)፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ከመቼው የበለጠ ተመቻችቷል ይበል እንጂ፤ ተቃዋሚዎች ግን የፖለቲካ ምህዳር በመቀሸብ ኢህአዴግን የሚስተካከል የለም ባይ ናቸው (ቻይናም ብትሆን!፡፡ አባላቶቻችን ይዋከባሉ፣ ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ ወዘተ --- የሚሉት ተቃዋሚዎች፤ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ የፍትህና ነፃነት መጉዋደል ከእለት ወደ እለት መባባሱን ይጠቅሳሉ፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ከዚህ በላይ እሽኮኮ ላደርጋቸው ስለማልችል ሌላ አገር ሄደው ተቃዋሚነትን ይሞክሩት ይላል (እቺማ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ቅሸባ ናት!) ይሄን ጊዜ ተቃዋሚዎች ሆድ ይብሳቸውና የኢህአዴግን የመቀሸብ “አሻጥር” (ሚስጥር) ያፍረጠርጡታል - የመሰብሰብና የስብሰባ አዳራሽ ቅሸባ፣ የተቃውሞ ቅሸባ፣ የፕሬስ ነፃነት ቅሸባ፣ የሰብአዊ መብት ቅሸባ፣ የሲቪል ማህበራት መብት ቅሸባ፣ የተቃዋሚ እስረኞች መብት ቅሸባ ... እያሉ፡፡

በነገራችሁ ላይ የሩሲያው መሪ ፑቲንም የህግ ቅሸባ ፈፅመዋል ተብለዋል - ሰሞኑን፡፡ ባልተፈቀደ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፈ ግለሰብ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል የሚለው አዲሱ የፑቲን ህግ ተቃውሞ ቢያስነሳም እሳቸው ግን በአውሮፓውያን ስታንዳርድ የወጣ ነው ብለዋል (የቀለጠ የህግ ቅሸባ ማለት ይሄ ነው)።

እኔና እናንተን ይታክተን ይሆናል እንጂ የአበሻ ቅሸባ ማለቂያ የለውም - በጥናቴ ውጤት መሰረት፡፡ በቃ የመንግስትና የግል ቀሻቢዎች ኑሮአችንን እየቀሸቡ እነሱ በሰላም ይኖራሉ፡፡

እኔ የምለው የሚኒባስ ረዳቶችን ቅሸባ “ነቄ” ብላችኋል? ለምሳሌ ታክሲ ተሳፍራችሁ ስትሄዱ ረዳቱ፤ ሳያውቅ በስህተት፣ አውቆ በድፍረት ከ5 ሳንቲም ጀምሮ መልስ ያረሳሳችሁ የለ! እናንተም ረስታችሁ ልትወርዱ ትችላላችሁ - አንዳንዴ፡፡ ያኔ ቅሸባ ተሰራች ማለት ነው፡፡ ማን ላይ? እናንተ ከፍላችሁ የምትጓዙት የኑሮ ውድነት ተቀሻቢዎች  ላይ! ታክሲዎች እያቆራረጡ ሲሄዱም መቀሸባቸው እኮ ነው! የመዲናችን አንዳንድ ሉካንዳ ቤቶች ደግሞ ከእያንዳንዱ ኪሎ ሥጋ ላይ 300 ግራም ገደማ ይቀሽባሉ የሚል መረጃ አግኝቻለሁ (ማስረጃ ያልተገኘለት)፡፡ አንዳንድ ወተት አከራዮችም ወተት ይቀሽባሉ ይላል - ጥናቴ፡፡  (በውሃ እያቀጠኑ) ለህፃናት እንኳን ማዘን ቀረ እንዴ?

