Saturday, 16 November 2019 11:44

“ዘውድ ጫኑልኝ” ብሎ ነገር!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)


          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ከዚህ በፊት ያወራናት ነገር አለች:: በበፊተኛው ‘ስርወ መንግስት’ ጊዜ ነው:: (ቂ…ቂ…ቂ…) እናላችሁ… ይህ ወዳጃችን ምን ጊዜም ከኪሱ ፌስታል አይጠፋም:: በሆነ ቀበሌ ህብረት ሱቅ በኩል ሲያልፍ… የሆነ የሚሸጥ ነገር ሊገጥም ስለሚችል ጥንቃቄ መሆኑ ነው:: ከዕለታት አንድ ቀንም በሰሜን አዲስ አበባ አካባቢ ሲያልፍ ረጅም ሰልፍ ያያል:: ረጅም ሰልፍ ከሆነ…  ህብረት ሱቅ እንጂ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ ወዳጃችን ሰልፉን ያዘ፡፡ ሰልፉ እንደ ምንም እየተሳበላችሁ ዋናው ስፍራ  ደረሰ፡፡ ስፍራው ምን ቢሆን ጥሩ ነው…ጠጅ ቤት! አጋጣሚ ሆነና ወዳጃችን በ‘ቢጫዋ’ አይጨክንም ነበርና ገባላችሁ፡፡
እናላችሁ… ዘንድሮም የሰልፍ ነገር አልተወንም፡፡ ደግሞላችሁ በቅርብ ጊዜ የሚወገድም አይደለም፡፡ የምር ግን…በሰልፍ ተራ ጠብቆ አገልግሎት ማግኘት እኮ ምንም ክፋት የለውም፡፡ እንደውም ዘመናዊ አሠራር ነው፡፡ ‘ሰለጠኑ’ በሚባሉት ሀገራት እኮ በሬስቱራንቶች ሁሉ ሳይቀር ቦታ እስኪለቀቅ ሰልፍ አለ፡፡ (መቼም ‘ፈረንጅ’ የሚሠራው ሁሉ ‘ስልጣኔ’ ነው የሚል ያልተጻፈ ህግ ስላለ ምን እናድርግ…እንጥቀሳቸው እንጂ!) እናማ…እኛ አሁን በአንድ በኩል ግራ የገባን… ተቋማት አሠራራቸውን ዘመናዊ ማድረግ ባለመቻላቸው ብቻ በቀላሉ ሊያልቁ በሚችሉ ነገሮች ሁሉ እንድንሰለፍ መገደዳችን ነው፡፡
 እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አሁን ሌላው ዓለም የሚጠቀምባቸው እንደ ኢንተርኔት የመሳሰሉ የኢንፎሮሜሽን ቴክኖሎጂ ግብአቶች ሀሉም ዘንድ አሠራራቸው ተመሳሳይ አይደለም እንዴ! የሆኑ መላው ዓለም የሚጠቀምባቸው ዘመናዊ የሚባሉ ሶፍትዌሮች… አለ አይደል… ለእኛ ሲላኩ እንደ ዘመዶቻችን ፉርኖ የሚያደርግ ጫማ አይነት ሆነው ነው! እናማ…ሌላው ሀገር በሚሊዮኖችና በአስር ሚሊዮኖች ብቻ ሳይሆን በመቶ ሚሊዮኖች እያስተሳሰሩ ያሉ ቴክኖሎጂዎች፤ እኛ ዘንድ ሲደርሱ አንድና ሁለት ሚሊዮን ማስተሳሰር ያቃታቸው  ለምንድነው?!  
ሌላው ከሰልፍ ጋር ተያይዞ ግራ እየገባን ያለው ደግሞ ምን መሰላችሁ… በተለያዩ ስፍራዎች በሚፈጠሩ የአገልግሎት ጥበቃ ሰልፎች… ቅድሚያ እንዲሰጠን የምንፈለግ የ‘ልዩ ጥቅም’ ፈላጊዎች ነገር ነው፡፡
የተወሰኑት ወጣቶች፣ አብዛኞቹ አዛውንት እናቶችና አባቶች የበዙበት ሰልፍ ነበር…  የፈረደበት የኮረንቲ ሂሳብ ለመክፈል፡፡ (ኮረንቲ ያልነው ለምን መሰላችሁ… ሲቋረጥም ‘እየነዘረን’ ሂሳብ ስንከፍልም ‘እየነዘረን’ ስለሆነብን ነው፡፡) የሆነ ሽክ ያለ ባለ ከረባት ይመጣና ቀጥታ ወደ በሩ ይሄዳል፡፡ ልክ የተረከበው የአርባ ስድሳ ኮንዶሚኒየሙ ይመስል ዘው ብሎ ሊገባ ሲል ጥበቃዎቹ ያስቆሙታል፡፡ የተኮለኮለውን ሰው እያሳዩ ሰልፍ እንዲይዝ ይነግሩታል፡፡ አጅሬው… (ለጠቅላላ ዕውቀት ያህል… የ‘አጅሬዎች’ ቁጥር የህዝባችንን ስንት ስንተኛ ይሆናሉ?) እና አጅሬው ምን ቢል ጥሩ ነው? “እኔ ሥራ ስላላብኝ ወደ ቢሮ እሄዳለሁ” ምን? እና ምን ይጠበስ!
