Saturday, 30 November 2019 11:52

እነ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በ111 የማይጠቅሙ ራዳሮች ግዥ ጉዳይ አዲስ ክስ ተመሰረተባቸው

Written by  መታሰቢያ ከሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

  ለህዳር 30 የክስ መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ፍ/ቤት አዟል
                                     
               የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከቻይና በተገዙና ጥቅም ላይ ሊውሉ በማይችሉ የአንድ መቶ አስራ አንድ ራዳሮች ግዥ ጉዳይ በቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውና ሌሎች 3 ግለሰቦች ላይ አዲስ ክስ መሰረተ፡፡
ትናንት በዋለው ችሎት፤ ተከሳሾቹ ህዳር 30 ቀን 2012 ከጠበቆቻቸው ጋር ተማክረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
የመንግሥትን ስራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከግዥ መመርያ ውጪ ጥራቱን ያልጠበቀ ራዳር ግዥ ለመፈፀም ከ214 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት በመንግሥት ላይ ጉዳት ከባድ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው፣ በሌተና ኮሎኔል ፀጋዬ አንሙት፣ በኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታና በኮሎኔል መሀመድ ብርሃን ላይ አቃቤ ህግ ክስ መስርቷል፡፡
የፌደራል ዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያመለክተው፤ ተከሳሾቹ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በ2004 ዓ.ም ከኮርፖሬሽኑ የግዥ መመሪያ ውጪ፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የግዥ ፍላጎት ሳይጤቅ ያለጨረታ ከቻይና ኩባንያዎች የአንድ መቶ አስራ አንድ ራዳሮች ግዥ ፈጽመዋል፡፡
የተገዙት ራዳሮች በአገር መከላከያ ሰራዊት የመስክ ሙከራ ሲደረግባቸው እጅግ ኋላ ቀር የሆኑ፣ ወጣ ገባ ለሆኑ መልክአ ምድሮች የማያገለግሉ፣ ሰው እንስሳትና ሌሎች ግዑዝ ነገሮችን ለመለየት የማያስችሉ፣ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የሚያስቸግሩና በቀላሉ ለመጠቀም የሚያዳግቱ መሆናቸው መረጋገጡን የዐቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ከ214 ሚ. ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው እነዚህ ራዳሮች እስከ አሁን ድረስ ያለ አገልግሎት በመጋዘን ውስጥ እንዲከማቹ መደረጋቸውን የጠቆመው ዐቃቤ ሕግ፤ ተከሳሾቹ በሕዝብና በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስና በከባድ የሙስና ወንጀሎች ክስ እንደተሰመረተባቸው አመልክቷል፡፡
ክሱ በጹሑፍ የደረሳቸውና በችሎት በንባብ የቀረበላቸው ተከሳሾቹ፤ የተከሰሱበት ወንጀል ከባድ በመሆኑ ጠበቃ ይዘው መከራከር እንደሚፈልጉ ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውን ተከትሎ ፍ/ቤቱ  ጠበቆቻቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ለትናንት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን፤ ትናንት በዋለው ችሎት ተከሳሾቹ ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበዋል፡፡ ፍ/ቤቱም ተከሳሾቹ ከጠበቆቻቸው ጋር ተማክረው የክስ መቃወሚያቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ለህዳር 30 ቀን 2010 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ለጊዜው ያልተያዙት አራተኛው ተከሳሽ ኮሎኔል መሐመድ ብርሃን ካሉበት ተፈልገው እንዲቀርቡም ፍ/ቤቱ አዟል፡፡

Read 1132 times