Saturday, 16 November 2019 11:30

የኮሪያ ዘማቾች የድጋፍ ማዕከል በአዲስ አበባ ተገነባ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  የደቡብ ኮሪያ መንግስት በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል በተደረገው ጦርነት ከደቡብ ኮሪያ ጐን ተሰልፈው ለተዋጉ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች የድጋፍ አገልግለት የሚውል ባለሁለት ፎቅ ህንፃ በአዲስ አበባ አስገነባ፡፡ የደቡብ ኮሪያ መንግስታዊ የዜና ወኪል የሆነው ኤ ኤን ኤ እንደዘገበው በአዲስ አበባ የተገነባው ባለሁለት ፎቅ ህንፃ በ712.8 ሜትር ስኩዬር መሬት ላይ ያረፈ እና በርካታ ክፍሎች ያሉት ነው፡፡ ህንፃው ለተለያዩ አገልግሎቶች እየተከራየም ለወታደሮችና ቤተሰቦቻቸው ድጋፍ የሚውል ገቢ እንዲያመነጭ መታሰቡን የጠቆመው ዘገባው ደቡብ ኮሪያ እንዲህ ያለውን የአገልግሎት ድጋፍ ማዕከል ከዚህ ቀደም በታይላንድ ባንኮክ እና በኮሎምቢያ በጐታ አስገንብታ ድጋፍ ላደረጉላት ለሀገሪቱ ወታደሮች ቤተሰቦቻቸው ማስረከቧ አስታውሷል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1950 እስከ 1953 በተደረገው የኮሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት 3.500 ወታደሮችን ኢትዮጵያ መላኳን ያስታወሰው ዘገባው በወቅቱ በጠርነቱ 122 ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ሲሞቱ 536 ያህሉ መቁሰላቸውን አስታውሷል፡፡ በጦርነቱ ከተሳተፉት መካከል 150 ያህሉ በህይወት እንደሚገኙም ዘገባው አትቷል፡፡
በጦርነቱ በአጠቃላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጥሪ ተቀብለው 2 ሚሊዮን የተለያዩ ሀገራት ወታደሮች መሳተፋቸውን 3ሺህ ዶክተሮች ለህክምና መሠማራታቸውን፤ በአጠቃለይ 40.670 ሰዎች መገደላቸውን፣ 104.280 መቁሰላቸውንና ከዘጠኝ ሺህ በላይ የሚሆኑት ጠፍተው መቅረታቸውን ሪፖርቱ አትቷል፡፡

Read 1117 times