በነገራችሁ ላይ ዳቦም ትቀሸባለች - ግራም በመቀነጫጨብ፡፡ በደርግ ዘመን በርበሬ ከቀይ ሸክላ ጋር ተደባልቆ  ሲቀሸብ የነበረውን መቼም ለናንተ አልነግራችሁም፡፡ (ጨካኙ ደርግ “ስግብግብ ነጋዴዎች” እያለ ቀሸባቸው እንጂ!) ቅቤ ደግሞ ከሙዝ ጋር ነው የሚቀሸበው አሉ፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ … ቅሸባ በሽበሽ ነው ይላል - ያለአንዳች ስፖንሰር አድራጊ የሰራሁት ጥናቴ፡፡ (ልብ አድርጉ ጥናቴ አልተቀሸበም!) ከፍ ወዳለው ስትሄዱም እኮ ውስኪ አለላችሁ፡፡ “የተወጋ ውስኪ” ሲባል አልሰማችሁም? የውስኪ ቅሸባ እኮ ነው!

ግን እኮ… ወደ ሆድ የሚገባ ብቻ እንዳይመስላችሁ የሚቀሸበው… የአዕምሮ ምግብም በደንብ ይቀሸባል፡፡ በዋናነት የሚቀሸበው ግን ምን መሰላችሁ?  ትምህርት!! ባለፈው ጊዜ ስንቶቹ የግል ኮሌጆች የተዘጉትና ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው በምን መሰላችሁ? ትምህርት በመቀሸብ እኮ ነው! (ትውልድ መቀሸብ በሉት!) እነዚህ እንግዲህ የግል ቀሻቢዎች መሆናቸው ነው (የግል ኮሌጆች)፡፡ የቀድሞዋ የትምህርት ሚኒስትር፤ (ህንድ ያሉት) የትምህርት ስርዓቱ ትውልድ ገዳይ ነው በሚል ትችት ሲሰነዘርባቸው ምን እንዳሉ ታስታውሳላችሁ? “የሚገድል ከሆነም ይግደል” (ሲያናድዱዋቸው ምን ይበሉ?)  እኚህ የቀድሞ ሚኒስትር እንዴት የአምባሳደርነት ሹመት እንደተሰጣቸው ለማወቅ ጥናት ማካሄድ ይጠይቃል! (የዲፕሎማትነት አዝማሚያ አይታይባቸውም ብዬ እኮ ነው!)

አንዳንድ የትምህርት ኤክስፐርቶች ትምህርት በመቀሸብ ዙሪያ በሰጡኝ አስተያየት፤ ከግል ቀሻቢዎች የባሱት የመንግስት ቀሻቢዎች እንደሆኑ ነግረውኛል፡፡ አያችሁ… የትምህርት ቅሸባ እኮ ይሄን ያህልም ውስብስብ አይደለም፡፡ ለምሳሌ መንግስት አያሌ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ቢከፍትም ጥራት ያላቸው ተማሪዎችን አሰልጥኖ ለማውጣት አቅም ያንሳቸዋል የሚል ትችት ይሰነዘርባቸዋል አይደል - በቂ መምህራንና ፋሲሊቲዎች የሉዋቸውም በሚል፡፡ በቃ መንግስት በአገሪቱ ትምህርት ላይ ሃይለኛ ቅሸባ እያካሄደ ነው ማለት ነው (ሳያውቀው!) ሌላ ምሳሌ እነሆ፡- 12 ዓመት ሙሉ እንግሊዝኛ ተምረው የስማቸውን ስፔሊንግ እንኳን በወጉ የማይፅፉ ወጣቶች እንዳሉ ሳትሰሙ አልቀራችሁም፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ቅሸባ ማለት እኮ ይሄ ነው፡፡ ት/ሚኒስቴር ወይም ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚል አካል “የትምህርት ቅሸባ የለም” ብሎ የሚከራከር ከሆነ መድረኩ ክፍት ነው (እኛ ጋ ነፃ ሃሳብ አይቀሸብም!)

በየክልሉ ይሄን ያህል ት/ቤቶች ተከፍተዋል ሲባል ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? ሌላ መረጃ ደግሞ በእነዚያ ት/ቤቶች ከተማሩት መካከል 35 በመቶው ማንበብ አይችሉም ይላችሁዋል፡፡ እናስ --- የትምህርት ቅሸባ አለ የለም? ሞልቷ እንጂ!

ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከአንጋፋው የመንግስት ዩኒቨርስቲያችን፤ አንድ “የግል ቀሻቢ” አድኖ ክስ መመስረቱን  ሰምታችኋል? ግለሰቡ በዩኒቨርስቲው ሬጅስትራር ሲሰራ ለበርካታ ተማሪዎች ገንዘብ እየተቀበለ ግሬድ አስተካክሏል ተብሏል፡፡ ለምሳሌ No Grade ለተባለ ተማሪ “C” ሰጥቷል፡፡ በርካታ ተመሳሳይ ቅሸባዎችን የፈፀመው ግለሰብ ፍርዱን እየተጠባበቀ ነው፡፡ (ፍርድ እንኳን አይቀሸብም!) እውነቱን ልንገራችሁ አይደል... ይሄን ከሰማሁ በኋላ እንኳንስ የሌላውን ዲፕሎማና ዲግሪ ቀርቶ የራሴንም መጠራጠር ጀመርኩ - የተቀሸበ ድግሪ ቢሆንስ? በሚል፡፡ በማዕረግ የተመረቁ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ሁሉ መፈተሽ ሊያስፈልገን እኮ ነው፤ ወይም መጠራጠር!!

ይሄን የቅሸባ ፅሁፍ እያጠናቀርኩ ሳለ ፊት ለፊቴ በተከፈተው የኢቴቪ መስኮት ምን ሰማሁ መሰላችሁ? በአንድ የመንግስት ሆስፒታል ላይ የተነጣጠረ እሮሮ። በሆስፒታሉ ለመታከም የሚመጡ በሽተኞች፣ ቁጥራቸው ፈፅሞ ከሃኪሞች ጋር አይመጣጠንም ተባለ። እንዴት ሲባል፣ በሆስፒታሉ 53 ሃኪሞች መመደብ ሲገባቸው ያሉት ግን 13 ብቻ ናቸው ይላሉ - የሆስፒታሉ እሮሮ አቅራቢዎች፡፡ አንዲት በሆስፒታሉ ተኝተው ሲታከሙ የነበሩ እናት ደግሞ “ሳህን እንኩዋን የላቸውም” ሲሉ አጋለጡ - ሆስፒታሉን፡፡ የምን ሳህን መሰላችሁ? ህመምተኞች የሚመገቡበት፡፡ እና በምን ይበላሉ? እኔም ሰፍ ብዬ የጠበቅሁት የዚህን መልስ ነበር፡፡ “አንድ ቀን ነርሱዋ ምግብ ይዛ መጣችና ኮመዲኖው ላይ ልገልብጥልሽ? አለችኝ” ብለዋል - ቅሬታ አቅራቢዋ፡፡ አያችሁልኝ… የጤና ቅሸባ! (የህይወት ወይም የነፍስ ቅሸባ ቢባል አይሻልም?)

የተባበሩት መንግስታትን የሚሌኒየም ግብ በጥራት ሳይሆን በቁጥር ብቻ ለማሳካት የሚደረግ ሩጫም ሆነ እሽቅድድምም እኮ ደንበኛ ቅሸባ ነው!! በአገራችን ባሁኑ ጊዜ ከምንም በላይ አደገኛ ቅሸባ ነው የሚባለው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? መሬት  መቀሸብ!!  ስንቶቹ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በመሬት ቅሸባ ወህኒ ቤት ቢገቡም አሁንም ቀጥሏል - ቅሸባው! ለካስ ጠ/ሚኒስትሩ “መረጃ የተገኘባቸውን  ስናስር አዳዲስ ወንጀለኞች  ይፈጠራሉ” ያሉት እውነታቸውን ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ በራስም ሆነ በወዳጅ ዘመድ ስልጣን ያለአግባብ መቅበጥ (መባለግ) ያው ስልጣን መቀሸብ ነው፡፡ (ለጠቅላላ ዕውቀት ያህል ነው!)