የምር ግን…አለ አይደል…ዓለም የትናየት በሄደበት ሰዓት አሁንም እንደ ኤልቪስ ጸጉርን መክፈል የስልጣኔ ጫፍ የሚመስለን ሰዎች… የአንዳንዶቻችን በባዶ ሜዳ መኮፈስ ግርም ይላል፡፡
(በነገራችን ላይ…ኤልቪስ ማለት የቼ ጉቬራ ወዳጅ ሳይሆን አሪፍ፣ ‘ቄንጠኛ’ የሚባል አይነት ዘፋኝ ነው፡፡ አይ…‘አይዴንቲቲ፣ ቅብጥርስዮ የሚባለው ነገር መምታታት… ‘መደበላለቅ’ ማለትም ይቻላል… ስለበዛ ለመረጃ ያህል ነው፡፡ ዘንድሮ እኮ ያልተደባላለቀ ነገር ያለ አይመስልም! በነገራችን ላይ ይቺ… ‘ቄንጠኛ’ የሚሏት ነገር በቃ ተሰወረች ማለት ነው! ነው… ወይስ በ‘ፍሪኪ’ ተተክታ ነው!)  
እናላችሁ… ‘ባለ ከረባቱ አጅሬ’ “እኔ ሥራ ስላላብኝ ወደ ቢሮ እሄዳለሁ፣” ሲል በተዘዋዋሪ እኮ መቶ ምናምን የሚሆነውና ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ገደማ ጀምሮ ተሰልፎ የቆመው ሰው… ለእሱ ሥራ የለውም ማለት ነው፡፡ ወይም ቢሮ የሚያስገባ ሥራ የለውም፡፡ እሱ ከረባት ስላደረገ ቢሮ ይሄዳል፣ እኛ የከረባት አንገት ስለሌለን ወደ የመንደራችን እንመለሳለን! (“ለከረባት የሚሆን አንገት በድሎሀል፣” ብላችሁ የምትዘባበቱብኝ ወዳጆቼ ምን መሰላችሁ… ዋናው ነገር ማስቀመጫው ሳይሆን የተቀመጠበት ነገር ጥራት ነው፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) እኛም እንዲህ ዙሩን እናክረው እንጂ! “በሶስት ሰዎች አስመሰክር፣” ብሎ ነገር የለ፣ “ይፍለጠኝ፣ ይቁረጠኝ…ብለህ ማል፣” ብሎ ነገር የለ…እንደፈለግን ራሳችንን፣ አይደለም ዘጠነኛው፣ አስራ ዘጠነኛው ደመና ላይ ማድረስ እንችላለን፡፡)   
እናላችሁ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በፖለቲካው እያወዛገበን ያለው ልዩ ጥቅም የሚባለው ነገር ገና ዓይኑን አፍጥጦ ይጠብቀናል፣ በጋራ አገልግሎት ስፍራዎች ‘ልዩ ጥቅም’ ፈላጊዎች ያለ ቅጥ በዛን፡፡ ያ ሰው ቢሮ ስለሚሄድ ብቻ (ጉድ እኮ ነው!) በ‘ልዩ ጥቅም’ በቀይ ምንጣፍ ላይ እንድናስገባው ይፈልጋል፡፡
“ዘውድ ጫኑልኝ፣” ብሎ ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
ስሙኝማ…እስቲ ፍተሻዎች አካባቢ ነገሬ ብላችሁ እዩልኛማ፣ ወይ ‘ከረባት ያሰረ’ ሊሆን ይችላል፡፡ (“አንተ ከከረባት ማሰር ጋር ችግርህ ምንድነው! አንተ ከረባት የምትለውን አንገትህ ላይ ስትቋጥር ለመዘነጥ ሳይሆን ሌላ ነገር ያሰብክ ያስመስልብሀልና እኛ ምን እናደርግ!” የሚል ሰው ቢገኝ፣ ጉዳዩን ወደ ሰፈር ልጅ ጉዳይ እንደማልጠመዝዘው ልብ ይባልልኝማ!)እናላችሁ … አብዛኛው ሰው በስነስርአት እጆቹን ወደ ላይ አድርጎ ይፈተሻል፡፡ ግንላችሁ… የሆነ በጉልበት ቪ.አይ.ፒ. ካላደረጋችሁኝ ባይ ሲመጣ… ነገርየው ለወጥ ይላል፡፡ እጆቹን በስርአት ለመዘርጋት እንኳን የሚጠየፍ ነው የሚመስለው!
