Saturday, 23 November 2019 12:15

የኢትዮጵያዊቷ ደራሲ እንግሊዝኛ ልቦለድ ለአለማቀፍ ገበያ ቀርቧል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

     በኢትዮጵያዊቷ ደራሲ ምህረት አዳል ጊዲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተጽፎ በእንግሊዝ አገር ለህትመት የበቃውና “ብሊዲንግሃርትስ ኦፍ ኤ በተርፍላይ” የሚል ርዕስ ያለው አዲስ የረጅም ልቦለድ መጽሐፍ አማዞንና ጉድ ሪድስን ጨምሮ በተለያዩ የኢንተርኔት መገበያያ አውታሮች አማካኝነት ለአለማቀፍ ገበያ ቀርቦ እየተሸጠ መሆኑ ታውቋል፡፡
የ25 አመቷ ወጣት ደራሲ ምህረት አዳል ጊዲ፤ ለህትመት ያበቃችው የመጀመሪያ መጽሐፏ የሆነው “ብሊዲንግ ሃርትስ ኦፍ ኤ በተርፍላይ” ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ መዲና ለንደን በሆነውና አለማቀፍ ዝናን ባተረፈው ኦስቲን ማኩሊ አሳታሚነት ለገበያ መብቃቱን ደራሲዋ በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልጻለች፡፡
በዚህ ታዋቂ ኩባንያ አማካይነት መጽሐፉን የማሳተሙን እድል ያገኘችው በእንግሊዝ አገር በተካሄደ አለማቀፍ የመጽሐፍ ሽፋን ሂስ ውድድር ማሸነፏን ተከትሎ እንደሆነ የገለጸችው ደራሲዋ፣ በ206 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ በአለማቀፍ ደረጃ በስፋት እየተሸጠ እንደሚገኝም ጠቁማለች፡፡ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሁፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በተቀበለችው ምህረት አዳል ጊዲ በዋናነት በአንደኛ መደብ ነጠላ የትረካ አንጻር የተጻፈውና ጠንካራ የሴራ መዋቅር እንዳለው የተነገረለት “ብሊዲንግ ሃርትስ ኦፍ ኤ በተርፍላይ”፣ እየቅል የሆኑት የፍቅርና የአስፈሪ ዘውጎች በሚገርም ሁኔታ በአንድ ላይ ተሰባጥረው የሚገኙበት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የማንበብና የመጻፍ ዝንባሌና ፍቅር ያደረባት ገና በለጋ ዕድሜዋ እንደነበርና ከአዲሱ መጽሐፍዋ በተጨማሪ ሌሎች ዘጠኝ ያህል መጽሐፍትን ጽፋ ማጠናቀቋን የምትናገረው ደራሲዋ፣ መጽሐፍቱን ለማሳተምና ለአንባብያን ለማድረስ ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን አዲስ ታሪክ እየጻፈች እንደሆነም ገልጻለች፡፡
አንባብያን አዲሱን መጽሐፏን ከአማዞን፣ ኦስቲን ማኩሊ፣ ቤተር ወርልድ ቡክስ፣ ፎየልስ፣ ጉድ ሪድስ፣ ኢቤይ እና ሌሎች በርካታ አለማቀፍ የኢንተርኔት የሽያጭ ድረ ገጾች ላይ ማግኘት እንደሚችሉም ደራሲ ምህረት ጠቁማለች፡፡

Read 12087 times