Saturday, 16 November 2019 11:23

ኢንተሌክችዋል ት/ቤት በካምብሪጅ ስርዓተ ትምህርት የሚያስተምር ቅርንጫፍ ከፈተ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

   በ“ስቴም” ኤዱኬሽን ፒኤልሲ የሚተዳደረውና ሙሉ በሙሉ በውጭ ባለሀብቶች የተመሰረተው ኢንተሌክችዋል ት/ቤት 6ኛውንና በካምብሪጅ ሥርዓተ ትምህርት አገልግሎት የሚሰጠውን 6ኛ ቅርንጫፍ ከፈተ፡፡ ትምህርት ቤቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሶስተኛዋ የአለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መቀመጫ በሆነችዋ አዲስ አበባ የሚኖሩ አምባሳደሮች ዲፕሎማቶችና ዲያስፖራዎች በጠየቁት መሰረት መከፈቱንና ከ167 አገራት በላይ ተቀባይነት ባለው የካምብሪጅ ሥርዓተ ትምህርት የተቃኘ የትምህርት አገልግሎት ለመስጠት ፈረንሳይ ለጋሲዮን በተለምዶ ብረት ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የአውሮፓን ስታንዳርድ ጠብቆ መሰናዳቱን ባለፈው ሰኞ ት/ቤቱ አምባሳደሮች፣ የተማሪ ወላጆች የት/ት ቢሮ ኃላፊዎችና የት/ቤቱ ባለሀብቶች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ስራ በጀመረበት ወቅት ተገልጿል፡፡
ባለሀብቶቹ የዲፕሎማቶችን እና የዲያስፖራዎችን ጥያቄ ተቀብለው ከካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ጋር ለመስራት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ እንቅስቃሴ መጀመራቸው የተገለፀ ሲሆን፤ ህንፃውን ከኢትዮጵያዊ አከራይ ተከራይቶ ከወሰደ በኋላ ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ ደረጃውን ጠብቆ ለመገንባትና ለትምህርት ምቹ ለማድረግ ከ30 ሚ. ብር በላይ ማፍሰሱን የት/ቤቱ ባለቤቶች አስታውቀዋል፡፡ ካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የት/ቤቱን ግንባታና አደረጃጀት ሲከታተልና ሲገመግም ከቆየ በኋላም እውቅና የሰጠው ሲሆን፤ ‹‹IGCSE›› በተሰኘው በዚሁ የካምብሪጅ ሥርዓተ ትምህርት እንዲያስተምር እውቅና ሰጥቶታል፡፡
በምርቃት ሥነ - ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ዲያስፖራና ዲፕሎማት ወላጆች ኢንተሌክችዋል ት/ቤት ይህንን ቅርንጫፍ በመክፈቱ በአማራጭነት ቀርቦ እፎይታ እንደሰጣቸው ገልፀው፤ ልጆቻቸው እዚህ እስካሉ ድረስ ተምረው በስራ ምክንያት ወደየትኛውም ዓለም ቢዛወሩ ስርዓተ ትምህርቱ በዓለም ላይ ተቀባይነት ስላለው በሄዱበት ቦታ ልጆቻቸው ያለ ችግር ትምህርታቸውን ለመቀጠል ስለሚያስችላቸው ደስታ ተሰምቶናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኢንተሌክችዋል ት/ቤት በሳር ቤት፣ በዓለም ገና እና በመቀሌ አምስት ቅርንጫፎችን ከፍቶ ላለፉት 15 ዓመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ የ60 አገር ዜጐችን ከኬጂ እስከ 12ኛ ክፍል ሲያስተምር የቆየ ሲሆን፤ ባለፈው ሰኞ ተመርቆ ስራ የጀመረው 6ኛው ዓለም አቀፍ ቅርንጫፉ እንደሆነም ታውቋል፡፡

Read 2319 times