Saturday, 30 November 2019 11:54

‹‹የዋለልኝ የብሄሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ›› ጽሑፍ 50ኛ ዓመት ታስቦ ዋለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  በጽሁፉ መነሻነት ሴሚናር ተካሂዷል
                        
               የዋለልኝ መኮንን ‹‹የብሄሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ›› በተሰኘውና ላለፉት 50 ዓመታት ከፍተኛ ተፅዕኖ ባሳደረገው ጽሑፍ ላይ ‹‹የዋለልኝ የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በኋላ›› በሚል ርዕስ ከትላንት በስቲያ በሸራተን አዲስ ሴሚናር ተካሄደ፡፡ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ጥናት ተቋም አዘጋጅነት በተካሄደው ሴሚናር ላይ ‹‹የዋለልኝ የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ›› የተሰኘው ጽሑፍ ባለፉት ሀምሳ ዓመታት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሊህቃን እንዲሁም የፓርቲዎች አስተሳሰብና የፖለቲካ ፕሮግራም ምህዳርን በእጅጉ የተቆጣጠረ እንደነበር ተወስቷል፡፡
በጽሑፉ የተካተቱት እምቅ ነገር ግን ግዙፍ ሀሳቦች በርካታ አስርት ዓመታትን ከተሻገሩ በኋላ ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እሳቤ እውን እንዲሆን መነሻ ሆነው ስለማገልገላቸውም ተገልጿል፡፡ በዕለቱ በዚህ ሴሚናር ላይ ንግግር ካደረጉት ምሁራን መካከል በካናዳ ዊልፍሪድ ለውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ጉዳዮች መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ማርታ ኩዊ ኩምለ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት እጩ ተመራቂ የሆኑት ስሜነህ አያሌው፣ የፖለቲካ ምሁር የኦነግ መስራችና በሽግግሩ ወቅት የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)፣ የኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ኤግዚኪዩብቲብ ዳይሬክተርና የቀድሞው የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) አባል የነበሩት አቶ ታምራት ከበደና በኢንስቲትዩት ፎር ሴኪዩሪቲ ስተዲስ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሰሚር ዮሴፍ (ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡
ተናጋሪዎቹ የዋለልኝ 50 ዓመታትን የተሻገሩ እሳቤዎች አሁንም ገዝፈው የሚታዩ ስለመሆናቸው፣ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በጥልቀትና ባለማቋረጥ እስካሁን ጊዜ ስለመዝለቃቸው፣ እሳቤዎቹ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አስተሳሰብ አቅጣጫ ተፅዕኖ ያሳደሩና አሁን የምንገኝበትን ጊዜ ቀድመው የተመለከቱ ስለመሆናቸው በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ በሴሚናሩ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለፈውን የግማሽ ምዕተ አመት የፖለቲካ ጉዞ የተዳሰሰ ሲሆን ሴሚናሩ የዋለልኝ አስተሳሰብ ጥሎት ያለፈውን የፖለቲካ ዳራና የአገራችንን ሁሉን አቀፍ ፌደራላዊ ፕሮጀክቶች በጥልቀት ዳስሷል፡፡

Read 2013 times