Tuesday, 19 November 2019 00:00

ሙሴቬኒን ለፍርድ ለማቅረብ ፊርማ እየተሰባሰበ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ኡጋንዳውያን ከሶስት አስርት አመታት በላይ አገሪቱን ያስተዳደሩትን ዮሪ ሙሴቬኒን፣ ዘ ሄግ በሚገኘው አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለመክሰስ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ መጀመራቸውንና እስካሁንም ከ800 በላይ ዜጎች ፊርማቸውን ማስፈራቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
“ፎረም ፎር ዲሞክራቲክ ፓርቲ” የተሰኘው የአገሪቱ ፓርቲ የቀድሞ መሪ በነበሩት ዶክተር ኪዛ ቢሴጅ አስተባባሪነት የተጀመረው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ፣ ሙሴቪኒንና ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናትን ለፈጸሙት ኢ-ሰብዓዊ የወንጀል ድርጊት በአለማቀፉ ፍርድ ቤት አቅርቦ የማስቀጣት ግብ እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፤ ግቡን ለማሳካት ቢያንስ የሁለት ሚሊዮን ሰዎች ፊርማ ማሰባሰብ እንደሚጠበቅባቸው  አመልክቷል፡፡
የዘመቻው አስተባባሪዎች፣ ዮሪ ሙሴቪኒ፣ በተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና በሌሎች ዜጎች ላይ እጅግ የከፋ የሰብዓዊ ወንጀሎችን እንደፈጸሙ የገለጹ ሲሆን ኡጋንዳውያንን በማሳመን ያሰባሰቡትን ፊርማ ለአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በማቅረብ ክስ እንዲመሰረትባቸው ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቪኒን በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለማስቀጣት ፊርማ ሲሰባሰብ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ ከሁለት አመታት በፊት በተመሳሳይ መልኩ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ተጀምሮ ከስኬት ሳይደርስ መቅረቱንም አስታውሷል፡፡


Read 4453 times