ጥቂት ደግሞ የኪነጥበብ ቅሸባን ቃኘት እናድርግ - በስሱ፡፡ ከባህር ማዶ ዜማ ወስደው የራሳቸው አስመስለው የሚያቀርቡ አርቲስቶች አልገጠሟችሁም? - እነሱ የዜማ ቀሻቢዎች ናቸው፡፡ የህንድ ፊልምን አይዲያ መንትፈው በአማርኛ የሚያቀርቡ የፊልም ቅሸባ “ስፔሻሊስቶች” እንዳሉም አለመዘንጋት ደግ ነው!! ነገርዬው ምን መሰላችሁ? ማንም ይሁን ማን የራሱ ያልሆነውንና የማይገባውን ነገር መንትፎ ከወሰደ ወይም ለሌላው መስጠት የሚገባውን ያለአግባብ ካስቀረ ሌላ ስም የለውም - ቀሻቢ እንጂ! አሁን ለምሳሌ መብራት ሃይል ሳናስበው መብራት ድርግም ያደርግብን የለ? (ያውም ሳይነግረን!) መብራት እየቀሸበ እኮ ነው! ኢትዮ ቴሌኮም ደግሞ ኢንተርኔትና ኔትዎርክ ይቀሽባል፡፡

አብዛኞቹ የመንግስት መ/ቤቶች ያማረሩን ግን በምን መሰላችሁ? በመረጃ ቅሸባ! መረጃ ፈፅሞ አይደማቸውም፡፡ ከደማቸውም ደግነት ይጎድላቸዋል። በእርግጥ የአዲስ አበባ ከንቲባ የተከበሩ ኩማ ደመቅሳ፤ ሰሞኑን በቲቪ መስኮት ብቅ እያሉ ለጥያቄዎቻችሁ መልስ እሰጣለሁ፤ ጠይቁኝ እያሉን ነው (አሁን የኛ ጥያቄ ጠፍቷቸው ነው ወይስ ሊያስለፈልፉን ፈልገው?)

በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገታችን ከ11 በመቶ በላይ መድረሱን ቢደሰኩርም እዚህች ባለሁለት ዲጂት አሃዝ ላይ የደረሰው እድገቱ የምር ሆኖ ሳይሆን በቅሸባ ነው ይላሉ - ሁነኛ ውስጥ አዋቂ ምንጮች፡፡ እንዴት ሆኖ  ሲባሉ፤ IMFን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ - የ2012/13 እድገት 7 በመቶ እንደሚሆን መተንበዩን በመጠቆም (ግን እኮ ይበቃናል - ቁጥር አይበላ!)እንግዲህ እንዳልኳችሁ ቅሸባ ያልገባበት የለም! አንዳንድ ቱባ የሃይማኖት አባቶች በማያገባቸው ገብተው ፖለቲካውን ሲፈተፍቱ አልታዘባችሁም? በዚሁ ከቀጠሉ እኮ “የሃይማኖት ቅሸባ” ሊጧጧፍ ነው ማለት ነው፡፡ የፍቅርና የትዳር ቅሸባስ? የትዳር ቅሸባ እኮ ሌላ እንዳይመስላችሁ - ሚስቱን ቤት ውስጥ ዘግቶባት ሲያበቃ ከዚህችና ከዚያችኛዋ ጋር ወጣ ገባ ሲል ነው፤ ወይም ባሏን ትታ ከሌላ ጋር ሸብ ረብ ስትል ነው ቅሸባ የሚባለው (ቅሸባ ስለበዛ እኮ ነው ፍቺ የበዛው! ይላሉ የትዳር ኤክስፐርቶች)። የሆኖ ሆኖ… የቅሸባ እስረኞች (ሰለባዎች) መሆናችን በደንብ እየታየልን ነው!! አንድዬ ከቅሸባ ይገላግለን!! (ፀረ - ቅሸባ ኮሚሽን ለማቋቋም አስቤአለሁ!!)

 

 

Read 3360 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 07:58