Saturday, 23 November 2019 11:53

የቀድሞ የፀረ ሽብር ህግ ሠለባዎች መንግስትን ሊከሱ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  የቀድሞ የፀረ ሽብር ህግ ሠለባዎች ለደረሰባቸው የስነልቦና አካላዊና ማህበራዊ ጉዳት መንግስትን በፍ/ቤት ለመክሰስ ማቀዳቸውን አስታወቁ፡፡
በቁጥር 3 መቶ ያህል የሚሆኑት የቀድሞ የፀረ ሽብር ህግ ሠለባ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ እና ሌሎች ግለሰቦች ከ14 ወራት በፊት በማህበር መልክ ተሰባስበው መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀው ጥያቄያቸውም ተቀባይነት አግኝቶ የነበረ ቢሆንም እስከዛሬ ተግባራዊ ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ የኮሚቴው ህዝብ ግንኙነት አቶ ዳንኤል ሽበሽ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ባለፈው አመት ጥር 2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ በተገኙበት በአዲስ አበባ ካፒታል ሆቴል ከፀረ ሽብር ህጉ ሠለባዎች ጋር ውይይት ተደርጐ እንደነበር እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይም ጥያቄው ለጽሑፍ ቀርቦላቸው እንደነበር ለአዲስ አድማስ ያስረዱት አቶ ዳንኤል በወቅቱ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣችኋል ቢባልም ጉዳያችን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል ብለዋል፡፡ በወቅቱ ለመንግስት ቀርበው የነበሩት ጥያቄዎች በእስር ላይ የቆየን ሰዎች አጠቃላይ ህይወታችን ተናግቷል፣ ኢኮኖሚያዊ መሠረታችን ተናግቷል፣ ኢኮኖሚያዊ መሠረታችን ተናግቷል፣ ጤንነታችን ተጋድሏል በሚል መነሻ ጤንነታቸው የተጋደለ በመንግስት ወጪ የሚታከሙበት፣ ከስራ የተባረሩ ወደ ስራ የሚደጐሙበትና እንደገና የሚቋቋሙበት፣ ከድር ካስፈለጋቸው ከድር የሚመቻችበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚሉት ከቀረቡት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ እነዚህን ያካተተ ሰባት ዋነኛ ጥያቄዎች ለመንግስት ቀርበው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዳንኤል ከቀረቡት ጥያቄዎች እስከዛሬ አንዱም አልተመለሰም ብለዋል፡፡
ታስረው ከተፈቱት መካከል መኖሪያ ቤታቸውን አጥተው በረንዳ እያደሩ ያሉ አባላትም አሉ ያሉት አቶ ዳንኤል መንግስት የፀረ ሽብር ህጉን ተጠቅሞ ንፁሃንን ሲያሸብር እንደነበር ባመነበት ሁኔታ ያለጥፋታቸው ህይወታቸው የተናጋ ሰዎች በድጋሚ የሚቋቋሙበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብለዋል፡፡
አባላቱም በነገው እለት ተገናኝተው ስብሰባ በማድረግ ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ መንግስትን በሚከሱበት ሁኔታ እንደሚወያዩ አቶ ዳንኤል ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡

Read 10429 times