30ኛው ኦሎምፒያድ በዩቲውብ የቀጥታ ስርጭት እንደሚኖረው ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ያስታወቀ ሲሆን ውድድሩ በተለይ በሁለቱ የሶሻል ሚዲያ ገፆች ፌስቡክ እና ትዊተር ከዓለም ዙርያ በርካታ ስፖርት አፍቃሪዎችን በማሳተፍ ልዩ ድምቀት እንዲኖረው ታስቧል፡፡ ከ4 ዓመታት በፊት ቤጂንግ ያስተናገደችው 29ኛው ኦሎምፒያድ በትዊተር 6 ሚሊዮን በፌስቡክ ደግሞ 100 ሚሊዮን ስፖርት አፍቃሪዎች እንደተከታተሉት ሲታወስ ለንደን የምታስተናግደው 30ኛው ኦሎምፒያድ 140 ሚሊዮን የትዊተር መልክቶችን እንዲሁም ከ900 ሚሊዮን በላይ የፌስቡክ ግንኙነቶችን በመፍጠር አዲስ ክብረወሰን ይኖረዋል በሚል ተጠብቋል፡፡ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በትዊተር ገፁ 760ሺ ተከታታዮች በፌስቡክ ደግሞ 2.8 ሚሊዮን ታዳሚዎች እንዳሉት ሲያስታውቅ በኦሎምፒክ መንደር በሚሰጠው ሽፋን አትሌቶችንና መላውን የዓለም ስፖርት አፍቃሪ በልዩ ልዩ የመረጃ ልውውጦች ለማርካት ዝግጅቱን በማጧጧፍ ላይ ነው፡፡ ባለፈው ሰኞ የፌስቡክ ኩባንያ ልዩ የኦሎምፒክ ገፅ የከፈተ ሲሆን ይህ መድረክ በኦሎምፒኩ ተሳታፊ የሆኑ 60 አገራትና 200 አትሌቶቻቸው ከሚጠቀሙት የፌስቡክ አድራሻ ጋር ግንኙነት ፈጥሮ የሚሰራ ይሆናል፡፡