Thursday, 21 November 2019 00:00

በአለም በየቀኑ 2 ሺ 200 ህጻናት በሳምባ ምች ይሞታሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   በአለማችን በእያንዳንዱ ቀን 2 ሺህ 200 ያህል ህጻናት በሳምባ ምች ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉና ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ በአለማችን 800 ሺህ ያህል ከ5 አመት ዕድሜ በታች የሚገኙ ህጻናት፣ በዚሁ በሽታ ሰበብ መሞታቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
የሳንባ ምች ሊከላከሉትና ሊያድኑት የሚችል በሽታ ቢሆንም ያን ያህል ትኩረት ስላልተሰጠው በተለይ ህጻናትን በከፍተኛ ሁኔታ ለሞት እንደሚዳርግ የጠቆመው ድርጅቱ፣ በአመቱ ከሌሎች በሽታዎች በበለጠ መጠን በርካታ ህጻናት በሳንባ ምች ለሞት መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡
በአመቱ ከሳምባ ምች ጋር በተያያዘ ለሞት ከተዳረጉት የአለማችን ህጻናት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአምስት የአለማችን አገራት ህጻናት መሆናቸውን የጠቆመው ድርጅቱ፣ 162 ሺህ ህጻናት የሞቱባት ናይጀሪያ ከአለማችን አገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንና በአገሪቱ በየቀኑ ከ440 በላይ ህጻናት ከሳምባ ምች ጋር በተያያዘ ለሞት እንደተዳረጉ ገልጧል፡፡
ከሳንባ ምች ጋር በተያያዘ ብዙ ህጻናት ለሞት የተዳረጉባት ሁለተኛዋ አገር ህንድ ስትሆን በአገሪቱ 127 ሺህ ህጻናት በበሽታው ለሞት መዳረጋቸው ተነግሯል፡፡ ፓኪስታን በ58 ሺህ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በ40 ሺህ፣ ኢትዮጵያ በ32 ሺህ ከሳምባ ምች ጋር በተያያዙ የጤና ችግሮች ለሞት የተዳረጉ ህጻናት እንደቅደም ተከተላቸው፣ ከሶስተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ድርጅቱ አመልክቷል፡፡

Read 4336 times