በአንድ ወቅት አንዱ ከውጪ ሲያዩት ሸላይ የሚመስል፣ ሽክ ያለ ባለ ከረባት ይመጣል፡፡ ጥበቃው ሊፈትሸው እጁን ሲዘረጋ፣ እሱዬው አኳኋኑ እንዴት ነበር መሰላችሁ… በአንድ እጁ የቺስታ ቤት መስኮት የሚያክል ሞባይል ይዞ እያወራ፣ ሌላኛው እጁ  የት ቢሆን ጥሩ ነው… ኪሱ ውስጥ! ለማውጣት አንኳን አልሞከረም:: ምን አይነት ስፒሽስ እየተፈጠረ ነው?! (ቂ…ቂ..ቂ…)
እናላችሁ… ዝንብ እንኳን ያላረፈበት  ይመስል ገፋ አድርጎ ሊገባ ሲል… ጥበቃው ፊት ለፊቱ ቆመ፡፡ አጅሬው ኮስተር ለማለት ሲሞክር፣ ጥበቃውም ፊቱን መዶሻ የበዛበት የካባ ድንጋይ አስመሰለው፡፡ እናላችሁ…የፍተሻ ‹ልዩ ጥቅም› ፈላጊው ሳይወድ በግዱ ተፈትሾ ሳይሆን ተፈትጎ ገባላችሁ፡፡ (‘’ከመፈተግ ይሰውራችሁማ!)
“ዘውድ ጫኑልኝ፣” ብሎ ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
እግረ መንገድ ፍተሻን በተመለከተ አሁን የምናነሳው ነገር አለ…ፈረንጅ ሁሉ ማለት ‘ቅዱስ’ ነው ያለው ማነው! ላይም ታችም ያለነው ሁሉ እኮ የፈረንጅ ነገር ሲሆን ግራ የምናጋባ ሆነናል:: እና ጥበቃዎቻችን ሀሳብ አለን… የዘንድሮ ዓለም ምኗም አይታወቅምና፣ ወላ ፈረንጅ፣ ወላ ምን ሆኑ አይታወቅምና (ቂ…ቂ…ቂ...) እኛን ከምትፈትሹን የበለጠ ‘ፈረንጅ’ና ‘ፈረንጅ’ መሳዩን በሙሉ ከፈለጉ ‘ገለባ እስኪወጣቸው’… አለ አይደል… ‘ፈትጉልንማ!’
እኔ የምለው… ብዙ ቃለ መጠይቆች ስናይ ግራ የሚገቡን ነገሮች እየበዙብን ነውሳ! እናማ…አንጀታችንን ሲበላን እንዳይኖር ቢብራራልን… ተጋባዥ እንግዶቹ በሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች እንደየ ማነንታቸው  ልዩ ጥቅም የሚያገኙና የማያገኙ አሉ እንዴ! ነገሮች… የወጣቶቹን አነጋገር ለመዋስ… “ጦጣ እያደረጉን” ስለሆነ ነው፡፡
ስሙኝማ…የቃለ መጠይቅ ነገር ካነሳን አይቀር… ከ‘ቦተሊካው’ ውጪ ያሉ ቃለ መጠይቆች አሁንም… አለ አይደል… ‹‹ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ›› እንደሚሉት አይነት እየሆኑ፣ ሰዋችን “እርም ቃለ መጠይቅ፣” እንዲል አየተገደደ አይመስላችሁም!  
“ድርጅታችሁ የተቋቋመበትን አላማ ቢገልጡልን…” (እኔ የምለው..ለትርፍ ነዋ! ታዲያ የንግድ ድርጅት ለምን ሊቋቋም ኖሯል! “ፊኒቶ” እንደሚሉት የባጂዮ ሀገር ሰዎች፣ በቃ ይኸው ነው!!)
“እንግዲህ የእኛ ድርጅት የተቋቋመው፣” ይላሉ ባለሀብቱ፤ “በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ ያሉበትን ችግሮች ከስር መሠረታቸው ለመፍታትና ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ መካከለኛ ገቢ ለመግባት በምታደርገው ጥረት…”
ኧረ በህግ! ኧረ ፓራሲታሞል የማስታገስ ጉልበቱ አንድ መቶ ብራችን በሆነበት ዘመን ‘ክሬዚ’ አታድርጉን!
እናማ…በሆነ ምክንያት ስንትና ስንት ሰው… በፀሀይና በብርድ እየተንገላታ… አገልግሎት ለማግኘት እየጠበቀ ባለበት፣ ዘው ብላችሁ የንጉሠ ነገሥት አቀባበል እንዲደረግላችሁ የምትፈልጉ “ቅንጡዎች” ሆይ… ተዉን እንጂ!
“ዘውድ ጫኑልኝ፣” ብሎ ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2902 times