Sunday, 17 November 2019 00:00

ሂላሪ፤ ጫና ቢበዛብኝም ዳግም ከትራምፕ ጋር አልፎካከርም አሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ጂሚ ካርተር ሆስፒታል ገብተዋል

             ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዲሞክራቶችን ወክለው የተወዳደሩትና በሽንፈት የተሰናበቱት ሂላሪ ክሊንተን፤ በቀጣዩ ምርጫ ከትራምፕ ጋር ዳግም እንዲፎካከሩ ከተለያዩ አካላት ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሚገኝና እሳቸው ግን በፍጹም እንደማይወዳደሩ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ72 አመቷ ሂላሪ ክሊንተን፣ ከቢቢሲ ሬዲዮ 5 ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦችና ፖለቲከኞች በምርጫው እንዲወዳደሩ ከፍተኛ ጫና ቢያደርጉባቸውም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ባለፈው ወር ላይ ሄላሪን ወደ ምርጫው እንዲገቡ የሚገፋፋ ንግግር ማድረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ባለቤታቸው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተንም፣ ሂላሪ በቀጣዩ ምርጫ ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተው እንደነበር አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር፣ ባጋጠማቸው የጭንቅላት ህመም ሳቢያ ሰሞኑን ሆስፒታል መግባታቸውን ዋሽንግተን ፖስት ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡ የ95 አመቱ ካርተር፣ ድንገት ባጋጠማቸው የመውደቅ አደጋ የጭንቅላት መቁሰል እንደተከሰተባቸው ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህን ተከትሎ ከሚሰማቸው ከፍተኛ ህመም እንዲያገግሙ  ወደ ሆስፒታል መግባታቸውን አመልክቷል፡፡


Read 3097 times