Saturday, 16 November 2019 11:32

መንግስት በዩኒቨርስቲ የተማሪዎችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ “አብን” ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 የግጭቶቹ መነሻ ተጠንቶ ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅም አሳስቧል


              መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ የጠየቀው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ የግጭቶቹን መነሻ ምክንያት በጥልቀት መርምሮ ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብም አሳስቧል::
ንቅናቄው ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ በወልድያም ይሁን በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የተከሰቱትን አስነዋሪ ተግባራት አውግዞ፣ መንግስት ጥቃት እየተፈፀመባቸው ባሉና በሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች ላይ የጥናታና የደህንነት መዋቅሩን በፍጥነት በማሰማራት ጉዳዩን በቁጥጥር ስር በማዋል ተማሪዎቹን ከጥቃት እንዲከላከልና ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡
በወልድያ፣ ደንቢዶሎ፣ በመደወላቡ፣ አለማያ፣ ጅማና በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች በደረሰው የተማሪዎች ግድያና የአካል ጉዳት ላይ በሃሳብ የተባበሩ፣ የፕሮፖጋንዳ ስራ የሠሩና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አካላት ላይ አስተማሪ የሆነ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ አበክሮ የጠየቀው አብን፣ የግጭቱና ጥቃቶቹ መነሻም በጥልቀት እንዲመረመር አሳስቧል፡፡
ህይወታቸውን ላጡ ተማሪዎች መንግስት በይፋ ይቅርታ እንዲጠየቅና ለቤተሰቦቻቸው ካሣ እንዲከፍል እንዲሁም የሌሎች ተማሪዎችን የደህንነት ዋስትና እንዲያረጋግጥም አብን በመግለጫው ጠይቋል፡፡
“በኢትዮጵያ ውስጥ ከህጋዊ ስርአት፣ ከእኩልነት፣ ከፍትህና ከዲሞክራሲ ውጪ ያለው አማራጭ ሁሉ የጋራ ጥፋት የሚያመጣ ነው” ያለው ንቅናቄው፤ ከሚነደው እሣት ማንም መትረፍ እንደማይችል ሁሉም ሃይሎች በአግባቡ ተገንዝበው አፍራሽ ሚና ከመጫወት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከሰሞኑ በአውሮፓ የእግር ኳስ ጨዋታ ምክንያት በወልድያ ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ህይወት ሲያልፍ፣ ከ10 በላይ መጐዳታቸው ተገልጿል፡፡ በተመሳሳይ፤ በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲም የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉን መንግስት አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በወልደያ ዩኒቨርስቲ ከተፈፀመው ድርጊት ጋር በተያያዘ 15 ያህል ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ በተመሳሳይ በደምቢዶሎ ከተፈፀመው ጥቃት ጋር በተያያዘም ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

Read 9740 times