Saturday, 16 November 2019 11:31

የሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሣኔ የፊታችን ረቡዕ ይካሄዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  የሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሳኔ የፊታችን ረቡዕ ህዳር 10 ቀን 2012 የሚካሄድ ሲሆን በዛሬው እለት የመራጮች ምዝገባ ይጠናቀቃል:: ነገ የመራጮች ሙሉ ዝርዝር መረጃ በየምርጫ ጣቢያው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
“ሲዳማ ራሱን የቻለ ክልል ይሁን” ወይስ “በነበረበት የደቡብ ክልል ይቀጥል” በሚሉ አማራጮች የሚካሄደው የህዝበ ውሳኔው ውጤቱም ከምርጫው ማግስት ጀምሮ በየምርጫ ጣበያዎች ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ከጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ሲካሄድ በቆየው የመራጮች ምዝገባ እስከ ባለፈው ሣምንት ሠኞ ድረስ 1.4 ሚሊዮን ያህል መራጭ እንደተመዘገበ የምርጫ ቦርድ መረጃ ያመለክታል፡፡
በነገው እለትም በየምርጫ ጣቢያው የተመዘገቡ ሰዎች ዝርዝር ማንነት ይፋ ይደረጋል ያለው ቦርዱ፤ ይህን ማድረግ ያስፈለገው ያለአግባብ በተሳሳተ መረጀ የተመዘገቡ ካሉ ለይቶ ለማውጣት ጠቃሚ በመሆኑ ነው ብሏል:: በምርጫው ከፍተኛ ተመዝጋቢ የታየባቸው አካባቢዎች፡- አርቤጐና፣ ሁላ፣ ወንሾ፣ ቦና ዙሪያ ሲሆን ዝቅተኛ ተመዝጋቢ የታየባቸው አካባቢዎች ደግሞ ሃዋሣ ዙሪያ፣ አለታ ወንዶና ዳራ መሆናቸውን የምርጫ ቦርድ መረጃ ያመለክታል፡፡
በምዝገባ ሂደቱ እስከ ትናንት ድረስ ያጋጠመ የፀጥታ ችግር አለመኖሩንም ቦርዱ አስታውቋል::
ለዚህ ህዝበ ውሣኔ 5.500 የምርጫ አስፈፃሚዎች ተመልምለው የተሠማሩ ሲሆን ቦርዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ውስጡ በግልጽ የሚታይ የድምጽ መስጫ ኮሮጆን እንደሚጠቀም አስታውቋል፡፡
ውጤቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ቅሬታ ያለው አካል፣ በየደረጃው እስከ ፍርድ ቤት የሚደርስ ክስ ማቅረብ እንደሚችልም ታውቋል:: ከህዝበ ውሣኔው ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን አስመልክቶ ጥቆማ የሚቀበልበት ነፃ የስልክ መስመር ማዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡ (251 994780288)  
በዚህ ህዝበ ውሣኔ ላይ በመራጭነት ተመዝግበው መሣተፍ የሚችሉት በዞኑ ለ6 ወር እና ከዚያ በላይ የቆዩ እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ መታወቂያ ያላቸው ነዋሪዎች ከሆኑ ነው ተብሏል፡፡

Read 10004 times