Saturday, 30 November 2019 12:07

የምርጫ ቦርድና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ ባለመግባባት ተበተነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ማስፈፀሚያ ረቂቅ ህግ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ሰሞኑን የጠራው ስብሰባ ባለመግባባት ተበተነ፡፡ የውይይቱ ተሣታፊዎች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ የስብሰባው ዓላማ በምርጫ ማስፈፀሚያ ረቂቅ ህግ ላይ ውይይት ለማድረግ የነበረ ቢሆንም ቀደም ብሎ በፓርላማው ፀድቆ አዋጅ በሆነው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ ላይ ያለን ቅሬታ በድጋሚ ይታይ የሚል ሃሳብ በማንሣታቸው በተፈጠረው አለመግባባት ስብሰባው ሊቋረጥ ችሏል፡፡ ፓርቲዎቹ “አዋጁን ሳንቀበለው በአዋጅ ማስፈፀሚያ ላይ መወያየት አንችልም” ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው፤ አዋጁ በፓርላማው የፀደቀ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ቦርዱን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ቦርዱ ለፀደቀው አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብ ማውጣቱንና ፓርቲዎች በማስፈፀሚያ ደንቡ ላይ ሃሳብና አስተያየታቸውን  እንዲሰጡ ስብሰባውን ማዘጋጀቱን የገለፀ ሲሆን የፖለቲካ ድርጅቶቹ ተወካዮች ግን ከዚህ በፊት በአዋጁ ላይ የሠጠነው ሃሳብ ተቀባይነት ባለማግኘቱ፣ በማስፈፀሚያ ደንቡ ላይ ሃሳብ ለመስጠት አንችልም በማለት የስብሰባውን አካሄድ ተቃውመዋል፡፡
ይሄን ተከትሎም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢና አመራሮች፤ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ለሌላ ጊዜ ለውይይት ተዘጋጅተው እንዲመጡና ጥያቄና ቅሬታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ጠይቀው፣  ለግማሽ ቀን ተጠርቶ የነበረው ስብሰባ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መበተኑ ታውቋል፡፡   

Read 10282 times